1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከአፍሪቃ የሚወጣዉ የተጭብረበረ ገንዘብ

ማክሰኞ፣ የካቲት 3 2007

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ1970-እስከ 2008 በተቆጠረዉ ሐምሳ- ዓመት ግድም ከኢትዮጵያ 16.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ዉጪ መዉጣቱን አንድ ጥናት ጠቆመ።ባለፉት አርባ-ስምት ዓመታት ከመላዉ አፍሪቃ ወደ ዉጪ የወጣዉ የተጭበረበረ ገንዘብ መጠን አንድ ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል።

https://p.dw.com/p/1EZEp
AU Gipfel in Adis Abeba Äthiopien 2015
ምስል DW/G. Tedla

አፍሪቃ ባለፉት 50 አመታት አንድ ትሪሊዮን ዶላር በተጭበረበረ መንገድ ማጣቷን በቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪ የሚመራ አጣሪ ቡድን ያወጣው ዘገባ ይፋ አድርጓል።በአፍሪቃ ህብረት እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪቃ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተቋቋመው ይህ አጣሪ ቡድን ባወጣው ዘገባ መሰረት ግዙፍ ኩባንያዎችና ግለሰቦች በህገ-ወጥ መንገድ በሚደረግ ያልተገባ ክፍያ፤ከገቢ ግብር በማጭበርበር፤ የህግ ማዕቀፎችን በመጣስ፤ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም እና የውጭ ምንዛሪን ባልተገባ መንገድ ከሀገር ሀገር እንዲዛወር አድረገዋል።

አህጉሪቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ1970-2008 ባሉት አመታት በህገ-ወጥ መንገድ አጣችው የተባለው የገንዘብ መጠን በእነዚሁ አመታት በእርዳታ ከተቀበለችው ጋር የሚስተካከል መሆኑን ሪፖርቱ ያትታል። የገንዘብ ዝውውሩ የመንግስት ባለስልጣናትን እና ተቆጣጣሪዎችን በጥቅም በመደለል፤ከአደንዥ እጽ ዝውውር እና የጦር መሳሪያ ንግድ ጋር የተገናኘ በመሆኑ በባህሪው ሚስጢራዊነት ምክንያት በቂ ማስረጃ ለማሰባሰብ መቸገሩን የገለጸው ዘገባ በአመት ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከአፍሪቃ በተጭበረበረ መንገድ እንደሚወጣ ያትታል።

Symbolbild Steuern Steuererklärung Steuerhinterziehung Geld Kriminalität
ምስል Fotolia/Andre Bonn

ይህ ዘገባ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ1970-2008 ባሉት አመታት ከፍተኛ ገንዘብ አጥተዋል የተባሉ አስር የአፍሪቃ ሃገራትን ዘርዝሯል። ከናይጄሪያ 217.7 ቢሊዮን ዶላር፤ከግብጽ 105.2 ቢሊዮን ዶላር፤ ከደቡብ አፍሪቃ 81.8 ቢሊዮን ዶላር፤ ከሞሮኮ 33.9 ቢሊዮን ዶላር፤ ከአንጎላ 29.5 ቢሊዮን ዶላር፤ከአልጄሪያ 26.1 ቢሊዮን ዶላር፤ከኮትዲቯር 21.6 ቢሊዮን ዶላር፤ከሱዳን 16.6 ቢሊዮን ዶላር፤ከኢትዮጵያ 16.5 ቢሊዮን ዶላር፤ ከኮንጎ ሪፐብሊክ 16.2 ቢሊዮን ዶላር ወደ አደጉት ሃገሮች ባንኮች በህገ-ወጥ መንገድ መወሰዱን ዘገባው አትቷል።

የነዳጅ ዘይት፤ ውድ ብረትና ማዕድናት፤የኤሌክትሪክ ማሽኖች እና ቁሳቁሶች፤ ፍራፍሬና አዝርዕት፤ነሀስ፤የብረታ ብረት፤ካካዋ፤አልባሳትና ጌጣጌጥ፤አሳና የባህር ውስጥ ምግቦች ግብይት አፍሪቃ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ያጣችባቸው ዘርፎች ናቸው ተብለው በዘገባው ተዘርዝረዋል።

ከፍተኛ የውጭ እርዳታ እና ብድር ከሚያገኙ ሃገሮች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ1970-2008 ባሉት አመታት 16.5 ቢሊዮን ዶላር ያጣችባቸው ዘርፎች በዚህ ዘገባ በግልጽ አልሰፈሩም።አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ የቦርድ ሊቀ-መንበር ዶ/ር ብርሃኑ አሰፋ «የተባለው ገንዘብ ያክል ነውይ? መረጃው ከየት ነው የተገኘው?» የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሳሉ። «ወጥቶ እንደሆነ ትልቅ ነገር ነው።» የሚሉት ዶ/ር ብርሃኑ «ማን ነው ያወጣው? እነ ማን ሃላፊነት ይወስዳሉ?» የሚሉ ተጨማሪ ጥያቄዎች መመለስ እንዳለባቸው ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ ወጣ የተባለው የገንዘብ መጠን ቀላል አለመሆኑን የሚናገሩት ባለሙያው «የመጠኑ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር መኖሩ የሚካድ ጉዳይ አይደለም።መንግስትንም ያሳሰበ ጉዳይ ነው።» በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ከደሃ የአፍሪቃ ሃገራት በግዙፍ ኩባንያዎች እና የግል ጥቅም ፈላጊ ግለሰቦች የሚወሰደው ገንዘብ መዳረሻ ዩ.ኤስ.አሜሪካ እና የግብር ገነት የሚባሉት የአውሮጳ ባንኮች መሆናቸውን በዘገባው ላይ አስተያየት የሰጡ ባለሙያዎች ይተቻሉ። ያደጉት ሃገራት ባንኮች እና የገንዘብ ተቋማት ገንዘቡን በድብቅ በማስቀመጥ እና በህገ-ወጥ ገንዘብ ዝውውሩ በመሳተፍ በሚያገኙት ትርፍ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው የአፍሪቃውያንን ሃብት ለግል ጥቅማቸው ያውላሉ ተብሏል። ዶ/ር ብርሃኑ አሰፋ ሚስጥራዊነትን የሚያበረታቱት የምዕራቡ ዓለም የገንዘብ ተቋማት ለችግሩ ተጠያቂ እንደሆኑ ይናገራሉ።

USA Schuldenkrise Dollar Flagge Fahne Finanzkrise Symbolbild
ምስል picture alliance/dpa

«ገንዘቡን የሚያስቀምጡት የአሜሪካና የአውሮፓ ባንኮች ናቸው።የራሳቸውን ገቢ ለማዳበር በሚስጥር መያዝን የሚያበረታቱ ባንኮች ናቸው። ይህንን በማየት ችግሩ ያለው ከምዕራባውያን የገንዘብ ተቋማት ነው ማለት ይቻላል።» የሚሉት ዶ/ር ብርሃኑ ችግሩን መቅረፍ ቀላል እንደማይሆንም ያስረዳሉ። እንደሳቸው አባባል «ፍላጎታቸው ህገ-ወጥ አገልግሎት ሰጥተው ብር መፍጠር እስከቻሉ ድረስ ችግር የለባቸውም።ይህ ባህል እስካጠናከርን ድረስ ይኸ ችግር በአጭር ጊዜ ይፈታል የሚል እምነት የለኝም።»

ከአፍሪቃ የሚወጣው ገንዘብ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ2000-2010 ዓ.ም. ባሉት አመታት ጭማሪ እያሳየ መሆኑን ዘገባው አትቷል።

ከአፍሪቃ በህገ-ወጥ መንገድ የሚወጣውን ገንዘብ ለማስቆም የአፍሪቃውያን መንግስታት እና አለም አቀፍ ተቋማት ትብብር ያስፈልጋል ተብሏል።

እሸቴ በቀለ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ