1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመንግስት የደሞዝ ጭማሪ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 29 2006

የኢትዮጵያ መንግስት ለመንግስት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ለማድረግ መዘጋጀቱን ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ይፋ አድርጓል። የደሞዝ ጭማሪዉ ከ 2003ዓ,ም በኋላ ሲደረግ የመጀመሪያ መሆኑ ነዉ። የመንግስት ሠራተኛውን ከሃገሪቱ እድገት ተጠቃሚ ለማድረግ የታሰበ ነው የተባለው ይህ ጭማሪ ከኤኮኖሚ አኳያ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል?

https://p.dw.com/p/1CpH9
Mnisterium für den öffentlichen Dienst in Addis Abeba Äthiopien
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

በመጠናቀቅ ላይ ከሚገኘው የሐምሌ ወር ጀምሮ ለመንግስት ሠራተኞች ከ33 በመቶ እስከ 46 በመቶ የሚደርስ የደሞዝ ጭማሪ የሚደረግ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን አስታውቋል። የደሞዝ ጭማሪውን አስመልክቶ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፍያን አህመድ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አሁን 420 ብር የሚከፈለው የመንግስት ደሞዝተኛ 46 በመቶ ጭማሪ ተደርጎለት ወደ 615 ብር የሚያድግ ሲሆን ለከፍተኛ የመንግስት ተከፋዮች ደግሞ 33 በመቶ የደሞዝ ጭማሪ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ይህ የደሞዝ ጭማሪ በዓመታዊ በጀቱ ላይ 10.3 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚያስከትል የገለጹት አቶ ሱፊያን አህመድ "የመክፈል አቅማችንን በማሟጠጥ ይህ የደሞዝ ጭማሪ ተደርጓል" ብለዋል።
የሐምሌ ወርን የሚጨምረውና በሚቀጥለው የነሐሴ ወር ከተጠቃሚው እጅ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ የደሞዝ ጭማሪ የመንግሥት ሠራተኛውን ያበረታታል ተብሎ ይታሰባል የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር አሰፋ አድማሴ ይሁንና የዋጋ ግሽበትን ሊያመጣ የሚችልበት እድልም እንዳለ ይናገራሉ።
10.3 ቢሊዮን ተጨማሪ ብር ለገበያው ይዞ የሚመጣው የዘንድሮው የደሞዝ ጭማሪ ተጽዕኖው በዋጋ ግሽበት ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከቀረጥ፤ ብድርና ከውጪ መንግሥታት የሚገኝን ድጋፍ ታሳቢ ተደርጎ ወጪዎች ይሰላሉ የሚሉት ዶክተር አሰፋ አድማሴ ይህ የደሞዝ ጭማሪ በመንግስት ዓመታዊ ወጪ ላይም ተጽዕኖ እንዳለው ነዉ የሚያስረዱት።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ