1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኬንያ የአሸባሪዎች ጥቃትን የመቋቋም ጥረቷ

ሰኞ፣ መጋቢት 21 2007

ኬንያ እና ሶማልያን በሚያዋስነው ረጅም እና ጥበቃው ልል በሆነው ድንበር በኩል ብዙ ህዝብ፣ ስደተኞች እና ሚሊሺያ ሳይቀሩ በየጊዜው ወደ ኬንያ ይገባሉ። ይህ ካለ ቁጥጥር የሚደረገው ዝውውር ግን በቅርቡ ሊያበቃ እንደሚችል ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/1EyiF
Polizist in Mandera
ምስል picture-alliance/dpa

ምክንያቱም የኬንያ መንግሥት በዚሁ ጥበቃው ልል በሆነው የጋራ ድንበሩ ላይ አጥር ለመገንባት ዕቅድ እንዳለው ከጥቂት ቀናት በፊት አስታውቋል። በዚሁ እቅዱ ሀገሩን ከፅንፈኛው የአሸባብ ቡድን የሚሰነዘርባትን ጥቃት ለማከላከል እና ችግሩን ለማስወገድ እንደሚያስችለው ተስፋ አድርጓል። ለሀገሪቱ ፀጥታ ጥበቃ ኃላፊነቱን በተሸከመው የኬንያ ሀገር አስተዳደር ሚንስቴር ቃል አቀባይ ምዌንዳ ንጆካ እንዳስታወቁት፣ አጥሩን የመገንባቱ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው። እንዲያውም፣ በሰሜን ኬንያ ካለው እና ለሶማልያ ድንበር ቅርብ ከሆነው የማንዴራ አካባቢ የሚነሳው የአጥሩ ግንባታ ስራ ባለፈው ሰኞ መጀመሩን እና ይኸው 700 ኪሎሜትር የሚሸፍነው የመጀመሪያ ደረጃ የግንባታ ስራ የአውሮጳውያኑ 2015 ዓም ሳያበቃ በፊት እንደሚጠናቀቅ የላሙ ግዛት ኃላፊ ኢሳቲ ማሚን በመጥቀስ አመልክተዋል። በሁለተኛ ደረጃ ሌላ 900 ኪሎሜትር የሚሸፍን የአጥር ግንባታ ሊቀጥል እንደሚችልም ነው ቃል አቀባዩ ንጆካ ያስረዱት።

Infografik Al-Shabab Terroranschläge mit Todesopfern in Kenia 2014 Deutsch

የግንብ አጥር መስራቱ ግን የአሸባብን ጥቃት ለመከላከል መፍትሔ መሆኑን የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኝኤማኔዌል ኪሳንጋኒ ይጠራጠሩታል።

« ችግሩ የኬንያ ሶማሊያ ድንበር አይደለም ፣ ምክንያቱም አንዳንዶቹ አሸባሪዎች በዩጋንዳ በኩል ወደ ኬንያ እንደገቡ ነው የተሰማው። ስለዚህ የግንቡን አጥር በመስራት ብቻ በሀሪቱን ፀጥታ ማስጠበቅ ይቻላል ብዬ አላስብም። »

ያካባቢ ሀገራት በተለያዩ ደረጃ ለመቀራረብ እና የኤኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ውህደት ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ ባለበት ባሁኑ ጊዜ ይህን ዓይነት አጥር የመገንባቱን እቅድ የፖለቲካ ተንታኞች አከራካሪ ሆኖ አግኝተውታል። ኤማኑዌል ኪሳንጋኒም ከአጥሩ ግንባታ ይልቅ ድንበር ሩን የሚጠብቁ ወታደሮች ማሰማራቱ ይሻላል ባይ ናቸው።

« ኢትዮጵያ ያደረገችውን መመልከት ይቻላል። ከሶማልያ ጋ በሚያዋስነው ድንበሯ ላይ ጦሯን አሠማርታለች። እና ለኬንያም ጥሩ ይሆን የነበረው የአፍሪቃ ህብረትን በመጠየቅ ጦሯን ከሶማልያ ጋ ባለው የጋራ ድንበር ላይ መሠማራት ነበር። »

ይሁንና፣ ብዙ ኬንያውያን በሀገራቸው እና በሶማልያ ድንበር ላይ መንግሥታቸው የግንብ አጥር ለመስራት የያዘውን እቅድ ፣ ልክ እስራኤል ከራስ ገዙ የፍልሥጤም አስተዳደር በሚለየው ድንበር ላይ የሰራችውን አጥር ወይም የግሪክ ቆጵሮስን ከቱርክ ቆጵሮስ የሚለየውን አጥር በምሳሌነት በመጥቀስ ትክክለኛ አድርገው እንደተመለከቱት ነው አንዳንድ የሀገሪቱ ጋዜጦች ያስታወቁት።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ