1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከዶቼ ቬለ የመናገር ነፃነት ሽልማት

ረቡዕ፣ የካቲት 18 2007

የዶቸ ቨለ የዘንድሮው ሐሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ሽልማት ፤ በእሥራት ላይ ለሚገኘው ለስዑዲ ዐረቢያው የድረ ገጽ ዐምደኛ ለራይፍ ባዳዊ ተሰጠ።

https://p.dw.com/p/1Eh28
Österreich Raif Badawi Protest in Wien
ምስል picture alliance/APA/picturedesk.com

ለድረገጽ ጦማሪያን ሃሳብን የመግለፅ ተምሳሌት መሆኑ የተነገረለት በሳዉድ አረቢያ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዲከበር በሚጠይቁ መጣጥፎቹ ተፈርዶበት የታሠረዉ ራይፍ በደዊ የዶቼቬለን የመናገር ነፃነት ሽልማት አገኘ። ራይፍ በደዊ ፍርሃት ባልተጫናቸዉ መጣጥፎቹ ለዘብተኞች ሳዉዲ ዉስጥ ነፃነት እንዲኖራቸዉ ለዓመታት ሳይታክት ተሟግቷል። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012ዓ,ም እስልምናን ተዳፍረሃል የሚል ክስ ተመስርቶበት ባለፈዉ ዓመት ግንቦት የሳዉዲ ፍርድ ቤት 1,000 ግርፋት፤ የ10ዓመት እስራትና ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት በይኖበታል። ይህም ዓለማ አቀፋዊ ተቃዉሞን አስነስቷል።

Logo Deutsche Welle

ራይፍ በደዊ ለዓመታትም በሳዉዲ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ፍትህን እየጠቃቀሰ በድረገጽ ላይ ሲፅፍ ቆይቷል። የሃይማኖት ፖሊስ በሚባሉት ላይም ምፀታዊ መጣጥፎችን በተደጋጋሚ አቅርቧል። በሳዉዲ እንዳይከበር በሕግ ስለታገደዉ የፍቅረኛሞች ቀንም እንዲሁ። በመጀመሪያ ኤልክቶሪክ ገጽ በማቋቋምና በእስልምናን ላይ በመሳለቅ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2008 ዓ,ም ተከሰሰ። በዚህ ምክንያትም ለወራት ከሀገሩ ተሰደደ። ክሱ ሲነሳለት ወደሳዉዲ ተመልሶ መጻፉን ቀጠለ። በመቀጠል በ2009ዓ,ም የሳዉዲ መንግሥት ከሀገር እንዳይወጣ አገደዉ። በ2012ዓ,ም ባለስልጣናት አስረዉት ባለፈዉ ታህሳስ ነዉ ክስ የተመሰረተበት። የ10ዓመት እስራት ወደ200,000 ዩሮ እና ግርፋት ተፈረደበት።

ራይፍ ባዳዊ ሳዉድ አረቢያ ዉስጥ የሃሳብ ነፃነት እንዲከበር በሚጠይቁት በድረገጽ ባስተላለፋቸዉ መጣጥፎች ምክንያት ከእስሩና ከገንዘብ ቅጣቱ በተጨማሪ 1,000 ጊዜ እንዲገረፍ መወሰኑ ብዙዎችን አነጋግሯል እያነጋገረም ነዉ። ከምንም በላይ ባለፈዉ ጥር ወር የድረገጽ ጸሐፊዉ ሰዎች በተሰበሰቡበት የመጀመሪያዎቹ 50 ግርፋቶች ሲያርፉበት በስዉር በተንቀሳቃሽ ስልክ የተቀረጸዉ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ይፋ መደረጉ ትኩረትን ስቧል ዓለም አቀፍ ተቃዉሞም ቀስቅሷል። በርሊን ከሳዉዲ ኤምባሲ ፊት ለፊት በተካሄደዉ የተቃዉሞ ሰልፍ ራይፍ በደዊ እንዲፈታ ተጠይቋል። ዶቼ ቬለ ራይፍ ለመናገር መብት ባደረገዉ ተጋድሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ያደረገዉን የሃሳብ ነፃነት ሽልማት ሰጥቷል። የዶቼ ቬለ ሥራ አስኪያጅ ፒተር ሊምቡርግ ለድረገጽ ጸሐፊዉ ይህ ሽልማት የተሰጠበትን ምክንያት እንዲህ ያስረዳሉ፤

«በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ባሉባት ሳዉድ አረቢያ የራይፍ ባዳዊ በነፃነት ሃሳቡን ለመግለፅ መሞከር ትልቅ ድፍረት ነዉ። ይህ ደግሞ በእርግጥም ፅናት የሚጠይቅና አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚጠብቀዉ እያወቀ ለሃሳብ ነፃነት ለመቆም የቆረጠ ሰዉ መኖሩን ያመለክታል። እናም አሁን ራሱን ለዚህ አጋልጧል። ለዚህም ሽልማት የሚገባዉ ትክክለኛዉ ሰዉ መሆኑን አምናለሁ።»

Ensaf Haidar Frau vom Blogger Raif Badawi beim Protest in Montreal 13.01.2015
የራልፍ በደዊ ባለቤት ኢንሳፍ ሃይደርምስል picture alliance/empics

አያይዘዉም ሽልማቱ መላዉ ዓለም የሳዉዲ መንግሥት በሃሳብ ነፃነት እጦት ለእስር የዳረገዉን የድረገጽ ጸሐፊ እጣፈንታ በቅርበት እንዲከታተል እንደሚጋብዝም አመልክተዋል።

የራይፍ በደዊ ባለቤት ኢንሳፍ ሃይደር በታሠረበት ወቅት ነዉ ልጆቿን ይዛ ወደካናዳ የተሰደደችዉ። ዶቼ ቬለ ባለቤቷን መሸለሙን ስትሰማ የተሰማትን ደስታ ከገለጸች በኋላ፤ ይህ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ሽልማት ከፍተኛ ፖለቲካዊ አንድምታና መልዕክት እንዳለዉ አመልክታለች። በማያያዝም ሳዉዲ አረቢያ ሰብዓዊ መብቶችን በሚረግጠዉ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ በሰየመዉ ቡድን ላይ በተከፈተዉ ጦርነት የምትሳተፍ ሀገር ሆና ሳለም ለመብት የሚሟገተዉን ዜጋዋን ማሰሯንም አሳፋሪ ብላዋለች።

«ለእኔ የሳዉዲ መንግሥት አሁንም እሱን አስሮ በማቆየቱ ማፈሪያ ነዉ። ከታሠረ ዛሬ ሁለት ዓመት ከስምንት ወር ሆነዉ። በዚህ ወቅት በዉጭ ያሉ ሰዎች ለእርሱ አክብሮት ሲሰጡት እሱ 10 ዓመት ተፈርዶበት፤ ግርፊያና እስራቱን እየተቀበለ መገኘቱ ለሳዉድ አረቢያ አሳፋሪ ነዉ።»

ራይፍ በደዊ በተመሠረተበት ክስ የተፈረደበትን ግርፋት በየሳምንቱ ዓርብ 50 ለተከታታይ20 ቀናት እንዲገረፍ ነዉ የተበየነበት። አንድ ጊዜ ሾልኮ ከወጣዉ ቪዲዮ ሌላ ግን ከዚያ ወዲህ ስለግርፊያዉ በይፋ አልተሰማም። መረጃዎች እንደጠቆሙትን በህክምና ምክንያት በሚል ባለፉት ተከታታይ ዓርቦች ራይፍ ባዳዊ አልተገረፈም። ኢንሳፍ ሃይደር ይህ የሃሳብ ነጻነትን የሚያመለክተዉ ሽልማትም ሆነ ከመላዉ ዓለም በሳዉዲ መንግሥት ላይ የተሰነዘረዉ ትችትና ተቃዉሞ በሚያሳድረዉ ጫና ባለቤቷ ከእስር ይለቀቅ ይሆናል የሚል ተስፋ ነዉ ያላት። የዶቼ ቬለ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ሽልማት ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ ነዉ የተጀመረዉ። ዶቼ ቬለ በኢንተርኔት ለሚከናወን የመብት መሟገትም ሃሳብን የመግለጽ እንቅስቃሴዎች የሚሰጠዉ Z BOBS የተሰኘ ሽልማት አካል ነዉ። በሁለቱም የሽልማት ዘርፎች የተመረጡት ተሸላሚዎች በመጪዉ ሰኔ ወር አጋማሽ ቦን ከተማ ላይ ዶቼ ቬለ በሚያስተናግደዉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ ሽልማታቸዉን ይቀበላሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ