1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎትና ተግዳራቶቹ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 8 2006

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያደገ የመጣው የመገናኛዉ ዘርፍ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በርካታ ነገሮችን ለሚዲያ አበርክቷል።በሰዎች መካከል ያለው ማህበራዊ ግንኙነትና የመረጃ ልውውጥ በአዲስ መንገድ እንዲቀየር

https://p.dw.com/p/1CuMY
ምስል picture-alliance/dpa

ካደረጉ መንገዶችም ማህበራዊ መገናኛ አንዱ ነው። መረጃን ለመፍጠርና ለመቀባበል እንዲሁም ሃሳቦችን ለመለዋወጥ የሚያገለግለው ይህ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትሩፋት በውስጡ በርካታ ድረ-ገጾችን የያዘ ነው። ማህበራዊ ድረ-ገጾች ሰዎች ትዝታዎቻቸውን ለማስቀመጥ፤ ስለ አዳዲስ ነገሮች ለመማርና ለመመራመር፤ ራስን ለማስተዋወቅና ጓደኛ ለመፍጠር የሚያስችሉ መንገዶችም አሏቸው። ማህበራዊ ድረ-ገጽ ሬዲዮ፤ቴሌቭዥን፤ጋዜጣና መጽሔትን ከመሳሰለው ተለምዷዊው ሚዲያ የሚለይባቸው መንገዶችም አሉ። ፍጥነቱ፤ ጥራቱ፣ ተደራሽነቱ፤ ለአጠቃቀም ምቹ መሆኑ ከብዙ በጥቂቱ ሊጠቀስ ይችላል።

Symbolbild Twitter und Facebook
ምስል Reuters

ማህበራዊ ድረ-ገጾች ዘርፋቸዉ ብዙ ነው። የኢንተርኔት መድረኮች፤ የድረ-ገጽ ጦማሮች፤ ማህበራዊ ድረ-ገጽ ጦማር፤ ማይክሮ ብሎጊንግ የድምጽ፤ ቪዲዮና ምስል ማከማቻና፤ ማዳመጫ ፤መመልከቻና መለዋወጫዎች ይጠቀሳሉ።

እንድርያስ ካፕላንና ሚካኤል ሃይላይን የተባሉ ሁለት ባለሙያዎች ማህበራዊ ድረ-ገጽን በብዙ መንገድ ይከፋፍሉታል። ማኅበራዊ መገናኛ በሚለው የእነ እንድርያስ ምድብ ፌስቡክ፤ የተባበሩ ፕሮጀክቶች ዊኪፔዲያ፤ ብሎግ ወይም ማይክሮ ብሎጊንግ በሚለው ምድብ ደግሞ ትዊተር በይዘት ምድብ ደግሞ ዩቲዩብን ያስቀምጣሉ።

በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ208 በላይ የሚሆኑ ማህበራዊ ድረ-ገጾች ለዓለም ሕዝብ ግልጋሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። ፌስቡክ፤ ትዊተር፤ ዩቲዩብ፤ ጎግልና ማይስፔስ ደግሞ በዓለም ባላቸው ተቀባይነትና በሚሰጡት ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ተቀዳሚ ናቸው።

እነዚህ የማህበረሰብ ድረ-ገጾች መቀመጫቸውን አሜሪካን ባደረጉ ኩባንያዎች የሚተዳደሩ ሲሆን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የፈሰሰባቸውና በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎችን ያፈሩ ናቸው። ለምሳሌ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፌስቡክ ከ1.2 ቢሊዮን ፤ ትዊተር ደግሞ ወደ 200 ሚሊዮን፤ እንዲሁም ጎግል 540 ሚሊዮን ተጠዋሚዎች አሏቸው።

ማህበራዊ ድረ-ገጾች መረጃና ሃሳብ ለመለዋወጥ ከፈጠሩት ምቹ ሁኔታ ባሻገር የንግድና ግብይትን በማፋጠን ረገድ ላቅ ያለ ሚና ተጫውተዋል። በዚህም « ዘ ቢግ 3» /ሶስቱ ግዙፎች/ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ፌስቡክ፤ ትዊተርና ጎግል ከዘርፉ የሚያገኙት ገቢ ከዓመት ዓመት እድገት በማሳየት ላይ ይገኛል። ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ2014 ፌስቡክ በሞባይል ላይ ባደረጋቸው ማስታወቂያዎች የገቢውን 59 በመቶ ወይም 2.5 ቢሊዮን ዶላር አግኝቷል።

መርጋ ዮናስ

ተክሌ የኋላ