1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕፀን በር ካንሰር ቅድመ ምርመራ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 27 2007

የማሕፀን በር ወይም ሰርቫይካል ካንሰር በቀላሉ ሊከላከሉት ሲቻል የበርካታ ሴቶችን ሕይወት የሚቀጥፍ በሽታ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። ድርጅቱ እንደሚለዉም በየዓመቱ በማደግ ላይ በሚገኙ ሃገራት ከ270 ሺህ በላይ ሴቶች በዚህ በሽታ ምክንያት ይሞታሉ።

https://p.dw.com/p/1FKWq
Papillomavirus in Zellen von Gebärmutter
ምስል picture-alliance / OKAPIA KG, Germany

የማሕፀን በር ካንሰርን በየዓመቱ አስቀድሞ በሚካሄድ ምርመራ መከላከል ብሎም ማዳን እንደሚቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሳይታመሙ ወደሃኪም ዘንድ ሄዶ ምርመራ ማድረግ በምዕራቡ ዓለም የተለመደ ነዉ። እንዲህ አይነቱ ምርመራ እንደየእድሜ ደረጃዉና ፆታ ሊያጋጥሙ ይችላሉ ተብሎ የሚገመቱ የበሽታ ዓይነቶች ሳይከሰቱ፤ ከተከሰቱም ሥር ሳይሰዱ ለማከምና ለማዳን ፍቱን ዘዴ በመሆኑ ይታወቃል። በያዝነዉ ወር የአዲስ አበባዉ ቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል የማሕፀን በር ወይም በእንግሊዝኛዉ ሰርቫይካል ካንሰር ቅድመ ምርመራን በዘመቻ መልክ ማካሄዱ ተሰምቷል።

Humane Papillomviren
ለማሕፀን በር ካንሰር መንስኤ የሚሆነዉ ፓፒሎማ ቫይረስ ጎልቶ ሲታይምስል picture-alliance/dpa/DKFZ

«ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ» እንዲሉ አበዉ፤ በዓለማችን በመቶሺዎች የሚገመቱ እህትና እናቶችን እድሜ የሚያሳጥረዉ የማሕፀን በር ካንሰር ማንኛዋም እድሜዋ ከ21ዓመት በላይ የሆነች ሴት በቅድመ ምርመራ ልትከላከለዉ ትችላለች ይላሉ በቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል የማሕፀንና ፅንስ ክፍል የድህረ ምረቃ መርሃግብር ዳይሬክተር ዶክተር ባልካቸዉ ንጋቱ። ምርመራዉን አንዲት ሴት የሆነ ምልክት እስክታይ የሚጠበቅ ሳይሆን በየዓመቱ እንደመደበኛ ተግባር መደረግ ይኖርበታል።

በያዝነዉ ወር መጀመርያ ገደማ አንስቶ ለቀናት በአዲስ አበባ ቅዱስ ጳዉሎስ ሃኪም ቤት የማሕፀን በር ካንሰርን ቅድመ ለበርካቶች በነፃ ምርመራ አድርጓል። እንደዶክተር ባልካቸዉ የአሁኑ በዘመቻ መልክ መካሄዱ ካልሆነ በቀር አዲሱ ነገር ይህ የምርመራ አገልግሎት በዚህ ሃኪም ቤት መሰጠት ከተጀመረ ቆየት ብሏል። ዝርዝሩን ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ