1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡኻሪ ድልና የናጀሪያ ፖለቲካ

ረቡዕ፣ መጋቢት 23 2007

ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች እንደተስማሙበት የቅዳሜዉ ምርጫ ቡኸሪን ለሥልጣን ማብቃቱ ከማሰገረሙ ይልቅ ጆናታን ሽንፈታቸዉን መቀበላቸዉ የዚያችን ሐገር ፖለቲከኞች ብስለት፤ አርቆ አሳቢነት፤ለሐገርና ለሕዝብ ተቆርቋሪነትን መስካሪ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1F1BT
ምስል Ekpei/AFP/Getty Images

ናይጄሪያ ዉስጥ ባለፈዉ ቅዳሜ በተደረገዉ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላሸነፉት ለተቃዋሚዉ ፓርቲ መሪ ለሙሐመዱ ቡኻሪ የሚተላለፈዉ የደስታ መግለጫ መልዕክት እንደቀጠለ ነዉ።የቀድሞዉ ወታደራዊ መሪና ጡረተኛ ጄኔራል ቡኻሪ በሥልጣን ላይ ያሉትን ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታንን ያሸነፉት በ2,75 ሚሊዮን ድምፅ ብልጫ ነዉ።ተመራጩ ፕሬዝዳንት ከአፍሪቃ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ሕዝብ ሐገር ናይጄሪያን ተብትበዉ የያዟትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች የማቃለል ከባድ ሥራ ይጠብቃቸዋል።የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ቡኸሪ በተለይ የአክራሪዉ ፅንፈኛ የቦኮ ሐራምን ጥቃትና ሥጋትን የማስወገድና ሙስናን የመዋጋት ከባድ ፈተና አለባቸዉ።

እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ1983 በመሩና ባቀነባበሩት መፈንቅለ መንግሥት የሌጎስን ቤተ-መንግሥት ተቆጣጥረዉ ነበር።ሜጄር ጄኔራል መሐመዱ ቡኻሪ።ከዓመት ከመንፈቅ በኋላ እንደሰቸዉ ያን ቤተ-መንግሥት ከሚመኙ ባንዱ ጄኔራል ከሥልጣን ተወግዱ።ግን አላረፉም።በጠመንጃ ይዘዉ በጠመንጃ የተቀሙትን የመሪነት ሥልጣን በምርጫ መልሰዉ ለመያዝ እንደባተሉ ነበር።ዘንድሮ ተሳካላቸዉ።

Nigeria Goodluck Jonathan Abdulsalami Abubakar Muhammadu Buhari
ምስል DW/Ubale Musa

«ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል።ለናጀሪያዉያን ተደስተናል፤ በናይጄሪያ ዴሞክራሲ ተደሰተናል፤ ሥለወደፊቱ ኑሯችን ተደስተናል።በኛ እምነት ናይጄሪያን ዳግም ለመገንባት አዲስ መሠረት ተጣለ።የጄኔራል ቡኻሪ አመራር ናጄሪያዉያንን ዳግም አንድ ያደርጋል፤ ናይጄሪያ ዳግም እንድትገነባ ዕድል ይሰጣል የሚል ተስፋ አለን።»

ከደጋፊዎቻቸዉ አንዱ።የ72 ዓመቱ ጡረተኛ ጄኔራል ካሮጌዉ ቤተ-በመንግሥት ሌጎስ ሳይሆን ከአቡጃዉ አዲስ ቤተ-መንግሥት በቅርቡ ይገባሉ።የምርጫዉ ዉጤት ከተነገረበት ከትናት አመሻሽ ጀምሮ አደባባይ የወጣዉ ደጋፊያቸዉ ዛሬም በድሉ ፌስታ ሲፈንድቅ ነዉ-የዋለዉ።

ከዉጪም ከዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እስከ ጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቫልተር ሽታይን ማየር፤ ከአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ድላሚኒ ዙማ እስከ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀፊ ፓን ጊ ሙን-ያሉ የሐገራትና የድርጅቶች መሪዎችና ዲፕሎማቶች ለቡኸሪ የሚያሰተላልፉት የደስታ መልዕክት እንቀጠለ ነዉ።

ቀዳሚዉ እና ዋናዉ መልዕክት የተሰማዉ ግን በምርጫዉ ከተሸነፉት ከፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታን ነዉ።

«ይሕቺን ሐገር እንደመራ ለተሰጠኝ ታላቅ እድል ናይጄሪያዉያንን በሙሉ አመሰግናለሁ።የሥልጣን ዘመኔ እስኪያቃ ድረስም እንደ ሐገር መሪ የሚቻለኝን ሁሉ እንደምጥር አረጋግጣለሁ።የግል መልካም ምኞቴን ለጄኔራል መሀመዱ ቡኻሪ አስተላልፌያለሁ።»

ናይጄሪያ መቶ ዓመት ከዘለቀዉ የብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ በ1960 ነፃ ከወጣችበት-እስከ 1999 (እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ ዘመን) ከተቆጠሩት አርባ ዓመታት አብዛኛዉን ያሳለፈችዉ በመፈንቅለ መንግሥት ፤ በርስ በርስ ዉጊያና ግጭት ነዉ።በ1999 ከምርጫ ዴሞክራሲ ጋር ተዋዉቃለች።

Nigeria Präsident Goodluck Ebele Jonathan
ምስል imago/Wolf P. Prange

ይሁንና እስከ ቅዳሜዉ ምርጫ ድረስ PDP ከተሰኘዉ የፖለቲካ ማሕበር ሌላ ሌላ ፓርቲ ሥልጣን ይዞባት አያዉቅም።በሥልጣን ላይ ያለ ፕሬዝዳንት በተቃዋሚ ፓርቲ ተቀናቃኙ ሲሸነፍና ሽንፈቱን በፀጋ ሲቀበል ጆናታን የመጀመሪያዉ ናቸዉ።በዚሕም ምክንያት ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች እንደተስማሙበት የቅዳሜዉ ምርጫ ቡኸሪን ለሥልጣን ማብቃቱ ከማሰገረሙ ይልቅ ጆናታን ሽንፈታቸዉን መቀበላቸዉ የዚያችን ሐገር ፖለቲከኞች ብስለት፤ አርቆ አሳቢነት፤ለሐገርና ለሕዝብ ተቆርቋሪነትን መስካሪ ነዉ።

የሰባ ሁለት ዓመቱ አዛዉንት ካዲሱ ቤተ-መንግሥት ሲገቡ ነባሩ የናይጄሪያ ዉስብስብ ችግሮች አፍጥጦ ይጠብቃቸዋል።ጊጋ የተሰኘዉ የጀርመን ጥናት ተቋም ባልደረባ ሮበርት ካፔል እንደሚሉት ከብዙዎቹ ችግሮች ሁለቱ የቡኻሪን አፋጣኝ መፍትሄ ይሻሉ።የቦኮ ሐራም ሽብርና ሙስና።

«በቦኮ ሐራም ላይ የተጀመረዉን ዘመቻ በወታደራዊ ሐይል ብቻ ሳይሆን በድርድሩም መስክ መፍትሔ ለማግኘት መጣርና መምራት ይጠበቅባቸዋል።ሁለተኛዉ ባሁኑ ፕሬዝዳንት በጆናታን ዘመን አለቅጥ የተንሰራፋዉን ሙስናን ለማቃለል አበክረዉ መጣር አለባቸዉ።»

በሕዝብ ብዛት ከአፍሪቃ አንደኛ ናት።173 ሚሊዮን።በነዳጅ ዘይት ሐብትም ከአፍሪቃ አንደኛ ናት።ጠንካራ አሸባሪ ቡድንንን በማፍራት ሶማሊያን አስቀድማ ትከተላለች።በሙስና ከአፍሪቃ የሚስተካከላት የለም።አሁን ደግሞ በዲሞክራሲያዉ የሥልጣን ሽግግር ከጥቂት የአፍሪቃ ሐገራት አንዷ ሆነች።ናይጄሪያ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ

 

 

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ