1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶርያ ስደተኞች መርጃ ዓለማቀፍ ጉባኤ በበርሊን

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 18 2007

የሶርያዉ ደም አፋሳሽ የርስ በርስ ጦርነት አራት ዓመት ሆነዉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሶርያዉያን ጦርነቱን በመሸሽ ሀገር ቀያቸዉ ጥለዉ ተሰደዋል። ፖለቲከኞችና የርዳታ ድርጅቶች የዓለም ዓቀፍን ድጋፍ እየጠየቁ ነዉ። ዛሬ የ 40 ሀገራት መንግሥታትና ዓለማቀፍ ድርጅቶች የሶርያን ስደተኞች በተመለከተ ጉባኤ አድርገዋል።

https://p.dw.com/p/1DdQR
Syrien Konferenz Flüchtlinge Berlin Deutschland
ምስል Reuters/Hannibal

በመካከለኛዉ ምስራቅ ዉጥረት በሰፈነባቸዉ ሀገራት ነዋሪዎች በመሰደድ ላይ ይገኛሉ። እንደ ተመድ የስደተኞች መርጃ ድርጅት UNHCR የሶርያ የርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ከሶስት ሚሊዮን በላይ ሶርያዉያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ለስደት ተዳርገዋል። ከዚህ ሌላ በሀገሪቷ ባለዉ ዉጥረት ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉና ወደ ሌላ የሶርያ አካባቢ የሸሹ ነዋሪዎች ከ 6,5 ሚሊዮን በላይ ናቸዉ። የዚህ ገፈት ቀማሽ ህዝብ መካከል ደግሞ ከስድስት ሚሊዮን በላዩ ህፃናት ናቸዉ። የጀርመኑ የልማት ትብብር ሚኒስትር ጌርድ ሙለር ሁኔታዉን አደገኛ ብለዉታል። ይህ አሳሳቢና አደገኛ ጉዳይ የሚፈታዉ እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራዉ አሸባሪ ቡድንን በማባረር መሆኑን ሳይናገሩ አላለፉም። እስከ ቅርብ ግዝያት ድረስ ለሶርያን ስደተኞች መጠለያ ትሰጥ የነበረዉ ኢራቅም ብትሆን ነዋሪዎችዋ በዚሁ ችግር ምክንያት በመሰደድ ላይ ናቸዉ።

Frank-Walter Steinmeier im Libanon
ምስል Reuters

ስደተኛዉ ተጠልሎ በሚገኝበት አካባቢ የዝናብ ወራት ጀምሮአል፤ የክረምቱ ወራት ቅዝቃዜም እየመጣ በመሆኑ ምናልባት ብዙ ሰዎች ለሞት አደጋ እንደሚጋለጡ የጀርመኑ የልማት ትብብር ሚኒስትር ጌርድ ሙለር ተናግረዋል። በሰሜናዊ ኢራቅ እና በቱርክ የሚገኙ ስደተኞች ገሚሱ የሚኖረዉ በፓርኮችና በየአዉራ ጎዳናዉ ጣርያ በሌለዉ መጠለያ ላይ መሆኑ ተመልክቶአል። በስደተኞች መጠለያ ጣብያ የሚገኝ ህጻን እንዲሁም ማንኛዉም ተገን ጠያቂ በብርድ ሊቆራመት አልያም ሊራብ አይገባም ያሉት የጀርመኑ የልማት ትብብር ሚኒስትር ጌርድ ሙለር ፤ ሀገራቸዉ ለስደተኞች መርጃ የሚሆን በቀጣይ 100 ሚሊዮን ይሮ እንደምትሰጥ ቃል ገብተዋል። ጀርመን ለሶርያ መርጃ ከጎርጎረሳዊዉ 2012 ዓ,ም ጀምሮ 632 ሚሊዮን ይሮ ረድታለች። የጀርመኑ የልማት ትብብር ሚኒስትር ጌርድ ሙለር የሶርያ ስደተኞች መጭዉን የክረምት ወራት የሚወጡበት መርጃ አንድ ቢሊዮን ይሮ አዉሮጳ ማቅረብ አለበት ሲሉ ተናግረዋል። ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለተጎጂዎች ጠንካራ እገዛና ትብብርን ማድረግ ይኖርበታል ያሉት የጀርመኑ የልማት ትብብር ሚኒስትር በርካታ የስደተኞች መቀበያ ጣብያ ለተመቻቸ ሁኔታ ዝግጅት እንዳልተደረገበት ተናግረዋል።

« ይህ ጉዳይ የየዕለት ርዕሳችን ሊሆን ይገባል። እኛ አዉሮጳ ሃገራትና ዩናይትድ ስቴትስ እዚህ ቦታ ላይ በጥንካሪ እገዛና ድጋፍ ካላደረግን ስደተኛዉ በከፍተኛ ቁጥር ወደዚህ ወደ አዉሮጳ ወደ ጀርመን ወደ ፈረንሳይ ይፈልሳል። ስለዚህም የሰዎቹ ህልዉና እንዲረጋገጥ ማድረግ ይኖርብናል። በተጨማሪም የወጣቶችና የህፃናቱን መፃኤ ዕድል ማረጋገጥ ይኖርብናል »

Zaatari Flüchtlingslager in Jordanien
ምስል Guy Degen

የሶርያ ስደተኞችን ለመርዳት የ 40 ሀገራት የመንግሥትና የዓለማቀፍ ድርጅት ተወካዮች ዛሬ ማክሰኞ በርሊን ላይ ተቀምጠዋል። በዚህ ጉባኤ የጀርመኑ የልማት ትብብር ሚኒስትር ጌርድ ሙለር እና የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር ተጋባዥ ናቸዉ። በተባበሩት መንግሥታት የመካከለኛዉ ምስራቅ የአካባቢ የህጻናት መርጃ ድርጅት ተጠሪ ማርያ ካልቪስ ጀርመን ይህን ጉባኤ በማዘጋጀትዋ በማመስገን በሶርያ እና አካባቢዉ የሚታየዉ ችግር በአፋጣኝ እንዲፈታና ለርዳታ እዲበቃ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል። በሶርያዉ የርስ በርስ ጦርነት በድህነት በመማቀቅ ተስፋ አጥተዉ የሚገኙት ስደተኞቹ ብቻ ሳይሆኑ ስደተኞቹን የሚቀበሉ በተለይም በጎረቤት ሀገሮች ማለትም ቱርክ እና ዮርዳኖስ ጭምር መሆናቸዉ ተመልክቶአል። ስደተኞችን የተቀበሉ ሀገሮች በአሁኑ ሰዓት ችግር ላይ የወደቁም እንዳሉ ተገልፆአል ። ለምሳሌ በሊባኖስ በባካታል የስደተኞች መጠለያ ጣብያ የመጠጥ ዉኃ እጥረት ይታያል። በዮርዳኖስ ስደተኞችን የተቀበሉ ቤተሰቦች የያዙትን የመተዳደርያ ገንዘብ እየጨረሱ ነዉ። ይህ ጉዳይ የትዉልድ ቦታቸዉን ጥለዉ ለተሰደዱትና በተለይ ምንም ተስፋ ለማይታየቸዉ ህጻናት አስከፊ ሁኔታን ደቅኖ ይታያል። በተባበሩት መንግሥታት የመካከለኛዉ ምስራቅ የአካባቢ የህጻናት መርጃ ድርጅት ተጠሪ ማርያ ካልቪስ እንደሚሉት ፤

« 50 በመቶ ተጎጅዎች ህፃናት ናቸዉ። በወግ አጥባቂ ሃሳብ ማለትም ሰፋ ባለዉ ግምቴ 5,7 ሚሊዮን ህጻናት በዚህ ቀዉስ ለስደት ተዳርገዋል» እንደ ማርያ ካልቪስ በተመድ «UNHCR» በሊባኖስ በሚገኘዉ የስደተኞች ጣብያ በትምህርት ቁሳቁሶች የተሞሉ 70,000 የትምህርት ቤት ቦርሳዎችን አድሎአል። በዮርዳኖስም 120,000 የሶርያ ህፃናት በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ።

Flüchtlinge im Grenzgebiet zwischen der Türkei und Syrien
ምስል DW/J. Hahn

የበርሊኑ የሶርያ የስደተኞች ጉዳይ ጉባኤ ለሶርያ ስደተኞች መርጃ ማሰባሰብያ ብቻ ሆኖ እንዲታይ ሳይሆን አንድ ፖለቲካዊ ምልክትንና ርምጃን ያስገኛል የሚል ተስፋ አለኝ ሲሉ የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ዛሬ በርሊን ላይ በተካሄደዉ በሶርያዉ ስደተኞች ዓለማቀፍ መርጃ ጉባኤ ላይ ለመካፈል የመጡትን የሊባኖሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ታማም ሳላም ትናንት ምሽት በጽህፈት ቤታቸዉ ተቀብለዉ ባነጋገሩዋቸዉ ግዜ ገልፀዋል። « በሶርያ በሚታየዉ ችግር ምክንያት በሊባኖስ ለተከሰተዉ ችግር መፍትሄ ከሊባኖስ ጋር በአጋርነት እንቆማለን። አራት ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባት ሀገር ሊባኖስ በአሁኑ ወቅት አንድ ሚሊዮን ተገንጠያቂዎች ተመዝግበዋል።በእዉነቱ እዚህ ላይ ስላልተመዘገቡት ስደተኞች ቁጥር መናገር የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ለብዙ ዓመታት በሊባኖስ የፍልስጤም ስደተኞች ሁኔታ ያስከተለዉን ከፍተኛ ዉጣዉረድ እና ችግር ምን ያህል እንደሆን እኛ ጀርመን የምንገኝ መገመት ያዳግተናል። በዚህም ምክ ንያት ሊባኖስ የኛን የአጋርነት ድጋፍ ታገኛለች»

የሊባኖሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ታማም በበኩላቸዉ የጀርመንን አጋርነትና ፍላጎት በማመስገን የጉባኤዉን ዓላማ ለሀገራቸዉ ጥሩ ጠቀሚታን እንደሚያመጣ ገልፀዋል። ጀርመን በአሁኑ ወቅት ለሶርያን ስደተኞች መጠለያ ለመገንባት በብዙ መንገዶች በመሳተፍ ላይ ትገኛለች። ከጀርመን ለሶርያ የሚወጣዉ የርዳታ ገንዘብ በአዉሮጳ ሕብረትና በተመ የርዳታ ድርጅት በኩል በሁለት መንገድ እንደሚደርስም ተገልፆአል።

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ