1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሆንግ ኮንግ ፖሊስ የሰልፈኞችን ቦታ አስለቀቀ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 9 2007

ከመስከረም ወር አጋማሽ አንስቶ በቻይናዋራስ-ገዝግዛትሆንግኮንግ የተጀመረው የተቃዉሞ ሠልፍ እና አድማ አልተጠናቀቀም። አሁንም ሰልፈኞቹ የፋይናንስ ቦታዎችን ይዘው ይገኛሉ። ይሁንና ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ የሆንግ ኮንግ ፖሊስ የተወሰኑ ቦታዎችን ከሰልፈኞች አስለቅቋል።

https://p.dw.com/p/1DpN0
Räumung eines Protestlagers in Hongkong 18.11.2014
ምስል Reuters/T. Siu

በቻይናዋራስ-ገዝግዛትሆንግኮንግ ከ6 ሳምንታት በላይ የመንግሥት ፖሊሲ ተቃዋሚዎች ፤ በተለይም ተማሪዎች ሰፍረውበት የነበረው ቦታ ዛሬ በከፊል ነፃ ሲሆን ፤ በርካታ ጋዜጠኞች ተሰብስበው ፤ የሚፈራርሱትን አጥሮች ፎቶ ያነሱ ነበር። ይህም በአንድ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት፤ በከተማው የሚገኘው «ሲቲክ ታወር» የተባለው መስሪያ ቤት ህንፃ አካባቢ ለሰልፈኞች የተከበበው አጥር እንዲፈርስ በማዘዙ ነው። የተቀረው ቦታ ግን ቢያንስ ለግዜው እንዳለ አለ። ለዛም ሳይሆን አይቀርም ሰልፈኞቹ ድርጊቱን ብዙም ሲቃወሙ ያልተስተዋሉት። አንዳንዶች እንደውም ለዶይቸ ቬለ እንደገለፁት በፍቃደኝነት ነው ቦታውን ለቀው በመነሳት ላይ ያሉት፤« ይህ ንቅናቄያችንን አይለውጠውም። ቦታው ለእኛ ያን ያህል ወሳኝ አይደለም። ነገር ግን ሁሉንም ቦታ ለማስለቀቅ የሚሞክሩ ከሆነ ፤ ያኔ እንከላከላለን እና ለቀን አንሄድም። »

ትላለች ከሰልፈኞቹ አንዷ የሆነችው ተማሪ። በዩንቨርስቲ ተማሪዎች የተጀመረው አድማ ከፍተኛ አስጊ ዓመፅ ከታየበት ሰነበተ። በአደባባይ የሚታዩት ሰልፈኞች ቁጥር በ10ሺ መቆጠሩ ቀርቶ በመቶ ቤት ሆኗል። የተቃዋሚዎቹ የዲሞክራሲ ጥያቄም ከግብ ሳይደርስ ቀርቷል። የሆንግ ኮንግ መሪ ሊውንድ ቹን ይንግ ስልጣን ሊለቁ ፍፁም አያስቡም። የቤጂንግም አመራር ቢሆን ሙሉ ዲሞክራሲ እንዲኖር አልፈቀደም። ንቅናቄው አቅጣጫው ጠፍቶበታል ይላል፤ ሌላኛው የሆንግ ኮንግ የምጣኔ ሀብት ተማሪ «ሰዎች መሰልቸታቸው እውነት ነው። ነገር ግን አሁንም እዚህ ያለንበት ምክንያት ገዢው መንግሥት በጣም መጥፎ በመሆኑ እና ለሰዎች ምላሽ ባለመስጠቱ ነው። በእጃችን ምንም ነገር ሳንይዝ ደግሞ ዝም ብለን ልንተው አንችልም። መንገዱን ባዶ እስከሚያደርጉ ድረስ እዚህ እቆያለሁ።»

Räumung eines Protestlagers in Hongkong 18.11.2014
ምስል Reuters/T. Siu

መንግሥት ደግሞ ይህን እያደረገ አይደለም። ካደረገም እንደዛሬው በከፊል ነው። አንድ አዲስ ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ እንደውም 70 በመቶ የሚሆነው የሆንግ ኮንግ ነዋሪ፤ የዚህ የአደባባይ አድማ የሚያቆምበትን ቀን ይናፍቃል። እንደ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዳቪድ ስቫይግ ከሆነ የተቃውሞ አራማጆቹ ወሳኙን ጊዜ አልተጠቀሙበትም።« ዋናው ነጥብ ላይ ሲደርሱ እና ጫና ለማድረግ በቂ ሞራል በነበራቸው ጊዜ ገላጋይ ሀሳብ ላይ ለመድረስ ፍቃደኝነት አላሳዩም። ወይ ፍንክች ነበር ያሉት።እና ያ ደግሞ ንቅናቄውን አዳክሞታል።»

Räumung eines Protestlagers in Hongkong 18.11.2014
ምስል AFP/Getty Images/P. Lopez

በማለት ነው ስቫይግ የተቃዋሚዎቹን ዓመፅ የሚመለከቱት። ፖሊስ ቦታውን ነፃ እስኪያደርግ ተስፋ ያልቆረጡት የሆንግ ኮንግ ለውጥ ፈላጊዎች ለጊዜው ቁጥራቸው አናሳ ቢሆንም አደባባይ ይቆያሉ።

ማርኩስ ሪምለ / ልደት አበበ

ተክሌ የኋላ