1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኩፍኝን ለማጥፋት የገጠመ እንቅፋት

ማክሰኞ፣ ኅዳር 9 2007

ኩፍኝን ከዓለም ፈፅሞ ለማጥፋት የሚደረገዉ ጥረት መሻሻል አለማሳየቱን የዓለም የጤና ድርጅት ባለፈዉ ሳምንት ይፋ አድርጓል። በምክንያትነት ከተጠቀሱት የበሽታዉ ከሰዉ ወደሰዉ ፈጥኖ የመተላለፍ ባህሪ አንዱ ሲሆን የክትባት አለመዳረስም ሌላዉ ጉዳይ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1Doqf
Masernvirus
ምስል public domain

የሕፃናትን ነፍስ በአጭሩ ከሚቀጩ በሽታዎች ኩፍኝ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት መካከል ነዉ። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለዉ በየዕለቱ 400በየሰዓቱ ደግሞ 16 ነፍስ ይቀጥፋል። በተሐዋሲ አማካኝነት ከሰዉ ወደሰዉ በከፍተኛ ደረጃ በመተላለፉ የሚታወቀዉ ኩፍኝ ከባድ ከሚባሉ በሽታዎች አንዱ ነዉ። በትንፋሽና አየር እንዲሁም በቀጥታ ንክኪ ነዉ የሚተላለፈዉ። ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1980 በፊት መከላከያ ክትባት በስፋት ሳይዳረስ በየዓመቱ እስከ2,6 ሚሊዮን ነፍስ ይፈጅ እንደነበር የዓለም የጤና ድርጅት መረጃዎች ያመለክታሉ። አሁም ቢሆን ክትባት እያለም ኩፍኝ በዓለም ላይ ለሕፃናት ሞት ምክንያት ከሚሆኑትን በሽታዎች በዋናነት ይጠቀሳል። ለዓመታት ቀንሶ የቆየዉ በኩፍኝ ምክንያት የሚከሰት ሞት ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ወደ145,700 ከፍ ብሏል። ሟቾቹም አምስት ዓመት ያልሞላቸዉ ሕፃናት ናቸዉ። ክትባቱ ዉጤታማ መሆኑ ነዉ የሚነገረዉ። ለዚህ ማሳያዉም ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2000 እስከ 2013 ዓም በመላዉ ዓለም ክትባቱ የ15,6 ሚሊዮን ሕፃናትን ነፍስ ያለጊዜዉ ከመቀጠፍ አድኗል። ይህም ከዚህ ቀደም ከነበረዉ ጋ ሲነፃፀር በኩፍኝ ምክንያት የሚደርሰዉን ሞት በ75 በመቶ ቀንሶታል። የሟቾች ቁጥር በ2012 122 ሺህ ነበር በቀጣዩ ዓመት ግን ቀደም ብሎ እንደተገለጸዉ በ23 ገደማ ከፍ አለ። በወቅቱ ለጨመረዉ የሟች ቁጥር ቻይና፤ ኮንጎና ናይጀሪያ የተነሳዉ የኩፍኝ ወረርሽኝ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉ ነዉ የተነገረዉ። ይህ ያሳሰባቸዉ ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ ወገኖች ያደረጉት ጥናትም የክትባቱ በበቂ ሁኔታ አለመዳረስ ያስከተለዉ መዘዝ መሆኑን ያመለክታሉ። በኩፍኝ ምክንያት በዓለም ከሚደርሰዉ ሞት አብዛኛዉ ድሀ ሃገራት ዉስጥ እንደሆነ ያመለከተዉ ዘገባም በተለይ ሰፋ ያለዉን ድርሻ የሚወስዱት ናይጀሪያ፤ ፓኪስታን፣ ኢትዮጵያ ኢንዶኔዢያ፣ እና ዴሞክታሪክ ሪፑብሊክ ኮንጎ መሆናቸዉን ይዘረዝራል። ኢትዮጵያ የሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ትኩረት ከሰጠችባቸዉ ገዳይ በሽታዎች አንዱ ኩፍኝ መሆኑን ይገልጻሉ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የክትባት ዘርፍ አስተባባሪ ወ/ሮ ሊያ ወንድወሰን ። እሳቸዉ እንደሚሉትም ክትባቱ ዘጠኝ ወር ለሞላቸዉ ሕፃናት በቋሚነት እንዲሁም በዘመቻ ይሰጣል።

Entführung Ärzte ohne Grenzen Mitarbeiter in Darfur
የኩፍኝ ክትባት ዳርፉርምስል AP

ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በመላዉ ዓለም ከሚገኙ ሕፃናት 84 በመቶዉ የኩፍኝ ክትባት እንዳገኙ የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። ኢትዮጵያ ዉስጥ በየዓመቱ ለምን ያህል ሕፃናት ክትባቱ መሰጠቱን የሚያመለክት መረጃ ባላገኝም ወ/ሮ ሊያ የገለፁልኝ ክትባቱ በመላ ሀገሪቱ የሚዳረስበት ስልት መኖሩ ነዉ።

Somalia Flüchtlingslager in Mogadishu
ሶማሊያዊቱ ስደተኛ በኩፍኝ ከተያዘ ልጇ ጋምስል DW

ወ/ሮ ሊያ እንደገለፁት ክትባቱን በየጊዜዉ በመደበኛነት የመስጠቱ ተግባር የማይቋረጥ ነዉ። የመድሃኒት አቅርቦትም ቢሆን እጥረት የለም። የዓለም የጤና ድርጅትን የጠቀሰዉ ዘገባ ደግሞ ኩፍኝ ዛሬም ጉዳት ከሚያደርስባቸዉ ሃገራት ኢትዮጵያም ትገኝበታለች። ክትባቱ የሕፃናትን ሞት የሚቀንስ ነዉ የሚለዉን ሃሳብ ይዞ ክትባቱ እየተዳረሰ ከሆነ በኩፍኝ ሕይወቱ የሚያልፍ የለም ማለት ነዉ ወይ ላልኳቸዉ እንዲህ ይላሉ።

የሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ከሚሰጡ የክትባት አገልግሎቶች አንዱ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ነዉ። ልጆች ገና አንድ ዓመት ሳይሞላቸዉ ነዉ የኩፍኝ ክትባት መከተብ ያለባቸዉ። ያልተከተቡ ልጆች ለበሽታዉ የተጋለጡ መሆናቸዉን ነዉ የዓለም የጤና ድርጅት የሚያሳስበዉ። ያልተከተቡ ነፍሰ ጡር እናቶችም ለኩፍኝ በሽታ የተጋለጡ ናቸዉ እንደመረጃዉ። ተከትበዉ በሽታዉን የመቋቋም አቅም ያላዳበሩም እንዲሁ ከኩፍኝ አያመልጡም። ኩፍኝ አሁንም ባላደጉ ሃገራት በተለይም አፍሪቃ እስያ ዉስጥ ጉዳት ማድረሱን አላቆመም። አነስተኛ ዓመታዊ ገቢና ደካማ የጤና መሠረተ ልማት ያላቸዉ ሃገራት ኩፍኝ ከሚያደርሰዉ ሞት 95 በመቶዉን ይሸፍናሉ። በሽታዉ የሚያደርሰዉን ጉዳት ለመቀነስ ክትባቱ ተደጋግሞ ይሰጥ ይሆን?

በሽታዉን በክትባት አስቀድሞ ከመከላከል በቀር በኩፍኝ ለተያዘ ሕፃን የሚሰጥ ይኽ ነዉ የሚባል መድሃኒት አለመኖሩ ነዉ መረጃዎች የሚያመለክቱት። ይኽም ሆኖ አንዳንዶች ኩፍኝ ተይዘዉ በጥቂት ሳምንታት ዉስጥ የሚድኑበት አጋጣሚ አለ። በአብዛኛዉ ግን በተለይም በድህነት ህይወት የሚኖሩና በቂና የተመጣጠነ ምግብ ያላገኙ ሕፃናትን ባይገድል እንኳን የአይን ብርሃን ማሳጣትን ጨምሮ፤ ከባድ ትኩሳትና ጉንፋን መሰል ህመም፤ ኃይለኛ ተቅማጥ፣ የጆሮ ዉስጥ ቁስለት እና የሳንባ ምችን ሊያስከትልባቸዉ ይችላል።

Krankenpfleger China
የኩፍኝ ክትባት ቻይናምስል STR/AFP/Getty Images

ኩፍኝ የድሀ ሃገራት በተለይም የአፍሪቃና እስያ ከፍተኛ ችግር ነዉ ቢባልም አዉሮጳ ከዚህ ነፃናት ማለት አይቻለም። ጆርጂያ፣ ዩክሬንና ቱርክ ዉስጥም ወረርሽኙ ባለፈዉ ዓመት ተቀስቅሶ ነበር። በማስነጠስ፣ በሳል እንዲሁም በንክኪ እንደሚተላለፍ የሚነገርለት የኩፍኝ ተሐዋሲ በተለይ መከላከያ ክትባት ያልተከተቡ ሕፃናትን ለመያዝ ፈጣን መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ። ኩፍኝን ከዓለም ለማጥፋት ለተጀመረዉ ጥረት የበሽታዉ የመጋባት ኃይል ከፍተኛ መሆንና ደካማ እንደሆነ የተገለጸዉ ክትባት የማዳረስ እንቅስቃሴ እንቅፋት መሆኑ ተገልጿል። ኢትዮጵያ ዉስጥ የመድሃኒቱ አቅርቦት እንዴት ነዉ?

ለአንድ ጊዜ ለመከላከል የሚዉለዉ የኩፍኝ ክትባት አንድ ዶላር እንደሚያስወጣ ነዉ መረጃዎች የሚያመለክቱት። ያም ቢሆን ግን ይህ ነዉ የሚባል መድሃኒት የሌለዉና በፍጥነት ከሰዉ ወደሰዉ የሚተላለፈዉን ኩፍኝ በሽታ የመከላከያዉ ብቸኛ መንገድ ልጆችን በተገቢዉ እድሜ ማለትም ዘጠኝ ወር ሲሞላቸዉ ማስከተብ ነዉ። ከዛሬ 50ዓመት ገደማ አንስቶ ሥራ ላይ የዋለዉ የኩፍኝ ክትባት በዓለማችን ዉጤት ካሳዩና አምስት ዓመት ያልሞላቸዉን ልጆች ሕይወት ከመቀጠፍ እና ለተለያዩ ዉስብስብ የጤና ችግሮች ከመጋለጥ የሚያስጥል በመሆኑ ወላጆች ጊዜ ሳያባክኑ ለልጆቻቸዉ ጤና ሲሉ ሊወስዱት የሚገባ ቀዳሚ የጥንቃቄ ርምጃ መሆን ይኖርበታል። የመድሃኒቱ እጥረት ሀገር ዉስጥ አለመኖሩን ያመለከቱት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የክትባት ዘርፍ አስተባባሪ ወ/ሮ ሊያ ወንድወሰን መከላከል በሚቻል በሽታ የሚቀጠፈዉን የሕፃናት ሕይወት ለማዳን ክትባቱን ማዳረሱ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ያስገነዝባሉ።

Mädchen mit Masern
ኩፍኝ የያዛትምስል imago stock&people

የዓለም የጤና ድርጅት በአራተኛዉ የአምዓቱ የልማት ግብ ማለትም ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1990 እስከ 2015 ማለትም እስከመጪዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን ሞት በሁለት ሶስተኛ መቀነስ እቅድ ይዟል። ይህን ያሳካሉ ተብለዉ ከታሰቡት መካከል ለሕፃናት የኩፍኝ ክትባትን ማዳረስ አንደኛዉና ዋነኛዉ ነዉ። እንደየዓለም የጤና ድርጅትም የኩፍኝ ክትባትን በዓለም ለሚገኙ ሕፃናት ማዳረስ የልጆችን የጤና አገልግሎት የማስፋት አንዱ መንገድ ነዉ። ለሰጡን ማብራሪያ ወ/ሮ ሊያ ወንድወሰንን ከልብ እያመሰገንን በየትኛዉም አካባቢ የሚኖሩ ቢሆን ልጅዎን የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ማስከተብን ችላ አይበሉ የሚለዉን መልዕክት በማስተላለፍ ለምሽቱ ያልነዉን በዚሁ እናብቃ።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ