1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስዉሩ ርሃብ ተጠቂዎቹ ቢሊዮኖች

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 22 2006

በጎርጎሪዮሳዊዉ 1990 እና 1992ዓ,ም በቢሊዮን ይገመት የነበረዉ ለምግብ እጥረት የተጋለጠዉ ሕዝብ አሁን ወደ 842 ሚሊዮን ዝቅ ማለቱ አንድ ነገር ነዉ ቢባልም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸዉን ወገኖች አሁን የሚያሳስበዉ የተደበቀ ወይም ስዉር ረሃብ መኖሩ መሆኑን ያመለክታሉ።

https://p.dw.com/p/1Cm1Z
Nordkorea - Kinderbespeisung
ምስል Getty Images

ወደሁለት ቢሊዮን የሚሆነዉ የዓለማችን ሕዝብ ለምግብ እጥረት የተጋለጠ ነዉ። የተመጣጠነ ምግብ በማጣቱም ሰዉነትን የሚገነቡ ጠቃሚ ቫይታሚኖችና ማዕድኖችን ከሚመገበዉ ስለማያገኝ በእነዚህ እጥረት በሚመጡ በሽታዎች የተጋለጠ፤ በሽታ የመከላከል አቅሙም የተዳከመ ይሆናል። «ቴርዴዞም»እና«ቬልትሁንገርሂልፈ» የተሰኙት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥናት እንደሚለዉ፣ ለስዉሩ ረሃብ የተጋለጡት ወገኖች በተለይ ሕንድ፣ ባንግላዴሽ፣ማዕከላዊ እስያ እና በአብዛኛዉ የአፍሪቃ ሃገራት ይገኛሉ። የ«ቬልትሁንገርሂልፈ» ዋና ጸሐፊ ቮልፍጋንግ ያማን ስዉሩ ረሃብ እንደይፋዊዉ ምግብ ማጣት ማለትም ርሃብ አቅም የሚያሳጣ ትልቅ ችግር ነዉ ይላሉ።

Symbolbild Hungernot Afrika
ምስል picture-alliance/dpa

«ምሥራቅና ደቡብ አፍሪቃ የሚገኙ ወገኖች በአብዛኛዉ የሚመገቡት የበቆሎገንፎ ነዉ። ይህን በልተዉ ሊጠግቡ ይችላሉ ነገር ግን ከዚህ አንድ ዓይነት ብቻ ከሆነ ምግብ ለጤናና ህይወታቸዉ አስፈላጊ የሆኑ ቫይታሚኖችንአያገኙም።በተመሳሳይ ሩዝን ብቻ በመመገብ ህይወታቸዉን የሚገፉወ ገኖች የሚገኙበት አካባቢም አለ።ነጩን ሩዝ ለመመገብ ስለሚፈትጉትም በሂደቱ ለሰዉነት የሚጠቅሙት ቫይታሚኖች ይወገዳሉ።»

የተመጣጠነ ምግብ በማጣት በተለይም በቫይታሚን ኤ እጥረት በየዓመቱ ከ300 ሺህ እስከ 700 ሺህ የሚሆኑ ሕፃናት ይሞታሉ። ሌሎች 300 ሺዎቹ ደግሞ ለአይነስዉርነት ተዳርገዋል። ሌሎች ለሰዉነት ጠቃሚ የሆኑ እንደብረትና ፎሊክ አሲድ ያሉ ማዕድኖች እጥረት በርካታ ነፍሰጡር እና የሚያጠቡ እናቶች እንደሚሰቃዩም ባለሙያዎች ያመለክታሉ። በማሕጸን የሚገኙ ሕፃናትም በዚሁ ችግር የሚጋለጡበት ሁኔታ አለ። ይህ ችግርም አንዳንዱ ፅንሱ ጤናማ እንዳይሆን እስከማድረግ ይሄድ ይችላል ጉዳቱ። ቮልፍጋንግ ያማን የብረት፤ ቫይታሚን ኤ እና ዚንክ እንዲሁም፣የአዮዲንእጥረትአዲስየሚወለዱናጨቅላሕፃናትጤናላይከፍተኛተፅዕኖእንደሚያደርግያስረዳሉ፤

Kinder Mangelernährung Karachi Pakistan
ምስል Malcolm Brabant

«የሚያጠቡ እናቶች አብዛኛዉን ጊዜ የብረትና ቫይታሚንኤ እጥረት ያጋጥማቸዋል። ይህ ደግሞ በቀጥታ አዲስ የተወለደዉን ሕፃን ጤና ይነካል። እናትየዉ በቂ አዮዲን የማትወስድ ከሆነ ሕፃኑ ለአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊጋለጥ ይችላል፤ ለምሳሌ የአእምሮ ዘገምተኝነት። የተለያዩ ማዕድናት እጥረት በተለይ ጨቅላ ሕፃናትን ለልዩ ልዩ በሽታና ከባድ ጉዳቶች ይዳርጋሉ።»

በመሠረቱ እስከአሁን አልተሳካም እንጂ ሁሉም ሰዉ ደረጃዉን የጠበቀ፤ በንጥረ ነገሮች የበለጸገ ምግብ መመገብ የሚችል ቢሆን ኖሮ በጠቃሚ ማዕድናት እጥረት የሚመጡ በሽታዎች ባልተጋለጠ ነበር። ጤናማ ሰዉነትን ለመገንባትም ከመሠረታዊ ምግቦች በተጨማሪ አትክልትና ፍራፍሬ፤ አልፎ አልፎ ደግሞ እነእንቁላል፣ወተት፣ዓሣ እና ሥጋም ቢገኙ መልካም በሆነ ነበር። ነገር ግን በድህነት ለሚኖረዉ አብዛኛዉ ሕዝብ እነዚህ የህልም እንጀራ ካልሆኑ በቀር በተግባር ሊያገኛቸዉ እንደማይችል ነዉ የማኅበራዊ ልማት ባለሙያዉ ቮልፍጋንግ ያማን ቁርጡን የሚናገሩት።ለሰዉነት ገንቢ ምግቦችን በየገበያዉ ማግኘቱባ ይቸግርም ምን ያህሉ የመግዛት አቅም ይኖረዋል የሚለዉ የሚያጠያይቅ መሆኑንም ያሰምሩበታል።ስለዚህ ይላሉ እኒህ ምንዱባን በየዕለቱ የሚያገኙትን መሠረታዊ ምግብ በማዕድናት የማበልፀግ ጥረት እየተሞከረ ነዉ። 80 ሃገራት በሕግ ደረጃ ደንግገዉታል።

Vitamintabletten und Zitrusfrüchte
ምስል Getty Images

«ለምሳሌ ዛምቢያ ዉስጥ በቆሎ በቫይታሚን ኤ እና ቫይታሚን ዲ እንዲበለፅግ በሕግ ተደንግጓል። በዚያ ላይ በየቤቱ ሰዎች በሚመገቡት ምግብ ዉስጥ የድብልቅ ቫይታሚኖች ቅምም ዱቄት የቀረበዉ ምግብ ላይ እየተነሰነሰ የሚመገቡበት ሁኔታም አለ። ይህ የተሳካ ዉጤት ሊኖረዉ ችላል።»

ሌላዉ አስተማማኝ የሚመስለዉ ስልት ደግሞ «ባዮፎርቲፊኬሽን» ነዉ። ይህም ማለት የየአካባቢዉ መደበኛ ምግብ ብዙ ቫይታሚንና ማዕድን እንዲኖራቸዉ በሰዉ ሠራሽ መንገድ ማዳቀል መሆኑም ይገልጻሉ።

«በማዳቀል በስልት ለምግብ የሚሆነዉ ተክል የሚኖረዉ የማዕድን ይዘት እንዲሻሻል ማድረግ ይቻላል። ይህ ብቻም አይደለም ተባይና ድርቅንም የመቋቋም አቅሙንም ማሻሻል ይቻላል።»

እንዲህ ያለዉ የሙከራ ጥረት በተለይ በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት በስኳር ድንች፣ አደንጓሬ፣ ካሳቫ እና በቆሎ ላይ ተደርጓል። ሕንድና ፓኪስታን ደግሞ በቅርቡ ተመራማሪዎች በስንዴ፣ አጃ እና ሩዝ ላይ ሞክረዉታል። ሌላ የአዝርዕት ተመራማሪ ደግሞ በቫይታሚን ኤ የበለጸገዉ ተቀቅሎ የሚበላዉን የሙዝ ዓይነት በዚህ ስልት ጥናት እንዳካሄዱበት ተገልጿል። ለቬልት ሁንገር ሂልፈዉ ያማን እነዚህ ሁሉ ሊበረታቱ የሚገቡ ጥረቶች ናቸዉ። እንዲያም ሆኖ ግን የተለያዩት እነዚህ ምግቦች ዉጤታማነታቸዉ ተረጋግጦ የተጠቃሚዎችም ዘንድ በተግባር ተቀባይነት ማግኘት እንደሚኖርባቸዉ ነዉ የሚያሳስቡት።

Grapefruit Cocktail
ምስል Fotolia/Maksim Shebeko

«እነዚህ የጠቀስናቸዉ አብዛኞቹ ስኬቶች በቤተ ሙከራ ተሠርተዉ ዉጤት ታይቶባቸዋል። ሰዎች እነዚህን ተቀብለዉ ለመጠቀም ዝግጅናቸዉ ወይ የሚለዉን እርግጠኛ መሆን አይቻልም።»

ለምሳሌ ፊሊፒንስ ዉስጥ የመጀመሪያዉ ወርቃማዉን ሩዝ በሰዉ ሠራሽ ስልት በቫይታሚን ኤ እንዲበለፅግ ተደርጎ የተሠራዉ የመስክ ላይ ሙከራ ከስኬቱ ይልቅ አሳሳቢ ነገር ይዞ ነዉ የመጣዉ። ሀገር በቀል የሆነዉ በተወሰነ የአየር ጠባይ በመብቀል ጤናማ ጠንካራ መሆኑን አስመክሯል። በምርምር የተዘጋጁት የተለያዩ ዘሮች «ስዉሩን ርሃብ» ለመዋጋት በሚደረገዉ ጥረት ዉጤት ማስገኘትም ሆነ ትርጉም ሊኖራቸዉ የሚችለዉ አርሶ አደሮች እነዚህን ዘሮች እንደልብ አግኝተዉ መጠቀም ሲችሉ ብቻ ነዉ። ከምንም በላይ ደግሞ ገበሬዎቹ ባለፈዉ ዓመት ዘርተዉት የነበረዉን ይህንኑ የተሻሻለ ዘር ለመጪዉ ዓመት ራሳቸዉ ቋጥረዉ በማስቀመጥ ዳግም ዘርተዉ ማምረት የሚችሉ ከሆነ ነዉ። ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለዉ እንደ አንዳንድ የተለመዱ ምርጥ ዘር እየተባሉ ተዳቅለዉ የሚዘጋጁና በየዓመቱ ገበሬዎች እንዲገዙ የማይገደዱበት ሁኔታ ከኖረ ብቻ ነዉ።

«አቅም የሌለዉ አርሶ አደሮችም ቢሆኑ ይህን የተሻሻለ የዘር ዓይነት መጠቀም መቻል ይኖርባቸዋል። በዓለም ገበያ ላይ ይህን ዘር በሚያቀርብ ብቸኛ አካል ላይ ጥገኛ መሆን የለባቸዉም። በተመሳሳይ ደግሞ የእነዚህ ምርቶች ዋጋ መወደድ የለበትም።»

Frauen arbeiten im Feld
ምስል Roots of Peace

ሩዋንዳ ዉስጥ ከ12 ሚሊዮን አጠቃላይ ሕዝብ 44 በመቶዉ ማዕከላዊ አፍሪቃ በምግብ እጥረት የተጎዳ ነዉ። ከሶስት ሩዋንዳዉያን አንዱ በዘልማድ የደም ማነስ የሚባለዉ ችግር ተጠቂ ነዉ። በተለይ በዚህ ከሚቸገሩ አብዛኞቹ ሴቶችና ልጆች ናቸዉ። ከአምስት ዓመት በታች ከሚሆኑት ልጆች 38 ከመቶዉ ከሀገሩሴቶች17 በመቶዉ የብረት ማዕድን እጥረት መጋለጣቸዉ ነዉ የሚነገረዉ። ይህን ስዉር ርሃብ ለመታገል በተቀየሰዉ ስልት ተጠቅመዉ በቅርቡ በወጡ መረጃዎች መሠረት አብዛኞቹ በማዕድን የበለፀጉ እህሎችን በመዝራት በጤናቸዉ ላይ ያንዣበበዉን አደጋ ለማስወገድ እየሞከሩ ነዉ። የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለማስወገድ ሀገሪቱ በጀመረችዉ ዘመቻም አምስት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ግንባር በመፍጠር እየሠሩ መሆናቸዉን የሩዋንዳ የግብርና እና የእንስሳት ሃብት ሚኒስትር አግነስ ካሊባታ ይናገራሉ። ለሩዋንዳዊ ቦሎቄ የሌለበት ምግብ፤ ምግብ አይደለም የሚሉት ሚኒስትር በሰዉ ሠራሽ ዘዴ የማዕድን መጠኑ የበለጸገዉ ቦሎቄ ዛሬ ትናንሽ ገበሬዎችም ጭምር ከነቤተሰቦቻቸዉ እንዲያመርቱት መደረጉን ያስረዳሉ። ሩዋንዳ 10 የተለያዩ በማዕድን የበለጸጉ የቦሎቄ ዘሮች እንዳሏት ያመለከቱት ሚኒስትር የሀገሪቱ ገበሬዎች በየዕለቱ ሥጋ ለመመገብ አቅማቸዉ ስለማይፈቅድ ፤ ያንን በእነዚህ ዘሮች ለመተካት እየተሞከረ መሆኑን አስረድተዋል። 80 በመቶ የሚሆነዉ ሩዋንዳዊ የገጠር ኗሪና በግብርና የሚተዳደር ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ