1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕዋ ጉዞና አደጋው

ሐሙስ፣ ጥቅምት 27 2007

በሕዋ ለመመራመርም ሆነ ለመንሸራሸር፣ የሚደረግ ጉዞ፣ በምድር ላይ እንደምናውቀው የተለያየ የማጓጓዣ ዘዴ ፍጹም ቀላል አይደለም። በሕዋ ጉዞ የማይታሰብ የተለያየ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል በማሰብ፣ በማሰላሰል ፤ አማራጭ መላዎችን ሁሉ መሻቱ ተገቢ ነው።

https://p.dw.com/p/1Di15
ምስል picture-alliance/dpa

ከሰሞኑ የደረሱ አደጋዎች ተጨማሪ አመላካቾች ናቸውና!

Weltraumtourismus Virgin White Knight
ምስል AP

የብሪታንያ ተወላጅ በሆኑት የጠነጠኑ ሃብታም ፤ ሰር ሪቸርድ ብራንሰን ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ፣ በኒው ሜክሲኮ ፌደራል ክፍለ ሀገር ዋና ጣቢያውን ያቋቋመው የግል የሕዋ ጉዞ ወኪል ኩባንያ ፣ «ቨርጅን ጋላክቲክ» ፣ ባለፈው ዓርብ ፣ አንድ የጠፈር መንኮራኩር አብራሪው ሲሞትበት ሁለተኛው ቆስሎ በዣንጥላ ወርዶ ሕይወቱን ለማትረፍ በቅቷል። ከኩባንያው ዋይታ ፤ የመገናኛ ብዙኀን የላቀ መስሎም ነው ጉዳዩ ሲነሣ ሲጣል የሰነበተው። የሕዋ ቱሪስቶች አመላላሹ፣ የተጠቀሰው ኩባንያ፤ SpaceShip Two-መንኮራኩር ተሸካሚ ጥንድም ሆነ መንታ አይሮፕላን ፤ ከተወሰነ ርቀት መንኮራኩሩን ካመጠቀ በኋላ ፤ ተልእኮው ባለመሣካቱ መንኮራኩሩ ሊቃጠል ችሏል።

ከምድር ከባቢ አየር ውጭ ፣ 150 ኪሎሜትር ያህል ራቅ ብሎ ፣ የስበት ኅይል ከሌለበት እርከን ፣ በሕዋ ቱሪስትነት ደርሶ መልስ ለአንድ ሰው የሚከፈለውን 250,000 ዶላር ዝግጁ በማደረግ ከ 700 በላይ የተመዘገቡ መኖራቸው ታውቋል። በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰለፉ ታዋቂ ሰዎች፤ ፣ የሃሊውድ ኮክብ ተዋንያን አንጀሊና ጆሊ ፣ ጀስቲን ቢበር፤ ቶም ሐንክስ፤ ሊዎናርዶ ዲ ካፕሪዮ እንዲሁም ድምጻዊት ሌዲ ጋጋ ን የመሳሰሉ ጭምር ፤ ባለፈው ዓርብ ፣ ከሙሃቪ ምድረ-በዳ አናት የደረሰው የመንኮራኩር አደጋ ቢያስደነግጣቸውም ፣ በጉጉት የሚጠባበቁትን የሕዋ የሽርሽር ጉዞ የሠረዙ አይመስሉም። በአዲሱ 2015 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት በጸደይ ምኞታቸውን ለማሣካት ተራቸውን በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ። ለሕዋ ቱሪስቶች ፤ ጉዞ ሲያመቻች የቆየው ኩባንያ ፣ «ስፔስሺፕ ቱ» ለሁለት አብራሪዎችና 6 ተሳፋሪዎች ቦታ ያለው መንኮራኩር ነው ያዘጋጀው። ለሙከራ ያመጠቀው ይኸው መንኮራኩር ነው ከተቃጠለ ወዲህ ፤ ሌላ የጉዞ መንኮራኩር በመሠራት ላይ መሆኑ ታውቋል።

Richard Branson enthüllt Flugzeug für Weltraumtouristen - Eve
ምስል Virgin Galactic

ቱጃሩ፣ የኩባንያው ባለቤት ሰር ሪቸርድ ብራንሰን፣ የደረሰው አደጋ ቢያስደነግጥም ፣ የሕዋ ቱሪስቶችን አድርሶ የመመለሱ የረጅም ጊዜ እቅድና ተግባር ይቀጥላል ነው ያሉት ። ብራንሰን፣ አያይዘውም፤ ከተፈጠረው ስህተት በመማር በቀጣዩ ርምጃ ሁኔታዎች እንደሚሻሻሉ ነው የተናገሩት።

«ምንጊዜም አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል እናውቃለን። ሆኖም ሆኖም ግን ዕውር-ድንብራችንን በመንቀሳቀስ ተግባራችንን የምናስቀጥል አይደለንም። እንዲያ ብናደርግ ግን ሐዘኑ በደረሰባቸው ሰዎች እንደማላገጥ ነው የሚያስቆጥርብን። በምን ስህተት፣ ያ አደጋ እንደደረሰ በመርመርም የደህንነቱን ይዞታ እንዴት እንደምናሻሻልና ፤ እንዴት ወደፊት መራመድ እንደምንችል ግንዛቤ እንጨባጣለን። የሰው ልጅ ዐበይት ተግባራትን ያከናወነው እጅግ ከባድ ከሆነ ጣር ጋር መሆኑን ፤ እውነት ነው አምናለሁ። ይህ የእኛ ቡድን ፍርሃት የሚባል የማያውቃቸውን ፣ እጅግ ብሩሕ አእምሮ ያላቸውንና አይበገሬዎችን ያካተተ ነው። ጀግኖቹን አባራሪዎችና ፣ ከዚህ የበረራውን አስተባባሪ አባላት ፣ እጅግ አሳዛኝ ከሆነው ክሥተት በመነሣት ትልቅ ክብር ልንሰጣቸው ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። ወደፊት በመግፋት፣ በመንቀሳቀስ ፤ የሰውን ዐቢይ የሥራ ክንዋኔ ገደብ፣ ድንበር ማሻገር የምንችለው፤ በጋራ ፍላጎት አንድነትን አጠናክረን ስንገኝ ነው »።

« ስፔስሺፕ ቱ» መንኮራኩር በአይሮፕላን ተጭኖ ከምድር ከፍ ብሎ በመብረር 15 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሲደርስ ፣ በራሱ የሮኬት ኃይል እስከ ሕዋ እርከን እንዲመጥቅ ነው የተዘጋጀው። በአቅድ የተሠራና የተመራ ሁሉ ሁልጊዜ ይሣካል ብሎ መጠበቅ እንደማይቻል ከዚህ ቀደም የደረሱ አደጋዎችም አመላካቾች ናቸው። ስለዓርቡ አደጋ የቨርጂን ጋላክቲክ ኩባንያ የሥራ መሪ ፣ ጆርጅ ኋይትሳይድስ ባለፈው ዓርብ ይህን ነበረ ያሉት።

«የሕዋ ጉዳይ ከባድ ነው፤ እናም ዛሬ አስቸጋሪ ዕለት ነው። ምን እንዳጋጠመ ለማወቅ ፤ ምርመራው እንዲካሄድ በሁሉም ነገር እንደግፋለን ። ወደፊት መንቀሳቀስ የምንችለውም በዚህ ፈተና ውስጥ በማለፍ ነው።»

ሕንድ በአንስተኛ ወጪ ፣ በ (74 ሚሊዮን ዶላር) ያመጠቀቻት መንኮራኩር ፣ ያውም በመጀመሪያ ተልእኮ ፣ ባለፈው መስከረም 14 ,2007 ያላንዳች ሳንክ ማርስ ምሕዋር መግባቷን ስታረጋግጥ፤ ቻይና ወደ ጨረቃ የላከቻት መንኮራኩር ዥያዖፌ(XIAOFEI) (ንዑሷ በራሪ ) ማለት ነው፣ በተሣካ ሁኔታ ወደ ምድር መመለሷን ስታረጋግጥ ፣ መንኮራኩሮችን ወደ ሕዋ በማምጠቅ የረዥም ጊዜ ልምድ ባላት ሀገር በዩናይትድ ስቴትስ ፣ ባለፈው ዓርብ በሕዋ ጉዞ ረገድ አነጋጋሪ ሁኔታ ነው ያስከተለው።

Virgin Galactic SpaceShipTwo Untersuchung des Absturzes 01.11.2014
ምስል Reuters/Lucy Nicholson

እርግጥ ነው የሕዋ ጉዞ ብዙ ተግዳሮቶች ያሉበት ነው። ይሁን እንጂ የዘመናቱን ሕልም እውን ለማድረግ ሰዎችን ከመጣር አልገታቸውም ። እ ጎ አ ጥቅምት 4,1957 ሶብየት ሕብረት ባመጠቀቻት «ስፑትኒክ » በተሰኘችው ሰው ሠራሽ ሳቴላይት የተጀመረው የሕዋ ጉዞ እሽቅድድምና ምርምር ፣ 57 ዓመት ሆኖታል። በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ፤ ብርቱ ፉክክር የታየበት የጠፈር ጉዞ፤ በሶቭየት ሕብረትና በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥታት በተለይም በጦር ኃይሎቻቸው ከፍ ወደ አለ ደረጃ ተሸጋግሮ ነበር። ከስኬትና ድቀትም ጋር ወጪው እየበዛ በመምጣቱ ፤ ባለፉት 20 ዓመታት ገደማ በተለይ ሁለቱ የሕዋ ጉዞ ጀማሪ መንግሥታት ውድድሩን ሲያረግቡ ፤ የግል ኩባንያዎች ተተክተዋል። እርግጥ ነው የቻይናና የህንድ መንግሥታት ለሕዋ ጉዞ አሁንም ትልቅ ትርጉም የሰጡ ነው የሚመስሉት።

በቀጥታ በመንግሥታት ቁጥጥር ሥር ተመራ በግል ኩባንያዎች፤ የሕዋ ጉዞ እጅግ ውድና በሥነ ቴክኒክም ረገድ አስቸጋሪ ነው። ስለሆነም፣ ወደ ሕዋ መንኮራኩር ማምጠቅ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን፤ በጠፈርተኞች ፤ በሕዋ ምርምር ሠራተኞች ፤ በመንኮራኩሮችም ላይ ወደ 20 የሚጠጉ ብርቱና ቀላል አደጋዎች መድረሳቸው ነው የሚነገረው። አደጋዎቹ ፤ በጠፈር ብቻ ሳይሆን ፤ በመንኮራኩር ማምጠቂያ ጣቢያዎች እንበል በሩሲያው ፤ ባይኖኩር በዩናይትድ ስቴትሱ ኬፕ ካነርቫል በኮሩ ፈረንሳይ ጋያን ና በመሳሰሉም ያጋጠመበት ጊዜ ነበረ። አሁንም ፈጽሞ አልተወገደም።

የቨርጅን ጋላክቲክ ፤ ስፔስሺፕ ቱ» መንኮራኩር ፣ አደጋ ያጋጠመው ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የማጓጓዣና የደህንነት ቦርድ እንደገመተው፤ መንኮራኩሩ ከምድር ከባቢ አየር ውጪ ስበት ወደሌለበት የሕዋ ክፍል ሲገባና ሲመለስ ምጥቀቱን የሚቆጣጠረው የሞተር ክፍል እንከን አጋጥሞት በመሰባበሩ ሳይሆን አልቀረም። ይሁንና መቶ በመቶ እርግጠኛ ባለመሆኑ የመንኮራኩሩን ቅርጽና አሠራርም እንደሚመረምር ነው ያስታወቀው።

የሕዋን ጉዞ አስተማማኝ ለማድረግ፣ እ ጎ አ ሚያዝያ 16 ቀን 2004 ዓ ም በኖርድቫይክ ፤ ኔደርላንድ የተመሠረተውና ዐቢይ ግምት በመስጠት የሚመክረው ዓለም አቀፍ ድርጅት (International Association for the Advancement of Space Safety) በደሕንነት ረገድ «የስፔስሺፕ ቱ » አያያዝ እንዳላረካው ከመጀመሪያው አስጠንቅቆ እንደነበረ ገልጿል። በተጠቀሰው ድርጅት ፣ የአምጣቂ ሮኬት ኃይል ጉዳይ ባለሙያ የሆኑት ካሮሊን ካምፕቤል ፣ የቨርጂን ጋላክቲክ ኩባንያ ኀላፊዎችን ፣ «የሮኬቱ ሞተር አደገኛ ነው» በማለት አስጠንቅቄአቸው ነበር ብለዋል። ካምፔል ይህን ማስጠንቀቂያ ያቀረቡት እ ጎ አ በ 2007 የቨርጂን ጋላክቲክ የሮኬት ሞተር ፈንድቶ 3 ኢንጂኔሮች ሕይወታቸውን ካጡ በኋላ እንደነበረ ገልጸዋል።

Space Shuttle Discovery vor dem Start Besatzung
ምስል AP

እ ጎ አ በ 2009 መንኮራኩር አምጣቂ የሮኬት ኃይል ከፍተኛ አደጋ እንዳለበት፣ በኔደርላንድ ለሚገኘው ድርጅትና በቨርጅን ጋላክቲክ ለሚገኙ ሰዎች በሳይንሳዊ ምርምር የተደገፈ የማስጠንቀቂያ ጽሑፍ አቅርበው እንደነበረ የገለጡት ካሮሊን ካምፕቤል ፣ ሰሚ ጠፋ ፣ ማስጠንቀቂያዬ ችላ ተባለ ሲሉ፣ ለዜና አውታሮች አስረድተዋል ። እርሳቸው በምሬት እንደገለጡት ከሆነ በጽሑፍ ብቻ ሳይሆን፤ በተለያዩ ጊዜያት ባደረጉአቸው የስልክ ጭውውቶችም፤ መንኮራኩር አምጣቂው የሮኬት ሞተር አስተማማኝ አለመሆኑን አስጠንቅቀው ነበር።

ሪቸርድ ብራንሰን ግን፤ «

የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የማጓጓዣና የደህንነት ጉዳይ ቦርድ፣ በምርመራ አጣርቶ የበኩሉን ማብራሪያ ከማቅረቡ በፊት ፣ የሆነ ያልሆነ የሚናገሩ ሰዎች ፤ አቀራረባቸው ከሞላ ጎደል ኀላፊነት የጎደለው መሆኑ ይሰማኛል» ነው ያሉት።

የመገናኛና የመረጃ ሳቴላይቶችንም ሆነ የሕዋ ምርምር የሚያካኺዱ መንኮራኩሮች ማምጠቅን ፤ እንዲሁ የተለመደና ቀላል ተግባር አድርጎ መመልከት ከባድ ነው ፤ ምክንያቱም አንዳንድ ለአደጋ የሚዳርጉ ሳንኮች ፤ ከፍተሻም በኋላ ባልታሰበ ሁኔታ ሊያጋጥሙ ይችላሉና!

Neue Mannschaft zur Internationalen Raumstation gestartet
ምስል AP

ጨረቃና ማርስ ላይ ሰው ለማሥፈር ምኖትም ዓላማም ያለው ሰው፤ አደጋ ባይወገድም ፣ የሕዋ ጉዞን ርግፍ አድርጎ ይተዋል ብሎ ማሰብ ይከብዳል።

ሰው የማያውቀውን ለማወቅ ሰፊ ጉጉት ያለው ፍጡር ነው። የማያውቀውን ለማወቅ ሰፊ ጥረት ሲያደርግ ፤ ምናልበትም ሊገኝ የማይችለውን ለማግኘት ሲኳትን ፣ የተገኘውን በእጁ ያለውን የህልውናው መሠረተ የሆነችውን ፕላኔት ላለማጥፋት ፤ እንዲያውም ይበልጥ ለመንከባከብ የተቻለውን ሁሉ ቢያደርግ ይበልጥ እንደሚበጀው የሚያሳስቡና የሚመክሩ ብዙዎች ናቸው። የሚሰማቸው አልተገኘም እንጂ!

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ