1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ካት «ዩሱፍ» ዳግም ወደ መድረክ

ሐሙስ፣ ኅዳር 18 2007

በ 70 ዎቹ ዓመታት በፖፕ ሙዚቃ ጥበቡ፣ በዓለም የሙዚቃ መድረክ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈዉና የስልምና ሐይማኖትን በመቀበሉ የሚታወቀዉ ምዕራባዊዉ ዝነኛ ሙዚቀኛ በጀርመን የሙዚቃ መድረክ ዳግም ብቅ ሊል መሆኑ ከተገለፀ በኋላ የብዙሃን መገናኛን ቀልብ ስቦ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/1DvTg
Cat Stevens
ዩሱፍ ኢስላም የቀድሞዉ ካት ስቲቨንስምስል picture-alliance/dpa/C. ONORATI

በሙዚቃ የጀመረዉ የዕለቱ መሰናዶአችን፤ የዓለም የሙዚቃ መድረክን ከሃያ ዓመታት በላይ የተለየዉ ካት ስቲቨንስ ወይም ዩሱፋ ኢስላም ዳግም ወደ ሙዚቃዉ ዓለም መምጣትን ያስተነትናል፤
በዓለም ዙርያ በፖፕ ሙዚቃ ቅላጼዉ በ 70ዎቹ የጎርጎረሳዊ ዓመታት ዝናንን ያተረፈዉ ካት ስቴቨንስ ዩኤስ አሜሪካ ካሊፎርኒያ ማሊቡ ባህር ዳርቻ ዋና ሲዋኝ ሳለ ድንገት ማዕበል ተነስቶ መፍቴ አልባ ሆኖ ማዕበሉ ወዲህ ወድያ ሲያንገላታዉ፤ ከባህሩ ለመዉጣት ትግሉን አልቻለዉ ይናገራል። ታድያ ከፍተኛ አደጋ ዉስጥ ሳላ በድንገት ፀሎትን የጀመረዉ ካት ስቲቨንስ፤ ከማዕበሉ አደጋ ከባህር ሲሳይ የጠበቀዉን አምላክ ህይወቱን ለመስጠት መወሰኑ ተዘግቧል። ካት ስቲቨንስ ባህር ላይ ሲዋኝ ያጋጠመዉ ከባድ ማዕበል እያንገላታ ዉቅያኖሱ ዳርቻ ከተፋዉ በኋላ ጊታሩን አስቀመጠ የሙዚቃ ዓለምንም ተሰናበተ። ከዝያን በኋላ ካት ሲቲቨንስ የስልምና ሐይማኖትን ተቀብሎ ዩሱፍ ኢስላም፤ ብሎ ራሱን ለመቀየር መወሰኑን መናገሩ ይታወሳል። እዉቁ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ካት ስቲቨንስ በ70ዎቹ ዓመታት በምዕራቡ ዓለም ከ 50 ሚሊዮን በላይ የሙዚቃ አልበምን ሸጥዋል። ካት ስቲቨንስ ከደረሰበት ከፍተኛ አደጋ ከዳነ በኋላ በጎርጎረሳዉያኑ 1979 ዓም የሙዚቃ መሳሪያዎቹን በሙሉ መሸጡና የሙዚቃ መድረክን መሰናበቱ ነዉ የተጠቀሰዉ።

ካት ስቲቨንስ በሚል የመድረክ መጠርያዉ የሚታወቀዉ እዉቁ እንግሊዛዊ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ስቴቨን ዲሚትሪ ጊዎርዲዉ ከቆጵሮሳዊዉ አባቱ እና ከስዊድናዊ እናቱ ብሪታንያ መዲና የለንደን ዉስጥ ነዉ የተወለደዉ። ካት ስቴቨንስ በጎርጎረሳዉያኑ 1967 ዓ,ም፤ የ 19 ዓመት ወጣት ሳለ Matthew & Son የተሰኘዉ የመጀመርያ የሙዚቃ አልበሙን በዓለም የሙዚቃ መድረክ እንዳቀረበ በጥቂት ቀናት ዉስጥ በትዉልድ ሀገሩ በብሪታንያ በምርጥ ሙዚቃ አልበም መዘርዝር ሰባተኛ ደረጃን በመያዝ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አተረፈ። ለሁለተኛ ግዜ የሰራዉ "New Masters" በሚል መጠርያ በሚታወቀዉ የሙዚቃ አልብም ግን እንደ መጀመርያዉ የሙዚቃ ስብስቡ እንብዛም በሽያጭ ወደረን አላገኝም፤ ተወዳጅነቱም እንብዛም ነበር። ካት ስቲቨንስ ሁለተኛ የሙዚቃ አልበሙን ባወጣ ከጥቂት ግዝያት በኋላ በሳንባ በሽታ ህመም በመያዙ አልጋ ላይ ዋለና ገና እያበበ የነበረዉ የሙዚቃ ዓለም ሞያዉ ከሰመ፤ እንድያም ሆኖ ካት ስቴቨንስ በሽታዉን እያስታመመ አልጋዉ ላይ ሆኖ የሙዚቃ ግጥምን እንዲሁም ዜማ መድረስን አልታከተም። ካት ስቲቨንስ በሳንባ በሽታ የአልጋ ቁራኛ በሆነበ ዘመን ወደ 40 የሙዚቃ ግዝጥችን እና ዜማን መድረሱም ተዘግቦለታል።
ካት ስቲቨንስ የሳንባ በሽታዉን ሲያስታምም አልጋዉ ላይ ሆኖ የሙዚቃ ግጥምን ሲጽፍ፤ በአንድ አኩስቲክ ጊታር ሙዚቃን ሲደርስ ቆየ ። ታድያ ይህ በርጋታ የፃፈዉ ግጥምና ዜማ ለሌላ ለታዋቂነትና ለተወዳጅነት መድረክ መንገድን ጠረገለት። ለዚህም በዓለም እጅግ ተወዳጅነትና ተደናቂነት ያተረፉት "Wild World","Morning has Broken" ወይም "Father and Son" የተሰኙት የሙዚቃ ስራዎቹ ተጠቃሽ ናቸዉ። እነዚሁ ስራዎቹ ናቸዉ በካት ስቴቨንስን የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ እንዲባል ያበቁትም። ለአስር ዓመታት የፖፕ ሙዚቃ መድረክን በመሪነት የያዘዉ ካት ስቴቨንስ በዩኤስ አሜሪካ ካሌፎርንያ ግዛት ማሌቡ ባህር ዳርቻ፤ በጎርጎረሳዉያኑ 1975 ዓ,ም ከከባድ ማዕበል አደጋ በማምለጡ የእግዜር ፈቃድ ሆኖ ድኛለሁ ማለቱና በጎርጎረሳዉያኑ 1977 ዓ,ም የሙዚቃ ስራዉን ሁሉ ማብቃቱ ተገልፅዋል። ይህን የሙዚቃ ስራ ሊያበቃ አካባቢ ደግሞ ካት ስቴቨንስ ህይወቱ እጅግ በአዎንታዊ መንገድ የተቀየረዉ ወንድሙ ዴቪድ ጎርደን፤ ቅዱስ ቁራንን እንደሸለመዉ ይናገራል። ከዝያም ነዉ በጎርጎረሳዉያኑ 1978 ዓ,ም እዉቁ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ካት ስቲቨንስ የእስልምና ሐይማኖትን ተቀብሎ ስሙንም ቀይሮ ዩሱፍ ኢስላም በማል የጀመረዉ። ካት ስቲቨንስ ስሙን እና ሐይማኖቱን ቀይሮ ብቻ አልቀረም፤ ዩሱፍ ኢስላም በመባል ራሱን ደብቆ መኖርን ጀመረ። ከዝያም በለንደን አንድ የቁራን ትምህርት ቤትን ከፍቶ ከተመድ የማኅበራዊ ጉዳዮች ስራ ላይ መሳተፍን ጀመረ።
ዩሱፍ ኢስላም ራሱን ደብቆ ማኅበረሰባዊ ጉዳዮችን በመተግበር ሲኖር በጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር በ80ዎቹ መጨረሻ ስሙ በዓሉታዊ ሁኔታ በዓለም ርዕሰ ዜና በቀይ ቀለም ደምቆ ወጣ። ይኸዉም « The Satanic Verses» በሚል መፅሐፉ የሙስሊም ሐይማኖትን አንቋሻል በሚል በሙስሊም ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ነቀፊታን የቀሰቀሰዉ፤ ደራሲ ትዉልደ ህንዳዊዉ የእንጊሊዝ ዜጋ፤ ሳልማን ራሽድ ላይ ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ ደራሲዉን እንደ ወንጀለኛ አይቶአል በሚል፤ ወቀሳ ቀርቦበት ነዉ። በዝያን ወቅት የኢራኑ የሃይማኖት መሪ፤ ሃያቶላ ሆሚኒ ሳልማን ራሽድ በሚል መጠርያ የሚታወቀዉና «The Satanic Verses» የሚል መፅሐፍን ያሳተመዉ ትዉልደ ህንዳዊ የእንግሊዝ ዜጋ እስልምናን በማንቋሸሹ በተገኘበት እንዲገደል ትዕዛዝን አስተላልፈዉ ነበር። ታድያ የቀድሞዉ የፖፕ ሙዚቃ ንጉሱ ካት ስቲቨንስ ማለትም ዩሱፍ ኢስላም፤ በብሪታንያ ቴሌቭዥን ቀርቦ በሰጠዉ ቃለ ምልልስ ደራሲዉን በሞት እንዳይቀጣ ሳይሆን የሞት ቅጣት ለፈረዱበት ለኢራኑ የሃይማኖት መሪ ለሃያቶላ ሆሚኒ አሳልፊ እስጣለሁ ብሎ በመናገሩ ነበር፤ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ ስሙ በዓለም እለታዊ ርዕሰ ዜና ሆኖ ደምቆ የተነበበዉ።
ቆየት ብሎ ዩሱፍ ኢስላም በቃለ-ምልልሱ ጋዜጠኛዉ በጥምዝ ጥያቄን ጠይቆ ይህን እንዲናገር እንደገፋፋዉ ተናግሮ ለሰጠዉ ቃለ ምልልስ ማስተባበያ ሰጥቶ እንደነበርም ተዘግቦአል። በጎርጎረሳዉያኑ 1996 ዓ,ም « በርሊነር ዛይቱንግ » ለተሰኘዉ የጀርመን ጋዜጣ የቀድሞዉ የፖፕ የሙዚቃ ንጉስ ዩሱፍ ኢስላም በሰጠዉ ሌላ ቃለ ምልልስ ደግሞ በአክራሪ እና በለዘብተኛ የሃይማኖተኞች መካከል አጣብቂኝ ዉስጥ እንዳለ ተናግሮም ነበር። እስራኤል ቀደም ሲል የቀድሞዉን የፖፕ የሙዚቃ ንጉስ፤ ዩሱፍ ኢስላምን በፅፈኞች ተርታ አስቀምጣዉ እንደነበር እና ለፍልስጤሙ የሃማዝ ድርጅት የገንዘብ ርዳታን ስለሚያደርግም በጎርጎረሳዉያኑ 2000 ዓ,ም ወደ እስራኤል እንዳይገባ አግዳዉ እንደነበርም ይታወቃል።
ከሙዚቃ መድረክ ከወረደ ከ 20 ዓመታት በላይ የሆነዉ ዩሱፍ ኢስላም ከሚታወቅበት ከጊታሩና ከሙዚቃዉ ጋር ዳግም መድረክ ላይ ይመጣል ብሎ ያሰበ ማንም አልገመተም። ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት ቢሆንም ዩሱፍ ኢስላም ማለትም ካት ስቲቨንስ ጊታሩን ይዞ እንዲያ የዓለምን የፖፕ የሙዚቃ አፍቃሪ በጥሩ ቃናዉ እንዳላስደመመ ሁሉ ድንገት መድረኩን ጥሎ ወደ ሐይማኖት ይገባል ብሎም የገመተ አልነበረም። ስርነቀል ለዉጥ በማድረግ በጎርጎረሳዉያኑ 1979 ዓ,ም የሙዚቃ ህይወቱን እርግፍ አድርጎ የተወዉ የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ አሁንም ስርነቀል አለዉጥን አድርጎ ወደ ሙዚቃዉ ዓለም ይመለሳል ብሎ የገመተ አልነበረም። ታድያ የፖፕ ሙዚቃ ንጉሱ ዩሱፍ ኢስላም ወደ መድረክ ለመመለስ ምን አነሳስቶት ይሆን?
እንደ ዩሱፍ ኢስላም ለዚህ ሁኔታ ያበቃዉ አንድ ነገር ነዉ። በዩኤስ አሜሪካ በጎርጎረሳዊዉ 2011 ዓ,ም የአሸባሪዎች ጥቃት ከደረሰ በኃላ ፤ ይኸዉም ከጎርጎረሳዉያኑ መስከረም 11 ቀን፤ 2001 ዓ,ም ጀምሮ ጽንፈኝነትን በመራቅ ለዓለም ማኅበረሰብ ሁሉ ለሰላም በማቀንቀን ዳግም ወደ መድረክ ለመዉጣት መወሰኑን ይገልፃል። በርግጥ ዩሱፍ ኢስላም በጎርጎረሳዉያኑ 2003 ዓ,ም "Peace Train" የተሰኘዉን ስለሰላም የሚቀነቅንበትን ሙዚቃ በኔልሰን ማንዴላ መታሰብያ ድርጅት በተዘጋጀዉ ሥነ-ስርአት ላይ አቀንቅኖአል። የቀድሞዉ የፖፕ ሙዚቀኛ ዩሱፍ ኢስላም በርግጥ ወደ ሙዚቃዉ ዓለም ተመልሶ ለመምጣት ዉሳኔ ላይ ቶሎ እንዳልደረሰ ነዉ የተናገረዉ። እንደ ዩሱፍ ኢስላም «ተመልሼ በሙዚቃዉ መድረክ ላይ ለመዉጣት የማደርገዉ ርምጃ በርግጥ ትክክል ነዉ አይደለም ስል ሳስብ ጊዜን ወስዶብኛል» እንደኔ እምነት አሁን እጅግ ቀላል መልስ ያገኘሁ መስሎኛል፤ ይኸዉም ጥሩ የሆነ ነገር መስራት ሁልግዜም ጥሩ ነዉ መጥፎ ስራ ደግሞ መጥፎ ነገርን ያስከትላል» ሲል መናገሩ ተዘግቦአል።
ካት ስቲቨንስ እስልምናን ተቀብሎ ከመድረኩ ዓለም በይፋ ከተሰናበተ ወዲህ ሶስት የሙዚቃ አልብምን ማዉጣቱ ተዘግቧል። ባለፈዉ ጥቅምት ያሳተመዉ አልብሙ "Tell 'Em I'm Gone" ይሰኛል ዩሱፍ በቅርቡ ባሳተማቸዉ አዳዲስ የሙዚቃ አልብሞች ላይ ሁሉ ስሙን ዩሱፍ በደማቁ ፅፎ ጎኑ ላይ በአንድ መለጠፍያ ላይ ካት ስቴቨንስ ተብሎ የድሮ ስሙም ይነበባል። ዩሱፍ ኢስላም ከ1970 ዎቹ ዓመታት ስሙን ከመቀየሩ፤ ረዥም ጢሙ ከመሸበቱ እንዲሁም መነፅር ከማድረጉ በቀር ምንም የተቀየረዉ ነገር የለም። ድምፁም ሆነ የጊታር አጨዋወቱ ለመጀመርያ ግዜ በዓለም የፖፕ ሙዚቃ መድረክ ወጥቶ ሲያዜም የነበረዉ ተወዳጅነት እና ልዩ መስቡ ሁሉ አሁንም ቅንጣት አልተቀየረም።
በጀርመን በርካታ አፍቃሪዎች ያሉት የፖፕ ሙዚቃ ንጉሱ ዩሱፍ ኢስላም ወይም ካት ስቲቨንስ ካለፈዉ ሳምንት ሃሙስ ጀምሮ በጀርመን የተለያዩ ከተሞች የሙዚቃ ድግሱን እያሳየ ማሳየቱን ጀምሮአል።

አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ

Yusuf Islam in Bremen
ዩሱፍ ኢስላም የቀድሞዉ ካት ስቲቨንስምስል AP
Cat Stevens alias Yusuf Islam
ዩሱፍ ኢስላም የቀድሞዉ ካት ስቲቨንስምስል picture-alliance/Photoshot
Cat Stevens
ዩሱፍ ኢስላም የቀድሞዉ ካት ስቲቨንስምስል picture-alliance/AP Photo/A. Ibrahim
Cat Stevens 1971
ዩሱፍ ኢስላም የቀድሞዉ ካት ስቲቨንስምስል AP