1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምግብ ዋስትና ጀግኖች

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 14 2007

የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በተገባደደዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የተሻለ የሰብል ምርት መገኘቱን በቅርቡ ይፋ አድርጓል። በተቃራኒዉ በመላዉ ዓለም ወደ805 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ በቂ ምግብ እንደማያገኝም ጠቁሟል። ከአየር ንብረት ለዉጥና ከለዉጡ መዘዞች በመታገል የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጥረቶች በተለያዩ ሃገራት እየተሞከሩ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1E9NW
Vorbildliche äthiopische Frauen
ምስል Oxfam Äthiopien

ኢትዮጵያ ዉስጥም በተለይ የሴት አርሶ አደሮች ጥረት ላይ ትኩረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎች በመካሄድ ላይ ናቸዉ።

በዓለም የምግብ ምርት ሴቶች ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይም በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ የሚደርሰዉ ተፅዕኖ የሚያስከትለዉን መዘዝ በመቋቋም እህል በማምረቱ ሂደት የሴቶች ድርሻ ላቅ ያለ መሆኑ ቢታመንም ጥረታቸዉ እጅግም እዉቅና ሲሰጠዉ አይታይም። ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከታታይ ከራሳቸዉ ቤተሰብ አልፈዉ ማኅበረሰቡን ብሎም ሀገር ለመመገብ ጥረት ያደረጉ ሴት አርሶ አደሮች ኢትዮጵያ ዉስጥ እዉቅና ያገኙባቸዉ መድረኮች ተዘጋጅተዋል። ባለፈዉ ሕዳር ወር ማለቂያ ላይም ከየሚኖሩበት ክልል በዚህ አስተዋኦዋቸዉ አንደኛ የሆኑት ሴት አርሶአደሮች የምግብ ዋስትና እመቤቶች ተብለዉ ሽልማት ተቀብለዋል።

Bauer bei der Arbeit in Äthiopien
ምስል AP

ሴት የምግብ ዋስትና ጀግኖችን የመሸለምና የማበረታታቱን ተግባር ቀደም ብላ የጀመረችዉ ታንዛኒያ ናት። ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ ነዉ እዚያ ይህ ብቻቸዉን ልጆች እያሳደጉ በእርሻዉ ተግባርም የተጠመዱ እናቶችን የሚያበረታታዉ መርሃግብር የተካሄደዉ። በዉድድሩ የሚሳተፉ ሴት አርሶ አደሮች የሚጠቀሙበት አካባቢን የማይጎዳና ለተፈጥሮ የበኩሉን ክብካቤ የሚያደርግ የግብርና ስልት፣ የአየር ንብረት ለዉጥን እና ያስከተላቸዉን መዘዞች ለመቋቋም የሚያደርጉት ጥረት፣ እንዲሁም በፆታቸዉ ምክንያት የሚደርስባቸዉን ጥቃት የሚከላከሉባቸዉ መንገዶች ለሚያገኙት ነጥብ ዋጋ አላቸዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ይህን መሰሉ ለሴት አርሶ አደሮች እዉቅና የመስጠቱ ተግባር ሲካሄድ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ዝግጅቱን ከኦክስፋም አሜሪካ ጋ በመተባበር የሚያካሂደዉ የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች መድረክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ገብሩ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ዉስጥ ይህን መሰሉን ዝግጅት የማካሄዱ ሃሳብ እንዴት እንደተጠነሰሰ አቶ ዮናስ ሲናገሩ፤

በዚህ ስብስብ የታቀፉት ዘጠኝ የሚሆኑ ድርጅቶች መሆናቸዉን የገለፁት አቶ ዮናስ የተለያየ ሥራዎችን ማከናወናቸዉን ሳይገልፁ አላለፉም። ከእነዚህ ሥራዎች አንዱ ደግሞ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚገኙ በተለይም ረዳት ባለቤት ሳይኖራቸዉ ብቻቸዉን ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ እናቶች በምግብ ዋስትና ዉስጥ ያላቸዉን ሚና የጎላ ቢሆንም እዉቅና ተነፍጎት በመቆየቱ ያንን ማዉጣት የሚለዉ ነዉ። ዓላማዉም ሌሎችን ማበረታታት ነዉ ይላሉ አቶ ዮናስ፤

ቀደም ሲል እንደተገለጸዉ ጀግና ሴት አርሶ አደሮችን ለአራተኛ ጊዜ የሸለመችዉ ታንዛኒያ ተሸላሚዎቹ ከሚመረጡባቸዉ መስፈርቶች ሰፊዉን ስፍራ የሚይዘዉ የአካባቢ ተፈጥሮን ለመከባከብ የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ነዉ። አቶ ዮናስ እንደሚሉት በኢትዮጵያም ከመስፈርቶቹ አንዱ ይኸዉ ነዉ።

Ausgezeichnete äthiopischen Bäuerin
ከተሸላሚዎቹ አንዷምስል Oxfam Äthiopien

በእርግጥም ከሶማሌ ክልል በአስተርጓሚ ያነጋገርኳቸዉ ተሸላሚ ወ/ሮ አሻ የዝናብ እጥረት ባለበት ሁኔታ የሚኖሩ ቢሆኑም በመስኖ በመጠቀም በረሃዉ ላይ ነፍስ ዘርተዉ እንደሚኖሩ የገለፁልኝ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል። ወ/ሮ አሻ በመስኖ የሚያመርቱት ቀይ ሽንኩር ቲማቲም፣ በቆሎ እና ሩዝ ከቤታቸዉ ተርፎ ለገበያ እንደሚያበቁም ገልጸዉልኛል።

ሌላዋ ተሸላሚ አማራ ክልል የሚገኙት ወ/ሮ ማሬ ላቀን በስልክ ማግኘት ባልችልም የአማራ ክልል የወረዳ ግብርና ስራ ስርፀት ባለሙያ ወ/ት ሙሉ አዳም የሰባት ልጆች እናት ሲሆኑ ብቻቸዉን ለሚያሳድጓቸዉ ልጆች በአንድ በኩል ተገቢዉን ትምህርት እንዲያገኙ እያደረጉ ለሌሎች ምሳሌ በሚሆን መልኩ በእርሻዉም የተሳካላቸዉ እንደሆኑ በአጭሩ ገለፁልን።

ከዚህ ቀደም ማለትም ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደዉ ተመሳሳይ መርሃግብር 10 ሴት አርሶአደሮች የምግብ ዋስትና እመቤቶች ተብለዉ ለሽልማት በቅተዋል። ዘንድሮ ደግሞ 8 ሴት አርሶ አደሮች ናቸዉ ልፋታቸዉ እዉቅና አግኝቶ የምግብ ዋስና እመቤቶች የተባሉት። ሽልማቱ ዋንጫና የምስክር ወረቀትን ጨምሮ ለእያንዳንዳቸዉ 30ሺህ ብር መሰጠቱንም አቶ ዮናስ ገልጸዉልናል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ