1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 18 2007

ኢትዮጵያውያን በዱባይ ማራቶን ከ1ኛ እስከ 10ኛ በመግባት እጅግ አመርቂ ድል አስመዝግዋል፣ የብር ሽልማትም አግኝተዋል። በዓለም አቀፍ የቢስክሌት ውድድር ኢትዮጵያዊው አበረታች ውጤት አምጥቷል። የዓለማችን ኮከብ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። በኤፍ ኤ ካፕ ውድድር ቸልሲና ማንቸስተር ሲቲን ጨምሮ ኃያላኑ በትንንሾቹ ጉድ ሆነዋል።

https://p.dw.com/p/1EQlS
Mali gegen Elfenbeinküste African Cup of Nations 2015
ምስል I.Sanogo/AFP/Getty Images

ኢትዮጵያውያን ዓርብ እለት በተከናወነው የዱባይ ማራቶን በወንዶች ከ1ኛ እስከ 10ኛ በተርታ በመግባት ያስመዘገቡት እጅግ አስደናቂ ድል በቀላሉ የሚረሳ አይደለም። በሴቶችም ያሸነፈችው ኢትዮጵያዊት ናት።

የዱባይ የስፖርት ምክር ቤት ሊቀመንበር እና የዱባዩ አልጋ ወራሽ በሆኑት ልዑል ሼክ ሐምዳን ቢን ሞሐመድ የበላይ ጠባቂነት በተሰናዳው የዱባይ ማራቶን ለመወዳደር ወደ መሮጫ ሜዳው የገቡት ከ25,000 በላይ የሚቆጠሩ ተወዳዳሪዎች ነበሩ። ከዚህ ሁሉ ወፈ ሠማይ ተወዳዳሪ ግን ነጥረው በመውጣት የኢትዮጵያን ስም በዓለም ዙሪያ በክብር እንዲጠራ ያስቻሉት ኢትዮጵያውያኑ ተወዳዳሪዎች ናቸው።

በወንዶች ፉክክር 2:05:28 በማስመዝገብ በአንደኛነት ያጠናቀቀው ለሚ ብርሃኑ የ200,000 ዶላር ሽልማት እና የክብር ዋንጫ ከአልጋ ወራሹ እጅ መቀበሉ ተዘግቧል። የ20 ዓመቱ ወጣት ለሚ በውድድሩ አሸናፊ እሆናለሁ ብሎ እንዳልጠበቀ፣ ስለተሸለመው በርካታ ገንዘብም እንዳላሰበበት ተናግሯል። ለሚ በጎርጎሪዮሳዊው 2013 ዓም የዱባይ እና የቦስተን ማራቶኖች አሸናፊ ከነበረው ሌሊሳ ዴሲሳ በ24 ሠከንዶች ቀድሞ ነው አንደኛ የወጣው። በሦስተኛ ደረጃ የገባው ደርብ ሮቢ 2:06:06 ሰከንድ አስመዝግቧል። በውድድሩ እስከዓሥረኛ ለወጡት ተወዳዳሪዎች በሙሉ የገንዘብ ሽልማት የተመደበ ሲሆን፤ በዱባይ ማራቶን የዘንድሮ ውድድር 10ኛ ለወጣ ተወዳዳሪ በወንድም በሴትም የ8 ሺህ ዶላር ሽልማት ተዘጋጅቶ ነበር።

Leichtathletik Hamburg- Marathon
ምስል picture-alliance/dpa

በዚሁ የዱባይ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አሠለፈች መርጊያ 2:20:02 በማስመዝገብ አሸናፊ ሆናለች። የ200 ሺህ ዶላር ተሸላሚም ሆናለች። ኬንያውያቱ ቼርኖ እና ሉሲ ካቡ ኹለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል። ግላዲስ በአሠለፈች የተቀደመችው በአንድ ሠከንድ ነው። ኢትዮጵያዊቷ ሹህሬ ደምሴ ሦስተኛ ከወጣችው ሉሲ 38 ሠከንዶች በመዘግየት በ2:20:59 አራተኛ ወጥታለች። የባህሪኗ ተወዳዳሪ አሊያክሳንድራ 8ኛ ጣልቃ ከመግባቷ በስተቀር ድሉ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያውያቱ ነበር። በዱባይ ማራቶን የዛሬ አራት ዓመት ኢትዮጵያ በወንዶች ሦስተኛ ከመውጣቷ በስተቀር ላለፉት ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያውያን በወንዶችም በሴቶችም የአንደኛ ደረጃቸውን የሚነጥቃቸው አልተገኘም።

ውድድሩን በመላው ዓለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የስፖርት አፍቃሪያን በቴሌቪዥን መስኮቶች ተከታትለውታል። በወቅቱ ውድድሩን በቦታው ላይ ሆነው ሲከታተሉ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እና ወኔም እጅግ የሚበረታታ ነው።

ትናንት ሆንግ ኮንግ ውስጥ በተደረገ የማራቶን ሩጫ ውድድርም ኢትዮጵያዊው ስንታየሁ መርጋ እጅጉ አንደኛ በመውጣት የ65,00 ዶላር ተሸላሚ ለመሆን ችሏል። ስንታየሁ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት 2:13:00 ሠከንድ ነው። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ፍቅሬ አሠፋ ኹለተኛ ወጥቷል። ኬኒያዊው ሮበርት ኪፕኮሪ ሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል።

እግር ኳስ

በአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታዎች እምብዛም ግምት ያልተሰጣት አዘጋጇ ኢኳቶሪያል ጊኒ ሦስተኛ ጨዋታዋን ትናንት ከጋቦን ጋር አድርጋ 2 ለ1 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜ ለማለፍ ችላለች። 7 ነጥብ ያለው የኮንጎ ቡድን አዘጋጇን በኹለት ነጥብ በመብለጥ የምድቡ ቀዳሚ ሆኗል። ኮንጎ ትናንት ቡርኪናፋሶን 2 ለ1 አሸንፏል። የዛሬው ጨዋታ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከቱኒዚያ እንዲሁም ኬፕቬርዴ ከዛምቢያ የሚያደርጉት ነው።

ኢኳቶሪያል ጊኒ ጋቦን ላይ አግብተው
ኢኳቶሪያል ጊኒ ጋቦን ላይ አግብተውምስል C.de Souza/AFP/Getty Images

ከ10 ቀናት በፊት ወደ ሣዑዲ አረቢያ በማቅናት የአቋም መለኪያ ያደረገው የጀርመኑ ኃያል ባየር ሙይንሽን ቡድን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አስመልክቶ ምንም ያለው ነገር የለም የሚል ትችት ቀርቦበታል። «ተጨዋቾች፣ ተፋላሚዎች እና ባለገድሎች፤ አይሁዳውያን በጀርመን እና በባየር ሙይንሽን የእግር ኳስ ቡድን ውስጥ» በሚል ርእስ የተዘጋጀውን አውደ ርእይ የከፈቱት ሥራ አስኪያጁ ካርል ኃይንስ የሚከተለውን መናገራቸው ነበር የሳዑዲ አረቢያው ጉዞ በድጋሚ እንዲነሳ ያደረገው።

«እንደሚመስለኝ ስፖርት በማኅበረሰባዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የራሱ ኃላፊነት አለበት። እናም በተገኘው አጋጣሚ ስፖርት ድምጹን ቢያሰማ መልካም ነው።»

አውደ ርእዩን ከባየር ሙይንሽኑ ሥራ አስኪያጅ ጋር በአንድነት የከፈቱት በሙይንሽን እና ኦበርባየርን የእስራኤል የባህል ማኅበረሰብ ፕሬዚዳንቲት ቻርሎቴ ክኖብሎኅ በበኩላቸው በዘወርዋራ ትችታቸውን ሰንዝረዋል። ባየር ሙይንሽኖች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈፀምባታል ወሚባልባት ሳኡዲ ዓረቢያ ከመሄዳቸው አስቀድሞ ማድረግ የነበረባቸውን እንዲህ ተናግረዋል።

የባየር ሙይንሽኑ ካርል ኃይንስ ሮሜኒጋ
የባየር ሙይንሽኑ ካርል ኃይንስ ሮሜኒጋምስል Alexander Hassenstein/Bongarts/Getty Images

«በሌላ መልኩ ግን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ አስቀድሞ አፅንዖት መስጠት ይገባ ነበር። ያ አልሆነም። ግን ደግሞ ለወዳጃችን ትንሽ የማንቂያ ማስታወሻ ብጤ ማስተላለፍም ይቻላል።»

ባየር ሙይንሽን ሰብዓዊ መብት ጥሰት ወደሚፈጸምባት ሀገር በማቅናቱ ከሳዑዲ ዓረቢያ 2 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል የሚል ዘገባም ወጥቷል። እናም ወደፊት ምናልባት የጀርመን ቡድኖች መሰል ስህተት ላለመሥራት መጠንቀቅ ይገባቸዋል የሚል ትችትም ከጋዜጠኞች ተሰንዝሯል።

በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ጨዋታዎች ከአርሰናል በስተቀር ዋነኞቹ ተፎካካሪዎች በዝቅተኞቹ ተረትተዋል። አርሰናል ብሪቶን አልቢኖን ትናንት 3 ለ2 አሸንፏል። ከትናንት በስትያ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ቸልሲም ሆነ ተከታዩ ማንቸስተር ሲቲ ከፕሪሚየር ሊጉ ውጪ ላሉ ቡድኖች እጅ ሰጥተዋል። ጨዋታውን 2 ለባዶ ሲመራ የነበረው ቸልሲ በብራድፎርድ ሲቲ ነው 4 ለ2 በመሸነፍ እንደማይሆን የሆነው። ማንቸስተር ሲቲም አልቀረለትም። በሚድልስብሩ 2 ለ ምንም ጉድ ሆኗል። ሊቨርፑል ከትናንት በስትያ ከቦልተን ወንደረርስ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል። ቀደም ብሎ ማንቸስተር ዩናይትድ ከካምብሪጅ ዩናይትድ ጋር እንደሊቨርፑል ግብ ሳያስቆጥር ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ቀይ ካገኘ በኋላ
ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ቀይ ካገኘ በኋላምስል picture-alliance/dpa/R.Alcaide

በስፔን ላሊጋ ትናንት ቫሌንሺያ ሴቪላን 3 ለ1 በመርታት በደረጃ ሠንጠረዡ አራተኛ ለመሆን ችሏል። ሴቪላ በኹለት ነጥብ ዝቅ ብሎ 39 ነጥብ በመያዝ አምስተኛ ለመሆን ተገዷል። አትሌቲኮ ቢልባዎ ከማላጋ አንድ እኩል፣ ዴፖርቲቮ ላ ኮሩኛ ከግራናዳ 2 እኩል ተለያይተዋል። አልሜሪያ በኢስፓኞላ የ3 ለዜሮ ሽንፈትን ቀምሷል። ከትናንት በስትያ መሪው ሪያል ማድሪድ ኮርዶባን 2 ለ1 በማሸነፍ ነጥቡን 48 አድርሷል። በእለቱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የተቀናቃን ተጨዋቹን በመርገጡ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ በስፔን ላሊጋ ግጥሚያ ለ7ና ጊዜ 30ኛ ግብ በማስቆጠር ታሪክ ሰርቷል። ኤልሼን 6 ለዜሮ ያንኮታኮተው ባርሴሎና ከሪያል ማድሪድ በአንድ ነጥብ ነው ልዩነቱ።

በጣሊያን ሴሪኣ ትናንት ጁቬንቱስ ቺዬቮ ቬሮናን 2 ለባዶ አሰናብቷል። ሮማ አንድ ግብ በማስቆጠር ከፍሎሬንስ ጋር አቻ ወጥቷል። ፓሌርሞ እና ሳምፕዶሪያም እንደነ ፍሎሬንስ በተመሳሳይ ውጤት ነጥብ ተጋርተዋል። ከትናንት በስትያ ላትሲዮ በሚላን 3 ለ1 ተቀጥቷል።

ብስክሌት

ኢትዮጵያዊው የብስክሌት እሽቅድምድም ተፎካካሪ ጽጋቡ ግርማይ ትናንት አውስትራሊያ ውስጥ በተከናወነው የRoad tour under የብስክሌት ውድድር አጠቃላይ ነጥብ የ11ኛ ደረጃን ለመያዝ ችሏል። ጽጋቡ ለጣሊያኑ ላምፕሬ ቡድን ተሰልፎ እስካሁን ያስመዘገባቸው ነጥቦች ተደምረው ነው ከምርጥ 30 ተወዳዳሪዎች መካከል ሊመደብ የቻለው በትናንቱ የመጨረሻ ውድድር ያስመዘገበው ነጥብ 29ኛ ነው። ጽጋቡ የሚወዳደርበት ላምፕሬ ቡድን የግንባታ ቁሳቁስ አምራች የጣሊያን ኩባንያ ሲሆን፤ ወደ ዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር መድረኮች ብቅ ካለ 25 ዓመታትን ማስቆጠሩ ይታወቃል።

Giro d'Italia Etappe 20 Gewinner Vincenzo Nibali
ምስል picture-alliance/dpa

ሰሞኑን በተከናወኑ የዝውውር ዜናዎች የ16 ዓመቱ የኖርዌይ የመሀል አጥቂ ማርቲን ኦዴጋርድ በ2,80 ሚሊዮን ዩሮ ከኖርዌዩ ሽትሮምስጎድ ሴትቡድን ወደ ሪያል ማድሪድ ተዛውሯል። በሌላ የዝውውር ዜና የብራዚሉ አማካይ ሉቃስ ሲልቫ ለሪያል ማድሪድ በመፈረሙ የተሰማውን ደስታ ዛሬ ገልጧል። የ21 ዓመቱ አጥቂ ከብራዚሉ ክሩዜሮ ቡድን ለሪያል ማድሪድ የፈረመው በ14 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ መሆኑም ተሰምቷል። በሪያል ማድሪድም ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ይቆያል ተብሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ