1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሩንዲ ምክር ቤታዊ ምርጫ መገፋት

ሐሙስ፣ ግንቦት 13 2007

ለዛሬ ሳምንት ማክሰኞ ታቅዶ የነበረው የብሩንዲ ምክር ቤታዊ ምርጫ በቀናት መገፋቱን የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ፕየር ንኩሩንዚዛ ትናንት አስታውቀዋል ። ከአንድ ወር በኋላ የተጠራው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በተቃደው ጊዜ ስለመካሄድ አለመካሄዱ ግን እስካሁን ግልፅ አይደለም ።

https://p.dw.com/p/1FTqu
Bujumbura Burundi Protest Gewalt
ምስል picture-alliance/D. Kurokawa

[No title]

ይሁንና የመንግሥት እርምጃ ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ የሥልጣን ዘመን መወዳደራቸውን የሚቃወሙ ኃይሎችን አላረካም ።የጎዳና ተቃውሞው ዛሬም ቀጥሎ ከፖሊስና ወታደሮች ጋር በተካሄደ ግጭት 2 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል ። የዶቼቬለው አንቶንዮ ካሳኬስ የዘገበውን ሂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች ።

ግንቦት18፣2007 ዓም ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው የብሩንዲ ምክር ቤታዊና አካባቢያዊ ምርጫ ተገፍቶ ግንቦት 28 2007 ዓም እንደሚካሄድ ተገልጿል ። የብሩንዲው ምርጫ በ10 ቀናት ስለመገፋቱ ከብሩንዲ ዋና ከተማ ቡጁምቡራ ትናንት የተሰማው ይህ ዜና ግን ጉዳዩን ሲከታተሉ ለቆዩ ታዛቢዎች አስገራሚ አልነበረም ።ቀኑ መገፋቱ የተገለፀው የሃገሪቱ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው ሃሳብ ተቃዋሚዎች የአፍሪቃ መሪዎችና ና ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም ምርጫው እንዲገፋ ከጠየቁ በኋላ ነው ። የጀርመን ዓለምዓቀፍና አካባቢያዊ ጥናቶች ተቋም የአፍሪቃ ጉፋዮች ጥናት ባልደረባ ዩልያ ግራውፎግል ምርጫው ሊገፋ የቻለው በምዕራባውያን ጫና ሊሆን እንደሚችል ነው የተናገሩት ።

« ምዕራባውያን ለምርጫው የሚሰጡት የገንዘብ ድጋፍ ትልቅ ሚና ይጫወታል ። 90 በመቶ የሚደርሰው የምርጫው በጀት የሚሸፈነው በዓለም ዓቀፍ ለጋሾች መሆኑን የተለያዩ ዘገባዎች ያስረዳሉ ።ያ ማለት ቤልጅየም ወይም ደግሞ ኔዘርላንድስና ስዊዘርላንድ የሚሰጡትን እርዳታ ከሰረዙ ለብሩንዲ መዘዞችን ማስከተሉ አይቀርም ።ዓለም ዓቀፉ ምህበረሰብ በአካባቢው ሃገራትና በብሩንዲ ላይ የተወሰነ ተፅእኖ ያደርጋል ።»

Bujumbura Burundi Protest Gewalt
ምስል Reuters/G. Tomasevic

ይሁንና የንኩሩንዚዛ ተቃዋሚዎች ምርጫው መገፋቱ ትርጉም የለውም ነው የሚሉት ።ነፃና ትክክለኛ ምርጫ ለማካሄድ ምርጫውን በአንድ ሳምንት መግፋቱ ብቻ በቂ አይደለም ይላሉ በምህጻሩ FNL የተባለው ተቃዋሚ ፓርቲ አባል አጋቶን ራዋሳ ። እንደ አለመታደል ሆኖ ፕሬዝዳንቱ ሁልጊዜ ሊቀልዱብን ይሞክራሉ ያሉት ራዋሳ የጎዳናዎች ፀጥታ እንኳን በቅጡ ሳይስተካከል ምርጫው እንዴት በጥቂት ቀናት ብቻ ይገፋል ሲሉም ይጠይቃሉ ።ራዋሳ እንደሚሉት ተቃዋሚዎች የምርጫ ቅስቀሳ እንዳያካሂዱ ልዩ ልዩ ወከባዎች ይደርሱባቸዋል ። ትናንት የምርጫ ዘመቻ ቁሳቁሶችን በመከፋፈል ላይ የነበሩ ጓዶቻቸው መታሰራቸውን ራዋሳ ተናግረዋል ። የብሩንዲ ምርጫ መገፋት ብቻውን ለሃገሪቱ ሰላም የሚበጅ አለመሆኑን የሚያሳስቡት ምዕራባውያን መንግሥታትም ጭምር ናቸው ። ይህን መሰል ስጋታቸውን ከገለፁት አንዱ የጀርመን መንግሥት ነው ። ግራውፎግል እንደሚሉት ጀርመን ለብሩንዲ መንግሥት ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች ።

«የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ለፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛና ለአካባቢው ሃገራት መሪዎች በላኩት ደብዳቤ ብሩንዲ ሰላም ካልወረደ ዲሞክራሲና የህግ የበላይነት ካልሰፈነ ለብሩንዲ የሚሰጠው የልማት እርዳታ ሊቆም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል ። »

Bujumbura Burundi Protest Gewalt
ምስል Reuters/J. P. Harerimana

መንግስት በበኩሉ ተቃዋሚዎች ተጨማሪውን ጊዜ እንዲጠቀሙበት እያሳሰበ ነው ። የተቃዋሚዎች አቤቱታ እንዲሁም የምዕራባውያን ማሳሰቢያ በቀጠለበት በዚህ ወቅት ላይ ለሰኔ 19፣2007 የተጠራው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በተያዘለት ቀን ስለመካሄዱ ከመንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም ።ግራውፎግል እንደሚሉት ኑኩሩንዚዛ ምርጫውን ለመገፋትም ሆነ ላለመገፋት ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊትጊዜያቸውን ወስደው ሊያስቡበት የሚገባ ጉዳይ ነው ።

«ፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ስለመገፋቱ አሁን ለመናገር አስቸጋሪ ነው ።ፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ቢገፋ እንደ ፕሬዝዳንታዊ እጩ ለንኩሩንዚዛ በጣም ጎጂ ነው።እንደ እኔ አመለካከት እርሳቸው ፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ከማድረጋቸው በፊት ሌሎች አማራጮችንም ቢያስቡ ነው የሚሻለው ።»

በፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ የስልጣና ዘመን መወዳደራቸውን የሚቃወሙ ወገኖች ዛሬም በአደባባይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል ። ጎማ ከሚያቃጥሉን ድንጋይ ከሚወረውሩ ተቃዋሚዎች ጋር የተጋጨው ፖሊስ አስለቃሽ ጢስና ጥይት ሲተኩስ ከመካከላቸው ሁለቱ ተገድለዋል ።

ኂሩት መለሰ

አርያም አብርሃ