1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባየር ሙኒክና የባርሴሎና ክለቦች ግጥሚያ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 29 2007

ትናንት በስፓኙ ባርሴሎና 3ለ0 የተረታው የጀርመኑ ታዋቂ የእግር ኳስ ክለብ ባየር ሙንሽን የአውሮፓ ክለቦች ሽምፕዮና ፍጻሜ ላይ የመድረስ ህልሙ የመነመነ መሆኑ እየተነገረ ነው ። ሆኖም የቡድኑ ተጫዋቾች ጠንከረንና ተባብረን በመስራት ህልማችንን እናሳካለን እያሉ ነው ።

https://p.dw.com/p/1FMQQ
Champions League Halbfinale Barcelona gegen Bayern München
ምስል Reuters/A. Gea

ትናንት ባርሴሎና ስፓኝ ውስጥ የባየርን ሙንሽንና የባርሴሎና የእግር ኳስ ቡድኖች ባካሄዱትየአውሮፓ ክለቦች የግማሽ ፍፃሜ ግጥሚያ ባየርን ሙንሽን የተሻለ ውጤት ይዞ ለመውጣት ከባድ ትግል ቢያደርግም አልተሳካለትም ። ቡድኑ በትናንቱ ጨዋታ በባርሴሎናዎቹ ሊዮኔል ሜሲና ኔይማር የኳስ ጥበብ ተበልጦ ሶስት ለባዶ ተሸኝቷል ።ባየርን የመጀመሪያው ከባድ ጥቃት የተሰነዘረበት ከ11 ኛው ደቂቃ በኋላ ነበር ። ሉዊስ ሳውሬዝ ወደ ግብ የላካትን ኳስ የባየርኑ ግብ ጠባቂ ማኑኤል ኖየር ባያድናት ከመረብ የምትዋሃድ የመጀመሪያ ግብ በሆነች ነበር ። ከሶስት ደቂቃ በኋላ ኔይማር በቅርብ ርቀት ያደረገው ሙከራም እንዲሁ አደገኛ ነበር ። የባየርኑ አሠልጣኝ ፔፕ ጉዋርድያሎ ከሁለቱ አደገና ሙከራዎች በኋላ በተከላካይ መስመር ያሰለፏቸውን ተጫዋቾች ቁጥር ከሶስት ወደ አራት ከፍ አደረጉ ። ይሁንና ከእረፍት በኋላ ባርሴሎናዎች ከ77ተኛው ደቂቃ አንስቶ 3 ግቦችን በማስቆጠር ጨዋታውን በድል ለማጠናቀቅ በቅቷል ። የባየር ሙንሽን ግብ ጠባቂ ማኑኤል ኖየር ሚሲ በባየርን ላይ ያስቆጠራት የመጀመሪያዋ ግብ ስጦታ ነበረች ይላል ።

«የመጀመሪያውን ግብ አመቻችተን ነበር የሰጠናቸው ። በግራ ክንፍ በኩል ብዙ ተጫዋቾች ነበሩ ።ያኔ ፈጥነን እርምጃ መውሰድ እንችል ነበር ። ምክንያቱም የባርሴሎና ተጫዋቾች ተበዚያ ቅፅበት በትጋት አልነበሩም የሚንቀሳቀሱት ።ከዳኛውም ጋር በመጨቃጨቅ ላይ ነበሩ ። ያኔ በዚያ ቅፅበት እድሉን ተጠቅመን አንድ ነገር ማድረግ እንችል ነበረ ። ተጫዋቾቹንም በቅብብል አጣድፈናቸው ነበር ። ይሁንና የአንዳንድ ግለሰብ ተጫዋቾች የላቀ ችሎታ ለምሳሌ የሜሲ ወደር የሚገኝለት ሆኖ አልተገኘም ።»

UEFA Champions League Lionel Messi 06.05.2015
ምስል Getty Images/S. Botterill

ጨዋታው 13 ደቂቃ ሲቀረው የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው ሜሲ ከሶስት ደቂቃ በኋላ ማለትም በ80ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን ግብ ደገመ ። የባየርኑ አሠልጣኝ ጉዋርድያሎ በሰጡት አስተያየት ቡድናቸው ለረዥም ጊዜ ጥሩ ጨዋታ ማሳየቱን ፣ ኳስም ወደ ባርሴሎናዎችን እግር እንዳትደርስ ብዙ መጣሩን ተናግረው ሆኖም ሚሲ ሁሉንም ነገር ቀይሮታል ብለዋል ። በ93 ተኛው ደቂቃ ላይ ኔይማር በባየርን ላይ ያገባት የመጨረሻው ሶስተኛ ግብ እግር ኳስ አፍቃሪዎችንም ሆነ ራሳቸውን የባርሴሎና ተጫዋቾችን አስደምሟል ። የባርሴሎናው ግብ ጠባቂ ማርክ አንድሬ ቴር ስቴገን

«አዎ ግልፅ ነው 70 ደቂቃ ሙሉ ያለ ምንም ግብ ቆይተን 3 ለባዶ ስናጠናቅቅ ማንም ሊገምት የሚችለው አልነበረም ። ሆኖም ያለውን እድል ሁሉ ተጠቅመናል ።ከመጀመሪያው ግብ በኋላ እንደገና ሌላ ደግመን፤ ሁለት ለባዶ ደረስን ።93 ተኛው ደቂቃ ላይ የገባው ሶስተኛው ግብ ሊቆጠርባቸው አይገባም ነበር ።ለባየርኖች መራር ግብ ነበር ።

Fußball Mario Götze Bayern München
ምስል AFP/Getty Images/Q. Garcia

በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሚካሄዱት የሁለተኛው ዙር የፍፃሜ ግጥምያዎች ከየምድቡ የላቀ ውጤት የሚያስመዘግበው ቅዳሜ ግንቦት 29 2007 በርሊን ላይ ለሚካሄደው የአውሮፓ ክለቦች ሻምፕዮና የዋንጫ ሽምያ ይሰለፋል ። ትናንት 3 ለባዶ የተረታው ባየርን ለበርሊኑ የፍፃሜ ጨዋታ ለማለፍ በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሜዳው ከባርሴሎና ጋር በሚያካሂደው ግጥሚያ ቢያንስ 3 ግቦችን ማስቆጠር ይጠበቅበታል ። አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ባየርን ለመጨረሻው ጨዋታ መብቃቱ ያጠራጥራል ይላሉ ። የክለቡ ተጫዋቾች ግን ጠንክረን በህብረት በመቆም የማሸነፍ ህልማችንን እውን እናደርጋለን እያሉ ነው ።

ኂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ