1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚደረገዉ ጥረት

ረቡዕ፣ መስከረም 14 2007

በተወለዱ 28 ቀናት ጨቅላዎች ለሞት የሚዳረጉበት ምክንያት ከነፍሰጡር እናት ጤንነትና አመጋገብ ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው። የእርግዝና ክትትልና በወሊድ ወቅትና ከወሊድ በኋላ እንክብካቤ በማድረግ በተወለዱ እስከ 28 ቀናት ውስጥ የሚሞቱ ህጻናትን ቁጥር መቀነስ ይቻላል።

https://p.dw.com/p/1DJDH
ምስል picture-alliance/dpa

ኢትዮጵያ ከምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች መካከል አንዱን የህጻናትን ሞት በመቀነስ አሳክታለች። የህጻናት ሞትን ለመቀነስ በኢትዮጵያ የተሰሩ ስራዎችና ምን ይመስላሉ?

ሲስተር ሰላም አበራ የጤና ኤክስቴሽን ሙያዋን በድሬዳዋ ከተማ የደቻቱ ጤና ጣቢያ ከአመታት በፊት ስትጀምር አንዲት ነፍሰጡር ገጠመቻት።ወጣቷ ሲስተር ሰላም የገጠመቻት ነፍሰጡር የ19 አመት ወጣት እንደነበረች ታስታውሳለች።

ሲስተር ሰላም የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አሰልጥኖ በመላ ሃገሪቱ ካሰማራቸው 38 ሺ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች መካከል አንዷ ናት።እነ ሲስተር ሰላም 16ቱን የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጆች በማበረሰቡ ውስጥ የመተግበር ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል።ከእነዚህ ሃላፊነቶቻቸው መካከል የእናቶችና የሕፃናት ሞትን መቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች ይገኙበታል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምዕተ አመቱ የልማት ግቦች በጤናው ዘርፍ ከታቀዱት መካከል የህጻናትን ሞት መቀነስ አንዱ ነበር።እ... 1990 እስከ 2015 ባሉት አመታት አዲስ ለሚወለዱ ጨቅላዎችና እናቶቻቸው ክብካቤ፤የተመጣጠነ ምግብና የክትባት አገልግሎት ማቅረብ ለሞት ከሚዳርጉ በሽታዎችም መጠበቅ የህጻናት ሞትን በሁለት ሶስተኛ ለመቀነስ ያስችላል የሚል እቅድ ተነድፎ ነበር።የ25 አመታቱ ውጥን የጊዜ ገደቡ ሊጠናቀቅ በተዳረሰበት በዚህ ወቅት ማላዊ፤ባንግላዴሽ፤ላይቤሪያ፤ታንዛኒያ፤ ኢትዮጵያ፤ቲሞር ሌሴቴ፤ኒጀርና ኤርትራ ከምዕተ-ዓመቱ የልማት ግቦች በአራተኛ ደረጃ የተቀመጠውን የህጻናትን ሞት መቀነስ ማሳካታቸውን ዩኒሴፍ አስታውቋል። ኢትዮጵያ የህጻናት ሞትን 69 በመቶ በመቀነስ እቅዱን ከሶስት አመታት በፊት ማሳካት መቻሏን በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ዶ/ር ፒተር ሳላማ ይናገራሉ።

Kongo Nahrung in den Least Developed Countries Flash-Galerie
ምስል UNICEF

''አንደኛው የኢትዮጵያ መንግስት እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የገባው ቁርጠኝነትና እቅዱን ለማሳካት በገንዘብና የሰው ሃይል ያደረገው ድጋፍ ነው። በእኔ አስተያየት በመንግስት ደሞዝ ተቀጥረውና በመላ ሃገሪቱ በሚገኙ መንደሮችና ቀበሌዎች የተሰማሩት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ለእቅዱ ስኬታማነት መሰረታዊ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል።አብዛኞቹ ደግሞ ለማገልገል ቁርጠኛ የሆኑ ወጣት ሴቶች ናቸው።''

እንደ ዶክተር ፒተር ሰላማ ኢትዮጵያ የህጻናትን ሞት በመቀነስ ረገድ ላስመዘገበችው ስኬት ቀዳሚውን ሚና የተጫወቱት ሲስተር ሰላምን የመሰሉ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እውነተኛ ጀግኖች ናቸው። የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎቹ እናቶችና ህጻናት ለሚገጥሟቸው ችግሮች መፍትሄ በመስጠትና በማስተማር ቀዳሚ ናቸው የሚሉት ዶ/ር ፒተር ሳላማ የኢትዮጵያ መንግስት ህጻናትን ለሞት የሚዳርጉ ምክንያቶችን በመለየት ትኩረት መስጠቱ ለስኬታማነቱ ተጠቃሽ ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ።

''የኢትዮጵያ መንግስት ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህጻናትን ለሞት የሚዳርጉ ምክንያቶች በመለየትና በምክንያቶቹ ላይ በፕሮግራሙና በጀቱ ትኩረት ትኩረት እንዲያደርግባቸው አደረገ። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የአፍሪካ ሃገራት ህጻናትን ለሞት የሚዳርጉ እንደ ተቅማጥ፤ወባ፤ በክትባት ሊወገዱ የሚችሉ በሽታዎችና አዳዲስ የሚወለዱ ጨቅላዎች ላይ የሚከሰቱ የጤና መታወኮች ናቸው።የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፕሮግራምና በጀት የህጻናት ሞትን በሚፈጥሩት በእነዚህ ምክንያቶችና መረጃዎች ላይ ያተኮረ ነው።''

ኢትዮጵያ የህጻናትን ሞት 69 በመቶ በመቀነስ ያስመዘገበችው ስኬት ከማላዊ፤ባንግላዴሽና ላይቤሪያ አኳያ ሲታይ ዝቅ ያለ ነው።ለ25 አመታት የዘለቀው የምዕተ አመቱ የልማት ግቦች የጊዜ ገደብ ወደ መገባደጃው ቢጠጋም ኢትዮጵያ በዘርፉ የጀመረችውን ስራ አጠናክራ የምትቀጥልበትን መንገድ ከአሁኑ መወሰኗን ዶ/ር ፒተር ሳላማ ይናገራሉ።

''ለምሳሌ ያህል የአሜሪካን፤ህንድና የኢትዮጵያ መንግስታት በጋራ የሚመሩት «የታደሰ ቃልኪዳን» በእንግሊዘኛው « ኧ ፕሮሚስ ሪኒውድ» የተሰኘ ፕሮግራም አለ። በዚህ ፕሮግራም ከሚወለዱ 1000 ህጻናት የሟችችን ቁጥር ወደ 20 ለመቀነስ መንግስታት ይሰራሉ። አሁን በኢትዮጵያ ከሚወለዱ 1000 ህጻናት መካከል 64 ይሞታሉ። ይህንን ቁጥር መንግስትና አጋሮቹ ወደ 20 ለመቀነስ እየሰሩ ነው። በነገራችን ላይ ይህ ቁጥር መካከለኛ ገቢ ካላቸው ከፍተኛ ሃገራት የሚገኝ ነው።ይህ እቅድ ከባድ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግስት ያሳካዋል የሚል እምነት አለኝ። ''

/ር ፒተር ሰላማ ኢትዮጵያ የህጻናትን ሞት ለመቀነስ ባደረገችው ጥረት ከፍተኛውን ድርሻ ተጫውተዋል ካሏቸው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች መካከል አንዷ የሆነችው ሲስተር ሰላም አበራ ኢትዮጵያ የህጻናትን ሞት በመቀነስ ከምዕተ-ዓመቱ የልማት ግቦች አንዱን ማሳካቷን ስትሰማ ደስተኛ መሆኗን ትናገራለች።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከሚወለዱት 1000 ሕፃናት 64 ሲሞቱ ከነሱ ውስጥም 37 ጨቅላዎች ናቸው፡፡ የጨቅላ ሕፃናቱ ያለዕድሜ መወለድ፣ በወሊድ ጊዜ የሚፈጠር ችግርና የሰውነት በኢንፌክሽን መመረዝ ጨቅላዎቹን ለሞት የሚያጣድፏቸው ምክንያቶች ናቸው፡፡ የህጻናት ሞትን በመቀነስ ከምዕተ አመቱን የልማት ስምንት ግቦች አንዱን ያሳካችው ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ የጨቅላ ሕፃናቱን ሞት መቀነስ ይኖርባታል። በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ፒተር ሳላማ ለዚህም መንግስት ትኩረት መስጠቱን ይናገራሉ።

UN Millenniumsziele Schule in Afghanistan
ምስል UN Photo/Shehzad Noorani

በተወለዱ 28 ቀናት ጨቅላዎች ለሞት የሚዳረጉበት ምክንያት ከነፍሰጡር እናት ጤንነትና አመጋገብ ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው። የእርግዝና ክትትልና በወሊድ ወቅትና ከወሊድ በኋላ እንክብካቤ በማድረግ በተወለዱ እስከ 28 ቀናት ውስጥ የሚሞቱ ህጻናትን ቁጥር መቀነስ ይቻላል። የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ላይም ትኩረት አድርጓል።በእርግዝና፤ወሊድ እንዲሁም አዲስ የተወለዱ ህጻናት ህይወት የመጀመሪያ ቀን ለሚደረግ ክትትልና ክብካቤ የጤና ለውጥ እቅድ (Health Transformation Plan) ተብሎ በሚጠራው አዲሱ እቅድ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። ''

ሲስተር ሰላም አበራ የጤና ኤክስቴንሽን ሙያዋን ስትጀምር እንክብካቤ ያደረገችለት እርግዝና ተወልዶ የሶስት አመት ጤነኛ ልጅ ሆኗል።

በዚህ መሰናዶ ላይ የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን አስተያየት ለማካተት ያደረግንው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ