1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕራባዉያን ማዕቀብና ሩሲያ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 23 2006

ባለፈዉ ዓመት ከሩሲያ ጋር የ326 ቢሊዮን ዩሮ የንግድ ልዉዉጥ ያደረጉት የአዉሮጳ ሐገራት በማዕቀቡ የወለፊንድ ዉጤት ባንድ ወይም በሌላ መንገድ መነካታቸዉ አይቀርም።ከዩናይትድ ስቴትስና ከቻይና ቀጥሎ ከሩሲያ ጋር ከፍተኛ የንግድ ልዉዉጥ ያላት ጀርመን ደግሞ ከሕብረቱ አባል ሐገራት ሁሉ ቀዳሚዋ ናት።

https://p.dw.com/p/1CmVu
ምስል Reuters

ዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ ሕብረት በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣላቸዉን ሩሲያ እንደተጠበቀዉ አጥብቃ ተቃዉመችዉ።የሩሲያ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት አዲሱ ማዕቀብ ወትሮም የሻከረዉን የምዕራባዉያንና የሩሲያን ግንኙነት ይበልጥ የሚያበላሽ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ ሕብረት የዩክሬን አማፂያንን ትረዳለች በሚሏት ሩሲያ ላይ የጣሉት ማዕቀብ በሩሲያ የገንዘብ ተቋማት፤በመከላከያና በሐይል ማመንጫ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያነጣጠረ ነዉ።የማዕቀቡ የተገላቢጦሽ ዉጤት የአዉሮጳ ሐገራትን መንካቱም አይቀርም።ነጋሽ መሐመድ የዜና መልዕክቶችን አሰባስቧል።

የሩሲያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ዛሬ ያወጣዉን መግለጫ-የቀመረበት ቃላት ጥንካሬ-ጠንካራዉ ማዕቀብ ከተገለጡበት ቃላት የጠጠረ ነዉ።ማቀቡን «አፍራሽ እና አጥፊ» ይለዋል-መግለጫዉ።ማዕቀብ ጣዮቹን ደግሞ «ካጭር ጊዜ ባለፍ አርቆ ማስተዋል ያጠጣቸዉ» እያለ ይቀጥላል።

አዲሱ ማዕቀብ እና የበቀሉ ዛቻ ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ በሁለቱ ወገኖች መካከል ከተወሰዱ-አሉታዊ እርምጃ፤ ዛቻዎች ሁሉ ጠንካራዉ ነዉ።ማዕቀቡ የሩሲያ መንግሥት ትላልቅ ባንኮችና የገንዘብ ተቋማት ከምዕራባዉያን አቻዎቸዉ ጋር እንዳይሰሩ፤ የመከላከያ መሳሪያዎች እና ለሕይል ምንጭ የሚዉሉ የቴክኖሎጂ ዉጤቶች ለሩሲያ እንዳይሸጡ የሚያግድ ነዉ።

«ለሩሲያ የሐይል መስክ የሚዉሉ ሸቀጦችና ቴክኖሌጂዎች እንዳይሸጡ አግደናል።በሩሲያ ባንኮችን እና በመከላከያ ኩባንዮች ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ጥለናል።ወደ ሩሲያ የሚደረጉ የወጪ ንግዶችን እና ሩሲያ ዉስጥ የሚከናወኑ የልማት ተግባራትን ለማበረታት የሚሰጡ ብድሮችንና ገንዘቦችን በይፋ አግደናል።ከዚሁ ጋር የአዉሮጳ ሕብረትም ከጎናችን ነዉ።»

Russland Sanktionen VTB Bank
ምስል picture-alliance/AP Photo

የዩናይድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ። በርግጥም የአዉሮጳ ሕብረት፤ ሞስኮ የዩክሬንን አማፂያን ትደግፋለች እያለ ሩሲያን በመወንጀሉም፤ተደጋጋሚ ቅጣት በመጣሉም ከአሜሪካ አልተለየም።እንዲያዉም ተጨማሪዉን ማዕቀብ በመጣል ወይም በማወጅ በሠዓታትም ቢሆን ከአሜሪካኖች ቀድሟል።

የሃያ-ሥምንቱ የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት አምባሳደሮች መሪዎቻቸዉ በተስማሙት መሠረት የማዕቀቡን አፈፃፀም ዘርዝረዉ ያጠናቀቁት ትናንት ማምሻ ነበር።በማዕቀቡ የተገላቢጦሽ ዉጤት ከአሜሪካኖች ቀድመዉ የሚጎዱትም አዉሮጶች ናቸዉ።ብዙ የንግድ ግኙነት ሥላላቸዉ።እርግጥ ነዉ ሩሲያ የምትጎዳዉን ያክል የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት አይጎዱም።

ይሁንና ባለፈዉ ዓመት ከሩሲያ ጋር የ326 ቢሊዮን ዩሮ የንግድ ልዉዉጥ ያደረጉት የአዉሮጳ ሐገራት በማዕቀቡ የወለፊንድ ዉጤት ባንድ ወይም በሌላ መንገድ መነካታቸዉ አይቀርም።ከዩናይትድ ስቴትስና ከቻይና ቀጥሎ ከሩሲያ ጋር ከፍተኛ የንግድ ልዉዉጥ ያላት ጀርመን ደግሞ ከሕብረቱ አባል ሐገራት ሁሉ ቀዳሚዋ ናት።

ሜኻኒክ ታዉኻ የተሰኘዉ የጀርመን ኩባንያ የበላይ ሐላፊ እንደሚሉት ሩሲያና ከሩሲያ ጋር የሚሠሩ የሳቸዉን መሠል የጀርመን ኩባንዮች ስድስት ሺሕ ይደርሳሉ።ዉዝግቡ ሲጀመር አሁን የሆነዉ ይሆናል ብለዉ አላሰቡም ነበር።

«ሩሲያ ዉስጥ የሚሠሩ በርካታ ኩባኖዮች አሉ፤የጀርመን ኩባንዮች ብቻ ከሥድስት ሺሕ ይበልጣሉ።መጀመሪያ ላይ ሁሉም ያሰበዉ ከጥቂት ሳምንታት በሕዋላ ሁሉም ነገር ያልፋል ብለዉ ነበር። ነገሮች የሚረጋጉበት ብልሐት አይጠፋም በማለት አስበንም ነበር።ይሕ ተስፋ አሁን በንኗል።»

Symbolbild EU und Russland Sanktionen
ምስል picture alliance/chromorange

ጀርመን ባለፈዉ ዓመት ከሩሲያ ጋር የነበራት የንግድ ልዉዉጥ ከዘጠና ቢሊዮን ዩሮ በላይ ነበር።ሩሲያ በተደጋጋሚ እንደዛተችዉ ክረምቱ እስኪቃረብ እድፍጣ ለአፀፋ እርምጃ የጋዝ ቧምቧዋን ከዘጋች ደግሞ የደቡብ ምሥራቃ አዉሮጳ ሐገራትን ሕዝብ በብርድ ልታቆራምድ ትችላላች።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ