1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሂትለር የአፍሪቃ እቅዶች

ሰኞ፣ ነሐሴ 26 2006

ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1933ዓ,ም እስከ 1945 ጀርመንን የገዛዉ አምባገነን መሪ አዶልፍ ሂትለር በመሠረተዉ ብሔራዊ ሶሻሊስት የሠራተኛ ፓርቲ በምሕፃሩ NSDAP አማካኝነት ከአካባቢዉ አልፎ ሌሎች ክፍለ ዓለማትንም የመቆጣጠር ህልም ይዞ ተንቀሳቅሷል።

https://p.dw.com/p/1D4rk
Zweiter Weltkrieg Nordafrika Deutschland Wüstenfuchs Erwin Rommel
ምስል Imago

በተለይ እሱ ስልጣን ላይ በወጣበት ወቅት ጀርመን ምንም የቅኝ ግዛት አፍሪቃ ዉስጥ ማጣቷ ሁሉን ለመቆጣጠር የሚመኘዉ መሪ በቀላሉ የሚቀበለዉ አልነበረም። ያንን እዉን ለማድረግም ነዉ «አፍሪቃን የመቀራመት» እቅድ ነድፎ ለመንቀሳቀስ የወሰነዉ። መነሻዉ የበላይነትን ማስከበር ብቻ ሳይሆን ጥሬ ሃብትን እንደልብ ለማግኘት ነበር። ግን ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ሲጀመር የእቅዱ የመጀመሪያዉ መጨረሻ ሆነ። ዘንድሮ 75ኛ ዓመቱ ይታሰባል።

አዶልፍ ሂትለር በጎርጎሪዮሳዊዉ 1933,ም በጥር ወር ወደስልጣን ሲመጣ ጀርመን በቅኝ ግዛትነት የያዘችዉ ሀገር አልነበረም። ታላቋ ብሪታንያና ፈረንሳይ ከአንደኛዉ የዓለም ጦርነት ድላቸዉ በኋላ በጀርመን ቅኝ ግዛት ሥር የነበሩትን ካሜሮን፤ ቶጎ፣ ታንዛንያ፣ ሩዋንዳን ቡሩንዲን ተከፋፍለዋልና። የቀድሞዋ ደቡብ ምዕራብ -ጀርመን ትባል የነበረዉ የዛሬዋ ናሚቢያም በደቡብ አፍሪቃ አስተዳደር ሥር ገብታለች። በወቅቱ ቅኝ ግዛቶቿን ላጣችዉ የጀርመን መሪ ሁኔታዎች ቀላል አልነበሩም። ለዚህም ነዉ ሂትለር ዕይታዉን ወደአዉሮጳ ያደረገዉ። ያኔ የሂትለር የመስፋፋት ርምጃዎች በቅድሚያ ያተኮሩት ወደፈረንሳይ እና ሶቭየት ኅብረት እንጂ አፍሪቃ ላይ አልነበሩም ይላሉ በበርሊን ሁምቦልት ዩኒቨርሲቲ የአፍሪቃ እና እስያ ተቋም የታሪክ ምሁር አንድሪያስ ኤከርት። እንደእሳቸዉ አፍሪቃ ለእሱ በጣም ሩቅ ነበር፤

Ehemalige Deutsche Kolonien in Afrika
የቀድሞ የጀርመን የቅኝ ግዛቶችምስል DW

«ለእሱ አፍሪቃ ዓለምን የመቆጣጠር ምኞቱ አካል አልነበረችም። ይልቁንም ለሂትለር ሌሎቹ አካባቢዎች ነበሩ ይበልጥ ቀርበዉ የታዩት። ሆኖም በእሱ አካባቢ የነበሩ ሰዎች አፍሪቃ ላይ ያላቸዉን ፍላጎት ተቃራኒም አልነበረም።»

በወቅቱ ከፍተኛ የፖለቲካ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ ፓለቲከኞች ቬርሳይ ፈረንሳይ ላይ የመጀመሪያዉን የዓለም ጦርነት የሚያበቃ ዉል ቢፈራረሙም፤ ሂትለር ስልጣን ላይ በወጣ በዓመቱ የእሱ ብሔራዊ ሶሻሊስት የሠራተኛ ፓርቲ የራሱን የቅኝ ግዛት ፖሊሲ ቀረጸ። እንደዉም ከጀርመን የተወሰዱ የቅኝ ግዛቶች እንዲመለሱለትም ሂትለር በግልፅ ጠየቀ። በዚያን ጊዜም ካሜሮናዊዉ ጸሐፊና የታሪክ ምሁር ልዑል ኩማ ናዱምቤ 3«ሂትለር ከአፍሪቃ ምን ይፈልጋልበተሰኘዉ መጽሐፋቸዉ ከኤኮኖሚ ጋ የተገናኙ ወሳኝ ነጥቦችን አነሱ። የተለያዩ ኩባንያዎች የጀርመን ባንክን ጨምሮ በቅኝነት ከሚያዙት የአፍሪቃ ሃገራት ብረታብረትም ሆነ ሌሎች ጥሬ ሃብቶችን የማግኘትና የመሸጥ ከፍተኛ ፍላጎትና ተስፋ ማሳደራቸዉ ይታይ ነበርና። ምንም እንኳን ጀርመን አፍሪቃ ዉስጥ የነበራት የቅኝ ገዢነት ስፍራዋ ከአንደኛዉ የዓለም ጦርነት በኋላ በሌሎች ቢተካም፤ በርካታ ጀርመኖች ግን ካሜሮን፣ ታንዛኒያ እንዲሁም ናሚቢያ ዉስጥ መኖራቸዉን ቀጠሉ። በእነዚህ አካባቢዎችም የሂትለር የብሔራዊ ሶሻሊስት የሠራተኛ ፓርቲ ቅርንጫፎች ነበሩ፤ ጦርነቱ ሲጀመር ግን እንደነበሩ አልቆዩም። እንዲያም ሆኖ አንድሪያስ ኤከርት እንደሚሉት የቀድሞ የጀርመንን የቅኝ ግዛቶች የማስመለስ ህልም የነበራቸዉ ወገኖች ነበሩ።

Galerie - Erwin Rommel
ምስል Getty Images

«በእነዚህ አካባቢዎች በሙሉ የጀርመን ብሔራዊ ሶሻሊስት የሠራተኛ ፓርቲ ማኅበራት ነበሩት። ጦርነቱ ሲጀመር ግን እንቅስቃሴያቸዉ ችግር ገጠመዉ ምክንያቱም አብዛኞቹ ጀርመናዉያን በጦር ግንባር በሚገኘዉ እስር ቤት ታጎሩ። እንዲያም ሆኖ በቀድሞ የቅኝ ግዛቶች ዉስጥ የነበረ የጥቂት ሰዎች ቡድን በአካባቢዉ የጀርመንን የተጠናከረ ይዞታ ለማምጣት ቁርጠኛ ነበር።»

ሃሳቡ በሃሳብና በምኞት ብቻ አልቀረም፤ በ1930ዎቹ ማለቂያም አዲሱ የቅኝ ግዛት ዉል እዉን ሆነ። ሂትለር ከፈረንሳይና ቤልጂየም ጋ ያካሄደዉ ዉጊያ በድል መጠናቀቁም አፍሪቃን የመቆጣጠር ፍላጎቱን እዉን ሊያደርጉ ከሚችሉ አጋጣሚዎች አንዱ ሆነ። ያ የቅኝ ግዛት ፖሊሲ የሚያራምድ ጽሕፈት ቤትም የመጀመሪያዉን የቅኝ ግዛት አስተዳደር ከአሁኗ ጊኒ እስከካሜሩን ባለዉ አካባቢ ዘረጋ። አካባቢዉን የሚያስተዳድረዉ በወቅቱ የዶቼ ባንክም ኃላፊ ነበር። የታሪክ ምሁሩ እቅዱ ተግባራዊ እንዲሆን የጊዜ ጥያቄ ብቻ መቅረቱን ነዉ የሚገልጹት።

«የጦርነቱ የመጀመሪያ ዓመት ለጦር ኃይሉ ብቻ ሳይሆን ለናዚ ከፍተኛ ዉጤት ያስገኙ በርካታ ድሎችን አምጥቷል። እነዚህን እቅዶች አፍሪቃ ዉስጥ ተግባራዊ ለማድረግም በእነሱ እይታ የቀረዉ የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነበር።»

በጎርጎሪዮሳዊዉ 1940,-ም የተጠቀሰዉ አካባቢ የጀርመን ሰፊ የቅኝ ግዛትና በተለይም የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብቶችን እንደልብ የምትጠቀምበት ስፍራ ሆነ።

Britischer Soldatenfriedhof in Tobruk in Lybien
ሊቢያ ዉስጥ የሚገኘዉ የብሪታንያ ወታደሮች መቃብር ሥፍራምስል picture-alliance/dpa

ናዚዎች ከዚህ በተጨማሪም ወደሕንድ ዉቅያኖስ አቅራቢያ ሌላ ስፍራም ለመቆጣጠር ተመኙ። ደቡብ አፍሪቃን ግን የነካ አልነበረም።ምክንያቱም በዚያን ጊዜ በሀገሪቱ የነበረዉ ዘረኛ የፓርታይድ መንግሥት አፍሪቃን ለመቆጣጠር ጀርመንን እንደአማራጭ ተጓዳኝ ይዞ ነበር። ምንም እንኳን አፍሪቃን የመቆጣጠር እቅዱ በወረቀት ላይ የሰፈረ ቢሆንም የታለመዉ እዉን ሳይሆን ብዙ ለዉጦች ተከሰቱ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 1941 የኢጣሊያን ቅኝ ገዢ ጦርን እንዲረዱ 45 ሺህ የጀርመን ወታደሮች ወደሊቢያና ግብፅ ተላኩ። በወቅቱ የተካሄደዉ ዉጊያ ግን ለቅኝ ገዢዉ ኃይል ድል ያስገኘ አልነበረም። እንደዉም ሂትለር ጥሬ ሃብቶችን ለማግኘት ያካሄደዉ ፍልሚያ ሆነ።ያኔም ከሊቢያ ነዳጅ ዘይት እንደልቧ ታገኝ የነበረዉን የተቀናቃኙን የብሪታንያን ጥቅም አደናቀፈ። በወቅቱ ሰሜን አፍሪቃ ዉስጥ የነበረዉ የጀርመን ጦር የአፍሪቃ እዝ ከባላጋራዉ ከብሪታኒያ ኃይል አንፃር ሲታይ በጣም አናሳ ነበር። ከሁለት ዓመታት በኋላም ሂትለር በምሥራቅ አዉሮጳ በተለይም ከሶቪየት ኅብረት በኩል የተጠናከረ ጦርነት ዉስጥ ሲገባ አፍሪቃን የመቆጣጠር ህልሙ እዉን ላይሆን ተበተነ። ዉጊያዉ ተጠናክሮ መላ ኃይሉን ስለወሰደም በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር በ1943 በየካቲት ወር ከላይ በመጣ መንግሥታዊ ትዕዛዝ የቅኝ ግዛት ፖሊሲዉ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት ፈረሰ። በወቅwt ሩሲያ ስታሊን ግራድ ላይ ጀርመንን ያሸነፈችበትን የድል በዓልና ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ያከተመበትን ልታከብር ዝግጅቷን አጠናቃለች።

ፊሊፕ ዛንድነር/ ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ