1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ፤ ግንቦት 17 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

ማንተጋፍቶት ስለሺሰኞ፣ ግንቦት 17 2007

በአውሮጳ ሲከናወኑ የነበሩ የዘንድሮ ታላላቅ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች በአብዛኛው በሣምንቱ ማሣረጊያ ተጠናቀዋል። ማን ተሰናበተ፣ የትኛውስ ቡድን ድል ቀናው?በአትሌቲክሱ ዘርፍ ኢትዮጵያ በወንድም በሴትም ትናንት ድል ቀንቷታል። በማራቶን የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ ካናዳ ውስጥ በወንድም በሴትም ማን በግሮን ብለዋል።

https://p.dw.com/p/1FWHR
Meisterfeier 1. FC Bayern München Rathaus
ምስል picture-alliance/dpa/M. Müller

የስፖርት ዘገባ፤ ግንቦት 17 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

ኦታዋ ካንዳ ውስጥ ትናንት በተከናወነ የማራቶን የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አበሩ መኩሪያ ውድድሩን በ2:25:30 በማጠናቀቅ አንደኛ ወጥታለች። አበሩ ውድድሩን ያጠናቀቀችበት የትናንትናው ሰአት በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር የ"silvere label" የጎዳና ውድድር ታሪክ ኹለተኛው ፈጣኑ ሰአት ተብሎ ተመዝግቦላታል። በእሁዱ የኦታዋ የማራቶን ሩጫ የወንዶች ፉክክርም አሸናፊ የሆነው ኢትዮጵያዊው ግርማይ ብርሐኑ በ2:08:14 በመግባት አንደኛ ኾኗል። ኦታዋ ካናዳ ውስጥ በወንዶችም በሴቶችም የተከናወኑ የማራቶን የሩጫ ውድድሮችን ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በመደዳ ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ናት።

የጀርመን ቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ግጥሚያ የዘንድሮ ውድድር ቅዳሜ እለት ተጠናቋል። ቀደም ሲል ዋንጫውን በእጁ ማስገባቱን ያረጋገጠው ባየር ሙይንሽን ውድድሩን በአንደኛነት ያጠናቀቀው በአጠቃላይ 79 ነጥብ በመሰብሰብ ነው። ባየር ሙይንሽን ከትናንት በስትያ ማይንትስን 2 ለባዶ አሸንፏል። ከኮሎኝ ቡድን ጋር 2 እኩል የተለያየው ቮልፍስቡርግ ባየር ሙይንሽንን ተከትሎ በቀጥታ ለሻምፒዮንስ ሊግ የቀጣይ ዙር አልፏል። በአውስቡርግ 3 ለ1 የተቀጣው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በደረጃ ሠንጠረዡ ሦስተኛ ሆኖ በማጠናቀቁ እና የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ በመሆኑ ተፅናንቷል። አራተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ባየር ሌቨርኩሰን ለሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ጨዋታ መግባቱን አረጋግጧል።

ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቬርደር ብሬመንን 3 ለ 2 ረትቷል፤ በደረጃ ሠንጠረዡ ግን 7ኛ ሆኖ በማጠናቀቁ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን በአውሮጳ ታላላቅ ግጥሚያዎች ላይ ተሳታፊ አይሆንም። በአውሮጳ ታላላቅ ግጥሚያዎች ላይ ለመሳተፍ በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ቢያንስ ስድስተኛ ሆኖ መጨረስ ያስፈልጋል። 48 ነጥብ በመሰብሰብ ስድስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ሻልከ በአንድ ነጥብ ከሚበልጠው አውስቡርግ ጋር ወደፊት ለአውሮጳ ሊግ ውድድር ማጣሪያ ማለፉን አረጋግጧል።

ባለፈው ሣምንት ከዜሮ ተነስቶ ሐምቡርግን 2 ለ1 በማሸነፍ ከተሰናባች ወደ ወራጅ ቃጣናው 16ኛ ደረጃ ከፍ ብሎ የነበረው ሽቱትጋርት ቅዳሜ እለት እድለ-ቢሱ ፓደርቦርንን 2 ለ1 ሸኝቶ ከቡንደስ ሊጋው ከመሰናበት ስጋት ሙሉ ለሙሉ ነፃ ኾኗል።

ለዘንድሮው ውድድር ከታችኛው ዲቪዚዮን ወደ ቡንደስ ሊጋው ብቅ ብሎ የነበረው ፓደርቦርን በቡንደስ ሊጋው ለመቆየት ከባለፈው ሣምንት ጀምሮ ጭልጭል ትል የነበረችው እጅግ ደብዛዛ ተስፋ ይዞ ከትናንት በስትያ ወደ ሜዳ ቢገባም ድርግም ብላ ጠፍታበታለች። ፓደርቦርን የትናንቱን ጨዋታ የግድ አሸንፎ የሐምቡርግን ሽንፈት መናፈቅ ብቻ አይደለም መማፀን ነበረበት። ናፍቆቱም ሆነ ተማጽኖው ግን አልሰመረም። በቡንደስ ሊጋው የመጨረሻ 18ኛ ሆኖ በማጠናቀቁ ከቡንደስሊጋው የመሰናበትን መራራ ጽዋ ባይወድም በግድ ጨልጦ በመጣበት እግሩ ወደ ታችኛው ኹለተኛ ዲቪዚዮን ተመልሷል። 17ኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ፍራይቡርግ በሐኖቨር 2 ለ1 ተቀጥቷል። የፓዴርቦርንን እግር ተከትሎ ቡንደስ ሊጋ ደኽና ሠንብች ብሏል።

ባለፈው ሣምንት ከመጨረሻ ጠርዝ ፓደርቦርንን ብቻ በልጦ በ17ኛ ደረጃ ከቡንደስ ሊጋው የመሰናበት ሰቀቀን ውስጥ የነበረው የሰሜን ጀርመኑ ሐምቡርግ ከሰቀቀኑ ተርፏል። የሞት ሽረት ብሎ ወደ ሜዳ የገባው ሐምቡርግ ሻልከን 2 ለ0 ድል በመንሳቱ በቀጥታ ከቡንደስ ሊጋው ባይሰናበትም ከስጋት ግን አልዳነም። ሐምቡርግ በቀጣዩ የቡንደስ ሊጋ የውድድር ዘመን ተሳታፊ ለመሆን ከታችኛው ዲቪዚዮን ሦስተኛ ሆኖ ካጠናቀቀው ኬ ኤስ ሲ ቡድን ጋር መጋጠም ይጠበቅበታል። ያም ብቻ አይደለም ማሸነፍ ይኖርበታል። ያኔ በቡንደስ ሊጋው ቆይታው ይረጋገጥለታል።

ከኹለተኛ ዲቪዚዮን አንደኛ እና ኹለተኛ ሆነው በማጠናቀቅ በቡንደስ ሊጋው ቀጣይ የውድድር ዘመን የመሳተፍን ክብር የተጎናፀፉት ዳርምስታት እና ካርልስሩኀ የፍራይቡርግ እና ፓደርቦርንን ቦታ ተረክበዋል።

የአይንትራኅት ፍራክንፉርቱ አሌክሳንደር ማየር በ19 ግቦች ኮከብ ግብ አግቢ ሆኗል። የባየር ሙይንሽኖቹ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ እና አሪየን ሮበን 17 ከመረብ ያረፉ ኳሶች አሏቸው። ኹለተኛ ኮከብ ግብ አግቢ ሆነው አጠናቀዋል። በተለይ ሆላንዳዊው አሪየን ሮበን ጉዳት ባይደርስበት ኖሮ ምናልባት የኮከብ ግብ አግቢነቱ ደረጃ ለውጥ ሊኖረው ይችል ነበር። የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ፒየር ኤሜሪክ እና የቮልፍስቡርጉ ባስ ዶስት 16 አግብተው በጋራ ሦስተኛ ለመሆን ችለዋል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ቸልሲ ትናንት ሠንደርላንድን 3 ለ1 በመቅጣት የውድድር ዘመኑን በድል ቋጭቷል። የትናንቱን 3 ነጥብ ደምሮ ቸልሲ በአጠቃላይ 87 ነጥብ ሰብስቦ ነው የውድድር ዘመኑን የተጠናቀቀው። ቸልሲ ከፕሬሚየር ሊግ የዋንጫ ድል ባሻገር በቀጣዩ ዘመን የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር አላፊ መሆኑ የደጋፊዎቹ ደስታ እጥፍ ድርብ ሆኖ እንዲቆይ አስችሏል።

በ79 ነጥብ ኹለተኛ ሆኖ የጨረሰው ማንቸስተር ሲቲ ትናንት ሣውዝሐምፕተንን 2 ለምንም አሸንፏል። በፕሪሚየር ሊጉ ሦስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው አርሰናልን ይዞ ቸልሲን በመከተል ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ያቀናል። አርሰናል ትናንት በመጨረሻው የፕሬሚየር ሊግ ውድድር ዌስት ብሮሚች አልቢኖን 4 ለ1 ድባቅ መቷል። ከዚህ ቀደም ተገናኝተው አርሰናል 4 ለባዶ ማሸነፉ ይታወሳል። በትናንቱ ግጥሚያ ቲዎ ዋልኮት ሔትሪክ ሠርቷል። በውድድር ዘመኑ ፍፃሜ አርሰናል ከማንቸስተር ሲቲ የተበለጠው በ4 ነጥብ ነው። ቸልሲ ግን በ12 ነጥብ ርቆት ነው ያጠናቀቀው።

ከሑል ሲቲ ጋር ትናንት በድጋሚ ተገናኝቶ በተመሰሳሳይ ያለምንም ግብ በመለያየት ይቶ ነጥብ የተጋራው ማንቸስተር ዩናይትድ ለሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር በቀጥታ ባያልፍም ማጣሪያው ውስጥ መግባት ግን ችሏል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን አጓጉል ሽንፈቶችን ሲያስተናግድ የከረመው ሊቨርፑል ትናንት በስቶክ ሲቲ ውርደትን ተከናንቧል። ከዚህ ቀደም 5 ለዜሮ የቀጣውን ቡድን ለመበቀል ቋምጦ ወደ ብሪታንያ ስታዲየም ያቀናው ሊቨርፑል ዳግም የ6 ለ 1 የውርደት ካባ ሲደረብለት ከ27 ሺህ በላይ ታዳሚዎች ስታዲየም ተገኝተው ታዝበዋል። ሊቨርፑል አምስተኛ ሆኖ ካጠናቀቀው ቶትንሐም ሆትስፐር ጋር ለአውሮጳ ሊግ መሳተፍ መቻሉ በእርግጥ መፅናኛ ሳይሆንለት አልቀረም። ሊቨርፑል ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ሽቴፋን ዤራርድ ነው።

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የዘንድሮ ኮከብ ግብ አግቢ የማንቸስተር ሲቲው ሠርጂዮ አጉዌሮ ሆኗል። 26 ከመረብ ያረፉ ኳሶች አሉት። የቶትንሐም ሆትስፐሩ ሐሪ ኬን በ21 ግቦች ተከትሎታል። የቸልሲው ዲዬጎ ኮስታ በ20 ግቦች ሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል።

በስፔን ላሊጋ የዋንጫ ባለድሉ ባርሴሎና ቅዳሜ ዕለት ከዲፖርቲቮ ላኮሩና ጋር ኹለት እኩል በመለያየት ያገኛት አንድ ነጥብን ደምሮ በ94 ነጥብ ውድድሩን አጠናቋል። ሪያል ማድሪድ ጌታፌን 7 ለ3 በሆነ ሰፊ ልዩነት በመርታት በ92 ነጥብ ጨርሷል። አትሌቲኮ ማድሪድ ከግራናዳ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል። በ78 ነጥብ ሦስተኛ ሆኖ ከእነ ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ጋር ለሻምፒዮንስ ሊግ ማለፉን አረጋግጧል። ቫለንሺያ በሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ በማጣሪያው ይወዳደራል።

የጣሊያን ሴሪኣ የመጨረሻ ዙር ውድድር የሚከናወነው የፊታችን እሁድ ነው። ጁቬንቱስ የዋንጫውም የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድርም አላፊ መሆኑን ካረጋገጠ ሰነባብቷል። 70 ነጥብ ያለው ሮማ እና በ 4 ነጥብ ዝቅ ብሎ የሚከተለው ላትሲዮ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነት ቦታቸውን ለማስጠበቅ ይፋለማሉ። ሮማ ከፓሌርሞ፣ ላትሲዮ ከኔፓል ጋር ነው የሚፋለሙት።

በፎርሙላ አንድ የሞናኮ ግራንድ ፕሪ የሚኪና ሽቅድምድም በአጠቃላይ ነጥብ ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ አንደኛ በመሆን አሸንፏል። ሌላኛው ጀርመናዊ ሠባስቲያን ቬትል በኹለተኛነት ሲያጠናቅቅ፣ የብሪታኒያው ሌዊስ ሐሚልተን ሦስተኛ ወጥቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አዲሱ አሠልጣኝ ዮሐንስ ሣኅሌ ለመጀመሪያ ዙር ልምምድ የመረጧቸውን ተጨዋቾች ማንነት ይፋ አድርገዋል። ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነትን ጨምሮ ሠባት ተጨዋቾች አሠልጣኙ ቀድሞ ያሠለጥኑት ከነበረው የደደቢት ቡድን መካተታቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኢሜል በላከው መልእክት አስታውቋል።

በኮሎኝ ከተማ ሊከናወን የታቀደው የኢትዮ ጀርመን የእግር ኳስ ውድድር የቅዳሜ ሣምንት እንደሚጀምር አዘጋጆቹ ጠቅሰዋል። የዝግጅቱ መታሠቢያ በሊቢያ እና በደቡብ አፍሪቃ እንዲሁም በየመን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እንደሚሆን ተገልጧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

የስፔን ላሊጋው ባለድል ባርሴሎና ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ
የስፔን ላሊጋው ባለድል ባርሴሎና ኮከብ ሊዮኔል ሜሲምስል Reuters/A. Comas
የዓeንግሊዝ ፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ቸልሲ
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ቸልሲምስል picture-alliance/empics/Potts
ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከቬርደር ብሬመን ጋር ሲጫወት
ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከቬርደር ብሬመን ጋር ሲጫወትምስል A. Grimm/Bongarts/Getty Images
ከቡንደስሊጋው የተሰናበተው የፓደርቦርን ቡድን እና የሽቱትጋርት ተጨዋቾች
ከቡንደስሊጋው የተሰናበተው የፓደርቦርን ቡድን እና የሽቱትጋርት ተጨዋቾችምስል picture-alliance/dpa/J. Güttler
USA Eugene Oregon Symbolbild Leichtathletik WM 2021
ምስል J. Ferrey/Getty Images

ኂሩት መለሠ