1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከፍተኛ የሐዘን መግለጫ ሰላማዊ ሰልፍ በሞስኮ

እሑድ፣ የካቲት 22 2007

70 ሽህ የሚሆን የሞስኮ ነዋሪ በክሬምሊኑ ቤተ-መንግሥት ላይ የሰላ ትችት በማቅረባቸዉ የሚታወቁት የሩስያ መንግሥት ዋንኛ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ቦሪስ ኔምትሶፍ ግድያን በተመለከተ ሐዘኑን በሰልፍ ገለፀ። የሩስያዋ ሁለተኛ ሰፊ ከተማ በሆነችዉ በሳንክት ፒተርስበርግም ቢያንስ 2500 ተቃዋሚ ሰልፈኞች አደባባይ በመዉጣት ሐዘናቸዉን ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/1EjTJ
Russland Trauermarsch zum Gedenken an Boris Nemzow am 01.03.2015
ምስል Picture-Alliance/dpa/S. Ilnitsky

ሰላማዊ ሰልፈኞቹ በተገዳዩ ምስል አጠገብ « ጀግኖች አይሞቱም » የሚል ፅሁፍ ጽፈዉና በከፍታ አንግበዉ ሐዘናቸዉን ጎዳና ላይ በመትመም ገልፀዋል። የ 55 ዓመቱ ፤የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ኔምትሶፍ የተገደሉት አንድ በማለፍ ላይ ከነበረ መኪና ውስጥ አራት ጊዜ ጀርባቸው ላይ ተተኩሶባቸው መሆኑም ተያይዞ ተጠቅሶአል። ከሩሲያ አንጋፋ የተቃዋሚ መሪዎች ተርታ የሚመደቡት ኔምትሶፍ በቭላድሚር ፑቲንና የዩክሬይኑን ጦርነት በተመለከተ ክሬምሊን ቤተ-መንግሥት ላይ የሰላ ትችት በማቅረባቸዉ ይታወቃሉ። ፑቲን ስለ ፖለቲከኛው ሞት፤ የተቀናበረ ግድያ መሆኑ አመላካች ነዉ ማለታቸውን ቃል አቀባያቸው መናገራቸዉን ተዘግቦአል። ከተቃዋሚዎች ስብሰባ ጥቂት ቀናት በፊት ከትናንት በስትያ ምሽት ሞስኮ ጎዳና ላይ ክሬምልን ቤተ- መንግሥት አቅራብያ የተገደሉት የሩስያዉ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ቦሪስ ኔምትሶፍ፤ ግድያዉን በተመለከተ የሩሲያ ከፍተኛ የምርመራ መሥሪያ ቤት ማረጋገጡ ይታወቃል።

የሩስያዉ ፖለቲከኛ በግፍ መገደል ከሩስያ ውጪ በዓለም ዙሪያ ብዙዎችን አስደንግጧል። ከአራት የምዕራብ ሀገራት መሪዎች እና ፖለቲከኞች የሀዘን መግለጫ በተጨማሪ፤ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ባን ጊሙን ድርጊቱን በጥብቅ በማውገዝ፤ በፍጥነት ጉዳዩ እንዲጣራ አሳስበዋል። የቀድሞው የሩስያ ምክትል ፕሬዚዳንት ቦሪስ ኔምትሶፍ ባልታወቀ ሰው ስለተገደሉበት ምክንያት እስካሁን በይፋ የታወቀ ነገር ግን የለም።

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ