1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሶርያ እየሸሹ ወደ ቱርክ የሚገቡት ኩርዶች ቁጥር ጨመረ

ቅዳሜ፣ መስከረም 10 2007

በጄኔቭ የሚገኘዉ የተ.መ የስደተኞች ርዳታ ሰጭ ጉዳይ መሥርያ ቤት እንዳስታወቀዉ፤ በ24 ሰዓታት ዉስጥ ብቻ ወደ 70 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ጥገኝነት በመፈለግ ቦታዉ ላይ ደርሰዋል።

https://p.dw.com/p/1DGGt
Syrische Flüchtlinge an der Grenze zur Türkei bei Suruc 19.09.2014
ምስል Reuters

ለሽሽቱ በምክንያትነት የተጠቀሰው የአይ ኤስ ማለትም እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራዉ ቡድንን ለመዋጋት ሰሜን ሶርያ ውስጥ በሚወሰደው የጦር ርምጃ ነው። አንካራ ለስደተኞች ትናንት ድንበሯን በከፊል ክፍት አድርጋ ቆይታለች። በሌላ በኩል እስከ ቅዳሜ የኩርድ ወታደሮች ሰሜን ሶርያ ውስጥ ከአይ ኤስ ቡድን ጋር ባካሄዱት ጦርነት 18 የአይ ኤስ ወታደሮች መገደላቸውን ለንደን የሚገኝ አንድ የሶርያ ታዛቢ ቡድን አስታውቋል።

በሌላ ዜና ፅንፈኛ እስላማዊ ቡድን ብራስልስ በሚገኘዉ የአዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ላይ ጥቃት ለመጣል እቅድ እንደነበረዉ አንድ የኔዘርላን ቴሌቭዥን ጣብያ የዜና ምንጩን ሳይጠቅስ ዘገበ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጥቃት ሊያደርሱ ነበር ተብለዉ የተጠረጠሩ በርካታ ጎልማሶች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉ ተመልክቶአል። የግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር መዋል ተከትሎ የቤልጂየም መንግሥት ምንም አይነት ዝርዝር ሳይጠቅስ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ይፋ አድርጓል። ከዚህ ቀደም ብሎ የቤልጂየሙ የብዙሃን መገናኛ እራሱን እስላማዊ መንግሥት ሲል የሚጠራዉን ቡድን በሚወግኑ፤ ከሶርያ ከተመለሱ ግለሰቦች ሊደርስ የነበረዉን ጥቃት በደህንነት ጉዳይ መስርያ ቤት መክሸፉን ዘግቦ ነበር። እንደ ዘገባዉ የከሸፈዉ ጥቃት ከዚህ ቀደም ብራስል በሚገኝ አንድ የአይሁድ ቤተ- መዘክር ላይ እንደደረሰዉ አይነት ጥቃት እንደነበር ተመልክቶአል። በዚያን ጊዜዉ ጥቃት አራት ሰዎች መገደላቸዉ ይታወሳል።
በሌላ በኩል በኢራቅና ከፊል ሶሪያ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘውን ታጣቂ ኃይል፤ ደግፈዋል የተባሉ 3 የበርሊን ኑዋሪዎች ተከሰሱ። ዋና ተከሳሽ ፣ ካሮሊና ኤር በመባል የታወቁ የጀርመንና የፖላንድ ዜግነት ያላቸው የ 25 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወጣት ሴት ሲሆኑ እርሳቸውም ፤ አንዱን የተጠቀሰውን አካራሪ ቡድን አባል ያገቡ ሲሆን፤ በ 3ኛ ሰው ረዳትነት ለተዋጊው ቡድን 1,100 ዩውሮ የሚያወጡ ካሜራዎችና ለፕሮፖጋንዳ ቪዲዮ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ባለፈው ዓመት በጥቅምት እንዲቀርቡ አብቅተዋል ተብሏል።
ከዚያም ራሳቸው ሶሪያ ድረስ በመጓዝ፣ በተጨማሪ 3 ካሜራዎችንና 5,000 ዩውሮ መስጠታቸው በክሱ ሰነድ ላይ ተወስቷል። አምና በታኅሳስ ወር ሲመለሱም ተጨማሪ 6,000 ዩውሮ አሰባስበው መላካቸው ተገልጿል። ይህን ያደረጉት፣ አህመድ ሰዲቅ ኤም እና ጀኒፈር ቪንሴንዛ ኤም የተባሉ 2 የ 22 ዓመት ወጣቶች ባደረጉት ትብብር መሆኑ ተመልክቷል ሁለቱም በተጨማሪ ክስ ተመሥርቶባቸዋል።

Symbolbild Polizei in Belgien
ምስል AFP/Getty Images

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ