1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመን «ጉደኛ» ምድር

ሰኞ፣ ጥር 18 2007

የአሜሪካ ሕዝብን ደሕንነት ለመጠበቅ ዋሽግተኖች ሰሞኑን ያደረጉት አብዛኛ ዜጎቻቸዉን ከየመን ማስወጣት ነዉ።የመኖች የት ይሒዱ?አደባባይ ወጡ።ሁቲን በመቃወምና በመደገፍ።የመን ቀይ ባሕርን፤የአደን ባሕረ-ሰላጤና አረቢያ ባሕር ይገናኙባታል።ከሁለት ሺሕ ኪሎ ሜትር የሚበልጥ የባሕር ጠረፍ አላት።ጥንታዊናት ሰፊ ።ግን ከአረብ ሐገራት ሁሉ ደሐ

https://p.dw.com/p/1EQlY
ምስል Reuters/Khaled Abdullah

የጥንት እድገት፤ የዕዉቀት፤ ሐብት ሥልጣኔዋምጥቀት ከዛሬዋ ኤርትራ እስከ ቻይና፤ከኢትዮጵያ እስከ ሞንጎሊያ፤ ከሶማሊያ እስከ ሕንድ ዛሬም ድረስ ባልደበዘዘዉ አሻራዋ ይንፀባረቃል።ጦርነት ግን ተለይቷት አያዉቅም።የመን።በአቀማመጥዋ ሥልታዊነት የማይቀና፤ከሚያስቀናዉ ለመጠቀም የማይይመኝ መንግሥት ጥንትም፤ ድሮም፤ ዘንድሮም የለም።ቅናት፤ ጉጉት ምኞታቸዉን ዕዉን ለማድረግ አቅም፤ ጉልበት፤ ቅርበቱ ያላቸዉ ሁሉ በየዘመኑ እየዘመቱ፤ እየገደሉ፤እያጋደሉ በየዘመነኛዉ እየተዘመተባቸዉ፤እየተገደሉ፤ ሌላ አጋዳይ ተክተዉ እንደ ሔዱባት ናት።ገዳይ፤ አጋዳዮችዋ የሚለኩሱባት ጦርነት አጠፋት ሲባልላት ግን አመዷን አራግፋ ከሥልጣኔ ቅሪቷ ጋር ብቅ ትላለች።ከፋፍለዋት-አንድ፤ አንድ አድርገዋት ብዙ ትሆናለች።እየከበረች-ትደኸየላች።ዛሬም አንድም ብዙም አይደለችም።ጦርነት ሠላምም የለባትም።የመን ጉደኛ ምድር።ላፍታ እንቃኛት።

በሁለተኛዉ ያዓለም ጦርነት ወቅት የሠሜን አፍሪቃዉ ዉጊያ ለብሪታንያ ማርሻል ሞት ጎመሪን ለጀርመን ማርሻል የኤርቪን ሮመልን ጀግንነት ካስመሰከረ፤ለቱርኮች የጄኔራል ሐዲም ሱሌይማን ፓሻን የጦር ሜዳ ጀግንነትን፤የአስተዳድር ፖለቲከኝነት ከአራት መቶ አመታት በፊት አረጋግጦ ነበር።ሐዲም ሱሌይማን ፓሻ የሰሜን አፍሪቃ ተቀናቃኞችን ደፍልቀዉ ግብፅ ላይ ጠንካራ ገዢነታቸዉን ካረጋገጡ በኋላ ወደ ደቡብ ምሥራቅ ቁል ቁል ሲቃኙ ያቺ ሐገር እንዲሕ እንደዘንድሮዉ ተመሠቃቅላ አይዋት።

Machtkampf im Jemen 22.1.2015
ምስል Reuters/Abdullah

በ1530ዎቹ አጋማሽ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ለቆስጠንጥንያ አለቆቻቸዉ በፃፉት ደብዳቤም

« የመን ገዢ የሌላት ባዶ ግዛት ናት።ሐገሪቱን ማስገበር ብቻ አይደለም ቀላልም ነዉ።ከተቆጣጠርናት የሕንድ ምድር አዛዥነትችንን የሚያረጋግጥ፤ በየዓመቱ ከፍተኛ ወርቅና ጌጣ ጌጥ ወደ ቆስጠንጥኒያ መላክም ያስችለናል።» አሉ።

የመናዊዉ አይደሩስ አል-ሜታር በቀደም እንዳሉት ያቺ ሐገር ከአምስት መቶ ዓመታት በኋላ ዘንድሮም እንደየኔዉ ናት።« ሐገሪቱ ባዶ ናት፤ ፖለቲካዊ ክፍተት ዉስጥ ትገኛለች።የሁሉም የየመን ፖለቲካዊ ቡድናት ተወካዮች በጉዳይ ላይ እንዲወያዩ እንመኛለን።ሐገሪቱ አሁን ካለችበት የካፋ ችግር ዉስጥ እንዳትገባ የጋራ ወታደራዊ ምክር ቤት መመስረት አለባቸዉ።»

የበርግጥም ባዶ ናት።የሁቲ አማፂያን ርዕሠ-ከተማ ሠነዓን ባለፈዉ ሳምንት በተቆጣጠሩ ማግሥት ጠቅላይ ሚንስትሯ ከነ ካቢኔያቸዉ ሥልጣን ለቀቁ።ባለፈዉ ሐሙስ የጠቅላይ ሚንስትር ኻሊድ ባሀሕን የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ የተቀበሉት ፕሬዝዳንት አብድረቦ መንሱር ሐዲ የዚያኑለት ሥልጣን መልቀቃቸዉን አስታወቁ።የፕሬዝዳንቱን ሥልጣን መልቀቅ ማፅደቅ የሚገባዉ የሐገሪቱ ምክር ቤት ነዉ።ምክር ቤቱ ሥለ ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን መልቀቅ ሊነጋገር ቀርቶ መሠብሰብ እንኳን አልቻለም።

በልማዱ ወታደራዊ የበላይነትን የተቀዳጀዉ ሐይል መንግሥት መመስረት ነበረበት።የመን ግን እንዲያ የለም።ርዕሠ ከተማ ሰነዓን የሚቆጣጠሩት የሁቲ ሚሊሻዎች ቢያንስ እስካሁን መንግሥት መመሥረት አልፈለጉም፤ ወይም አልቻሉም።ግራ አጋቢ ምድር።

የሰነዓዉ ተባባሪ ወኪላችን ግሩም ተክለ ሐይማኖት።የመን እንደ ግዛት ሰዉ ካወቃት ከክርስቶስ ልደት አምስት ሺሕ ዓመተ-ዓለም ጀምሮ ቱርክ ገሚስ ዓለምን እስካስገበረችበት ጊዜ ድረስ በየዘመኑ ሱሌይማን ፓሻ እንደገለጧት ዓይነት ነበረች።ከሳባዎች እስከ ሐድራሞች፤ ከቃታባኖች እስከ ማኢኖች፤ ከኢትዮጵያዉያን እስከ ሮሞች፤ ከፋርሶች እስከ አረቦች፤ እያስገበሩ ገብረዉባታል።

Jemen Huthi-Befürworter demonstrieren in Sanaa 23.01.2015
ምስል Reuters/K.Abdullah

ሐይማኖት የለሾች፤ አይሁዶች፤ ክርስቲያኖች፤ ሙስሊሞች ተፈራርቀዉባትል። ቱርኮች እግራቸዉን ከተከሉባት በሕዋላ በተለይ ከዛይዴይ ሐይላት የገጠማቸዉን ተቃዉሞ ለመደምሰስ የገብፁ ገዢ ሐዲ ሱሌይማን ፓሻ ያቀረቡትን ሐሳብ የቆስጠንጥንያ አለቆቻቸዉ አፀደቁት።የቱርክ ጦር በዘጠና መርከብ ተጭኖ ቀይ ባሕርን ተሻገረ እና ጦርነት።1538።ጦርነቱ ቀጠለ።ተጨማሪ የቱርክ ጦር ከግብፅ ዘመተ።ጦርነቱ አላባራም።

ከጥቂት አመታት በፊት የመንን በቀላሉ እናስገብራለን ያሉት የቱርክ ጠንካራ ጄንራል አዉነቱን መቀበል ግድ ነበረባቸዉ።

«እንደ የመን ፈታኝ አካባቢ አጋጥሞን አያዉቅም።በየጊዜዉ የምናዘምተዉ ጦር ዉሐ እንደገባ ጨዉ ይሟሟል።» ብለዉ ነበር።

ቱርክ በጥቅሉ 80 ሺሕ ወታደሮች አዝምታለች።የቱርክ የጦር አበጋዞች በ1539 አብዛኛ የመንን ሲቆጣጠሩ የተረፋቸዉ ወታደር ግን ሰባት ሺሕ ብቻ ነበር።ያኔ በሰሜናዊ የመን አካባቢ ጠንካራ መስተዳድር መሥርተዉ የነበሩት የዛይዲ ሐራጥቃ ሙስሊሞች ዛሬ፤ «አማኝ ወጣቶች፤ አንሳር አላሕ » ወይም በገነነዉ ሥማቸዉ «ሁቲዎች» ተብለዉ የሚጠሩት ሐይላት ቅም አያት፤ቅድመ-አያቶች ናቸዉ።

Jemen Huthi-Rebellen 22.01.2015
ምስል Reuters/K. Abdullah

የአዉሮጳ ሐያላን በተለይም ብሪታንያ ፈረንሳይ ቱርኮችን እየገፉ መካከለኛዉ ምሥራቅን ሲቀራመቱ ብሪታንያ ደቡብ የመንን ከሰሜንዋ ነጥላ ተቆጣጠረቻት።

የአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎች የልዕለ ሐያልነቱን ሥፍራ በዩናይትድ ስቴትስና በሶቬት ሕብረት ሲቀሙ ሰሜን የመን በጎሳ መሪዎች በሚዘወረዉ ፊዉዶ-ካፒታሊስታዊ ሥርዓት ሥት ገዛ ደቡቧ የሶሻሊስቱን ጎራ ተቀየጠች።

የግብፁ ወታደራዊ መሪ ኮሎኔል ገማል አብድናስር አንድ የማይሆነዉን አረብ አንድ አደርጋለሁ ብለዉ በሚዋትቱበት ዘመን ሰሜን የመን ከጀርባ አሜሪካኖችና ሶቭየት ሕብረቶች በሚገፉቸዉ ከፊት ለፊት ሳዑዲ አረቢያና ግብፅ ባዘመቱት ጦርና በሚደግፏቸዉ ሐይላት ጦርነት ለተከታታይ ዓመታት ስትነድ ነበር።

ከናስር ሕልፈት፤ ከተከታታዩ ጦርነት፤ ከትርምስ ምስቅልቅሉ በኋላ በጎሳ መሪዎች ድጋፍ የሰነዓ ቤተ-መንግሥትን የተቆጣጠሩት ዓሊ አብደላ ሳላሕ የአደኑን ሶሻሊስታዊ ሥርዓት አፍርሰዉ የመንን አንድ ለማድረግ ያደረጉት ጥረት ዘመኑም ረዳቸዉ፤ ተሳካላቸዉም።አንድነቱ ግን ረጋ ሠራሽ ብጤ ነበር።

የሳላሕ አምባገነናዊ የአገዛዝ ዘመን እየረዘመ፤የእስተዳደር ፊሊጣቸዉ ከጎሳ ጎሳ፤ ከሐራጥቃ-ሐራጥቃ ማበላለጡ እየገጠጠ፤መሐመድ ዓል ሁቲና ወንድማቸዉ ሁሴይን አል-ሁቲ የሳይዲዎችን የዛይዲዎችን እመነት፤ባሕልና ይትባሐል የሚያስተምሩ ትምሕርት ቤቶችንና ተቋማትን መመስረት ጀመሩ።

የመጀመሪያዉ ትምሕር ቤትና ክበብ የተቋቋመዉ በ1992 ነበር።ሰዓዳ ግዛት።ከሺዓ እስልምና ጋር የሚቀራረበዉን ሐራጥቃ የሚከተሉት የዛሬዎቹ የሁቲ አማፂያንን ኢራን እንደምትረዳቸዉ የምዕራብ ሐገራት ፖለቲከኞች፤ የፖለቲካ ተንታኞችና ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ ይናገሩ።ሱኒዎች የሚበዙበትን የየመን መንግሥትትና ጎሳዎችን ደግሞ ሳዑዲ አረቢያ እንደምትደግፋቸዉ በሠፊዉ ይናገራሉ።

የኢራን ሺዓ አያቱላሆችን ሥርዓት ለመገርሰስ ግልፅ ጦርነት የገጠሙት የኢራቁ ሳዳም ሁሴን ነበሩ።የዛይዲዎችን ታሪክና ባሕል ለመጠበቅ የተመሠረቱ ተቋማትን ይመራ የነበረዉ የአማኝ ወጣቶች ስብስብ ወደ ሽምቅ ተዋጊነት የተቀየረዉ ግን አሜሪካኖች የኢራንን ቀንደኛ ጠላት ሳዳም ሁሴንን ለማስወገድ ኢራቅን መዉረራቸዉን በመቃወም ነበር።በ2003።

Schwere Kämpfe um Präsidentenpalast im Jemen 19.01.2015
ምስል picture-alliance/ZUMAPRESS.com

እኒያ ወጣቶች በ2003 ዩናይትድ ስቴትስንና እስራኤልን እያወገዙ አደባባይ መዉጣት ሲጀምሩ ሲጀምሩ በአሜሪካኖች ታማኝ በሪያድ ገዢዎች ይረዳሉ የሚባሉት ፕሬዝዳንት ዓሊ አብደላ ሳላሕ ያዘመቱት ጦር የወጣቶቹን መሪና አስተባባሪ ሁሴይን አል ሁቲን ገደለ።2004።ወጣቶቹ የቡድናቸዉን ሰም በሟች መሪያቸዉ ስም በመሪያቸዉ ሰይመዉ የሠነዓን መንግሥት ይወጉ ገቡ።

የሱኒዋ ሳዑዲ አረቢያ የምትረዳቸዉ ጎሳ መሪዎችም ከዓሊ አብደ ሳሌሕ መንግሥት ወግነዉ ሁቲዎችን ከመዉጋት ይልቅ ገሚሱ ለአልቃዲ አባላት ድጋፍና ከለላ በመስጠት፤ሌሎቹ ደግሞ አልቃኢዳን በመዉጋቱ እንደተጠመዱ ነበር የሠላሳ ዓመቱ ገዢ ዓሊ አብደላ ሳላሕ በሕዝባዊ አመፅ፤ በአካባባዉ መንግሥታትና በዩናይትድ ስቴትስ ግፊት ከሥልጣን የተወገዱት።

ሳላሕን የተኩት ፕሬዝዳንት አብድረቦ መንሱር ሐዲ ለዋሽግተንና ለሪያድ ታማኝነታቸዉን በርግጥ አላጓደሉም።ትኩረታቸዉ በሙሉ ግን ደጋፊዎቻቸዉ የሚፈልጉትን ለማሟላት አል-ቃኢዳ መዉጋቱ ላይ ነበር።ፕሮፈሰር ጉተር ማየር።

«የመን እስካሁንም የነበራት ለንቋሳ መንግሥት ነዉ።በተለይም ምሥራቃዊና ደቡብ ምሥራቅ የሐገሪቱ ክፍል የመንግሥት መዋቅር አለ ማለት እይቻልም።በዚሕ አካባቢ አል ቃኢዳ በተለይ ደቡባዊ ክፍሉን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮታል ማለት ይቻላል።የሐዲ መንግሥት ጦር ከዩናይትድ ስቴትስ የድሮን ድብደባ ጋር በመተባበር አል-ቃኢዳን ሲወጉ ነበር።»

የቀድሞዉ የሶሻሊስት የመን (ደቡብ) የጦር ጄንራል ሐዲ የዋሽግተኖችን ፍላጎት ለማርካት ምሥራቅና ደቡባዊ ምሥራቅ የመን ላይ ሲንደፋደፉ የጦር ጄኔራሎቻዉ ዓመፅ፤ የትዉልድ አካባቢያቸዉ የመገንጠል ጥያቄ እየተጠናከረ መጣ።ባለቀ ሠነዓን የመንን በስድስት የፌደራላዊ አስተዳደር ለመሸንሸን ያደረጉት ሙከራም ተቀባይነት አላገኘም።

ሐዲ ተቃዋሚዎቻቸዉን በተለይም አል-ቃኢዳንና አማፂ ጄኔራሎቻቸዉን በሁቲ አማፂያን ለመቅጣት የሰነዓ በርን ከፍቱላቸዉ።ሁቲዎቹ ሰነዓ በገቡ በአራተኛ ወራቸዉ ጠመንጃቸዉን ሐዲ ላይ ደገኑ።የየመን ሕዝብ በተኩስ፤ትምርምስ፤ምስቅል ቅሉ መሐል ባደባባይ ይሰለፋል።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦቦማ መንግሥታቸዉ አል-ቃኢዳን የማጥፋቱ ጦርነት ይቀጥላል ይላሉ።

Huthi-Rebellen stürmen Präsidentenpalast im Jemen
ምስል picture-alliance/dpa

«የፀረ-ሽብሩ እንቅስቃሴ ተቋርጧል የሚል ይዘት ያላቸዉ አንዳድ ዘገቦች አብቤያለሁ።ይሕ ትክክል አይደለም።የመን ዉስጥ የአል-ቃኢዳ መሪዎችን ማደናችንን እንቀጥላለን።የአሜሪካ ሕዝብን ደሕንነት ለማረጋገጥ ግፊት ማድረጋችንን እንቀጥላለን።»

የአሜሪካ ሕዝብን ደሕንነት ለመጠበቅ ዋሽግተኖች ሰሞኑን ያደረጉት አብዛኛ ዜጎቻቸዉን ከየመን ማስወጣት ነዉ።የመኖች የት ይሒዱ?አደባባይ ወጡ።ሁቲን በመቃወምና በመደገፍ።የመን ቀይ ባሕርን፤የአደን ባሕረ-ሰላጤና አረቢያ ባሕር ይገናኙባታል።ከሁለት ሺሕ ኪሎ ሜትር የሚበልጥ የባሕር ጠረፍ አላት።ጥንታዊናት ሰፊ ።ግን ከአረብ ሐገራት ሁሉ ደሐ።አሁን ደግሞ እየተመሰቃቀለች ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ