1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኦቶ ፎን ቢስማርክ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 29 2007

የጀርመን የመጀመሪያው መራኄ መንግሥት የኦቶ ፎን ቢስማርክ 200ኛ ዓመት የልደት በዓል ባለፈው ሳምንት ታስቧል ። ከ200 ዓመት በኋላ አሁንም ጀርመናውያን ስለ ቢስማርክ የሚሰጡት አስተያየት በሁለት የተከፈለ ነው ። ቢስማርክ ማንናቸው ?

https://p.dw.com/p/1F3kt
Otto Fürst von Bismarck
ምስል picture-alliance/dpa

ጀርመናውያን ሳያቅማሙ የማምለክ ያህል ለኚህ ሰው ትልቅ ክብር ይሰጧቸዋል ። በስማቸው ብዙ የታሪክ ማስታወሻዎች ተቀምጠውላቸዋል ። ሃውልት ተሠርቶላቸዋል መንገዶች ተሰይመውላቸዋል በስማቸው የሚጠሩ ማማዎች ቅርጾችና ሌሎችም ማስታወሻዎች በየከተሞች አሉ ፤ ለመጀመሪያው የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦቶ ፎን ቢስማርክ ።ቢስማርክ የተበታተኑ የጀርመን ግዛቶችን በማዋሃድ እጎአ ከ1871 እስከ 1890 ጀርመንን አንድ አድርገው ያስተዳደሩ የመጀመሪያው መሪ ናቸው ። የቢስማርክ 200ኛ ዓመት የልደት በዓል ባለፈው ሳምንት በብሔራዊ ደረጃ ታስቧል ።የጀርመን ተማሪዎች ቢስማርክ ጀርመንን አንድ ያደረጉ መሪ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን በ19 ዓመታት የንጉሣዊው ሥርዓት የሥልጣን ዘመናቸው በሃገራቸው አጠቃላይ የመመረጥና የመምረጥ መብትን ፣የማህበራዊ ዋስትና ስርዓትን የጤናና የአደጋ መድን እንዲሁም የጡረታ ዋስትናን ሥራ ላይ ያዋሉ እንደነበሩም ይማራሉ ። እንደ ብረት ጠንካራው መራኄ መንግሥት የሚል መጠሪያ የተሰጣቸው ቢስማርክ በ 25 ግዛቶች ተበታትና የነበረችውን ጀርመንን አንድ አድርገው እንደ ጎሮጎሮሳዊው አቆጣጠር ጥር 18 ፣1871 ነበር በአንድ ንጉሣዊ ግዛት እንድትተዳደር ያበቁት ። ቢስማርክ ከዚያ በፊት የፕረሺያ ጠ/ሚንስትር ነበሩ ። በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩዋት ፐረሽያ ዋና ከተማውን በርሊን አድርga ሰሜናዊ ጀርመንንንና የቀድሞዋን የምሥራቅ ጀርመን ግዛቶች እንዲሁም በስተደቡብ ምዕራብም የራይን ወንዝ የሚገኝባቸውን ግዛቶች እና በፖላንድ ሥር የነበሩ ግዛቶች ታጠቃልል ነበር ። የተለያዩትን የጀርመን ግዛቶች በማዋሃድ አንዲት ጀርመንን በመመስረታቸው ብቻ ሳይሆን በላቀ ዲፕሎማሲያዊ ብቃታቸው ስም ያተረፉት ቢስማርክ በጦር መሪነታቸውም ትልቅ ስፍራ ይሰጣቸዋል። ጀርመንን በአውሮፓ ለታላቅ የፖለቲካ ኃይልነት በማብቃት የሚወደሱት ቢስማርክ በአንጻሩ ሃገሪቱ የተለያዩ ጦርነቶችን እንድታካሂድ መንገዱን በመጥረግና የአውሮጳ ቅኝ ገዥዎች አፍሪቃን ለመቀራመት ያካሄዱትን የበርሊን ጉባኤ በማመቻቸት በእኩይነታቸው ወደር የማይገኝላቸው መሪ እየተባሉም ክፉኛ ይተቻሉ ። የዱስልዶርፍ ከተማው የታሪክ ምሁርና የቢስማርክ ግለ ታሪክ ፀሃፊ ክሪስቶፍ ኖን ፣ ቢስማርክ ለጀርመናውያን ትተውት ያለፉት ትሩፋት ሁለት ገፅታ ነው ያለው ይላሉ ።
« እርሳቸው አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ የጀርመን ብሔራዊ ታሪክ እንዴት ሊታይ እንደሚችል በማንፀባረቂያ መንፅርነት መቀመጥ ያለባቸው ናቸው ።ቢስማርክ ትንሽ የተጋነነ ታሪክ ይነገርላቸዋል ትልቅ ጀግና የንጉሣዊ ግዛት መስራች ፣ብቻቸውን የጀርመንንን አንድነት ከግብ ያደረሱ እየተባለ ይነገርላቸዋል ።ወይም ደግሞ እንደ ትልቅ እኩይ ፖለቲከኛ የዴሞክራሲንና የሊበራል ማለትም የነፃ አመለካከት አካሄድ እንዳይንሰራፋ አፍኖ ያስቆመ የገታ ሰው ሆነውም ይታያሉ »
ቢስማርክ ከዚህ ሌላ በሥልጣን ዘመናቸው በሶሻሊስቶች ላይ ይካሄድ ለነበረው ክትትል ፣ በ19ነኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ሊያድግ ላልቻለው የሃገሪቱ ምክር ቤት የአሰራር ባህል እንዲሁም ጀርመን በአፍሪቃ ና በእስያ ቅኝ ግዛቶችን እንድትይዝ በማድረግም ይወቀሳሉ ።
እነዚህን የመሳሰሉ ፍፁም የማይታረቁ አስተያየቶች የሚሰነዘሩባቸው ፣ ለ19 ዓመታት ጀርመንን የመሩት ቢስማርክ በፕረሽያ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ዘመን ፣ፐርሽያ እጎአ ከ1864 እስከ ከ1871 ከ ከዴንማርክ ከኦስትሪያና ከፈረንሳይ ጋር ሶስት ጦርነቶችን ጭራ ፣ሶስቱንም በአሸናፊነት አጠናቃለች ። ከነዚህ ድሎች በኋላ ነበር ቢስማርክ ተበጣጥሰው የነበሩትን የጀርመን ግዛቶች ወደ አንድነት በማምጣት ሃገሪቱ ኃይል አውሮፓዊት ሃገር እንድትሆን ለማድረግ የበቁት።ቢስማርክ አንድነቱ ሊመጣ የቻለው በብረትና ለጦርነቱ በፈሰሰው ደም መሆኑን በወቅቱ አስረድተዋል ። የታሪክ ምሁሩ Bismarck Preuße und sein Jahrhundert ቢስማርክ ፕረሽያና ዘመናቸው የተባለው መፀሀፍ ደራሲ
ክርስቶፍ ኖን እንደሚሉት አንዲት ጀርመንን የመመሥረቱ ሂደት በቢስማርክ ብቻ የተከናወነ አይደለም ። አንድነትን የማምጣቱ ታሪክ ለቢስማርክ ብቻ የተሰጠ ቢመስልም ሌሎችም በሂደቱ የበኩላቸውን ሚና እንደተጫወቱ ኖን ያስረዳሉ ።
« በዚህ ረዥምና ውስብስ ሂደት ከጀርመን ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጭም ብዙ ተዋናዮች ነበሩ ።አደረጉም አላደረጉ በዚያ ጊዜ የታየ ነገ,ር ቢኖር የጀርመንን ውህደትና አንድነት ለማደናቀፍ የተደረገ ነገር ግን የለም ። በርግጥ እዚህ ላይ የቢስማርክ ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ። ያም ሆኖ ከብዙዎቹ በዚህ ድርሻ ከነበራቸው መካከል አንዱ ነበሩ ።ስለሆነም እርሳቸው የጀርመን ንጉሳዊ ግዛት አንድነት መሥራች ብሎ ውዳሴውንን ለርሳቸው ብቻ ማሸከሙ ትክክል አይሆንም ። ምክንያቱም ርሳቸው ብቻቸውን ያከናወኑት ነገር አይደለምና ና »
ከዚህ ሌላ ኖን እንደሚሉት የተበታተነችውን ጀርመን አዋህደው ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ጠንካራ የተባበረች ጀርመን ከመመስረትዋ በፊት ለተካሄዱ 3 ጦርነቶች ሃላፊነቱን የሚወስዱት ቢስማርክ ብቻ አይደሉም ።እንዲውም ቢስማርክ ራሳቸው ከጦር ኃይሉ የመጡም ሆነ ጠብ ጫሪ አልነበሩም ። በአመዛኙ ውዝግቦችን በድርድር ለመፍታት ነበር የሚጥሩት ይላሉ ። ሌላው የበርሊኑ ነፃ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁር አርንድባወር ኬምፐር ከኖን አስተያየት ጋር የሚመሳሰል ሃሳብ ነው ያላቸው ።ሆኖም ከጀርመን ንጉሳዊ ግዛት ምስረታ በኋላ ቢስማርክ ስልታቸውን ቀይረዋል ይላሉ ።ይህም በርሳቸው አባባል ቢስማርክ በ1890 ባሳተሙት መፀሃፋቸው ላይ ተጠቅሷል ።
« ቢስማርክ የጀርመን ንጉሳዊ ግዛቶችን በማዋሃድ ከተደመደመ በኋላ ራሳቸውን በመጠኑም ቢሆን የጦር ፊት አውራሪ መራሄ መንግሥት አድርገው መመልከታቸው አልቀረም ። የሚያስታውሷቸውን ጉዳዮችና ትዝታዎች ባሰፈሩበት ናበተወዳጅነቱ በብዛት በተሸጠው መፀሃፋቸው ላይ ራሳቸው እንዳሉትም ለሥልጣን ጉጉ የሆኑ ፖለቲከኛ ነበሩ ።»
ይሁንና ባወርኬምፐር እንዳሉት ለቢስማርክ ጦርነት የማካሄዱ መሠረታዊ ህጋዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።ሆኖም ኖንም ሆነ ባወር ኬምፐር እንደሚስማሙት የጀርመን ንጉሳዊ አስተዳደር ና መራሄ መንግስቱ ኦቶ ፎን ቢስማርክ ከጦርነቱ በኋላ የመሬት ይገባናል ጥያቄ ሳያነሱ ሚዛናዊ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን መከተልን ነበር የመረጡት ።ይህን ያደረጉትም የሃገሪቱ ትኩረት በኤኮኖሚ ልማት ላይ እንዲሆን ለማድረግ ነበር ። ሆኖም በቢስማርክ የሥልጣን ዘመን እርስ በርሱ የሚጣረስ ነገር መከሰቱ አልቀረም ።ቢስማርክ ያኔ ጀርመን ቅኝ ግዛት አያስፈልጋትም ብለው ደጋግመው ሲናገሩ እንደነበረው ቃላቸውን ጠብቀው አልዘለቁም ።በተደጋጋሚ የጀርመን ንጉሳዊ ግዛት በሌሎች አገራት ቅኝ ግዛት አያሻውም ይሉ ነበር ያም ሆኖ ንጉሳዊው አገዛዝ ከተመሰረተ በኋላ እንኳን 15 ዓመት ሳይሞላ እንኳን አፍሪቃ ና እስያ ውስጥ የሞግዚት ግዛቶች እንዲመሰረቱ ከማድረግ አልቦዘነም ። እንደገና ኖን
«ጉዳዩ ከቅኝ ግዛት ጋር የተያያዘ ብቻ አይደለም ። ቅኝ ግዛቶቹ በርሊን ላይ የተነሳው የሥልጣን ትግል ለማስቆም እንደ አንድ መንገድ ተደርገው ነበር የተወሰዱት ።
ወግ አጥባቂው ቢስማርክ ተቀናቃኞቻቸውን ለዘብተኛ አቋም ያላቸውን የፓርቲ አባላትና የእነርሱን ደጋፊ ና አልጋ ወራሹን ፍሪድሪሽን ማዳከም ይፈልጉ ነበር ። ለዘብተኞች በሰፊው ቅኝ ግዛት ከነበራት ከእንግሊዝ ጋር የጠበቀ ትስስር የነበራቸው ናቸው ። ኖን እንደሚሉት ከእንግሊዝ ጋር የነበረውን ትብብር ለማደናቀፍ ቢስማርክ በ1884 ና 1885 በበርሊን ጀርመን ቅኝ ግዛት ማስፋፋት ይኖርባታል በሚል ለዓመታት ሲነገር የነበረው ለጊዜው ችላ እንዲባል አደረጉ ። ሆኖም በ1885 ሁኔታዎች ተቀያየሩ ።
« ከዚያም በ1885 ለዘብተኞቹ በምርጫ ከተሸነፉ በኋላ በመንግሥት ፖለቲካ አመራር ተሰሚነት አልነበራቸውም እና ያኔም ከንጉሱ ከአጼ ቪልሄልም ሞት በኋላ አልጋወራሹ ከቢስማርክ ጎን እንደሚቆሙ ነገሩዋቸው ከዚያም ቢስማርክ ቅኝ ግዛት የማስፋፋቱን ፖለቲካ እንዲቆም አደረገ »
ቢስማርክ አንዲት ጀርመንን በመመሥረታቸው ብቻ ሳይሆን እ ጎ አ ከ 1871 -1890 በመራኄ-መንግሥትነት ሲሠሩ የምርጫ መብትን በማስተዋወቃቸው ፤ በዲፕሎማሲ ታላቅ ችሎታቸውና በአስተዋይነታቸውም የሚደነቁ መሪ እንደነበሩ የታሪክ ምሁሩ ባወርኬምፐር ያስረዳሉ ።
« በመሃል ከአካባቢው ጠንከር ብሎ የሚወጣ ኃያል መንግሥት ለመመስረት ጠንካራ ፍላጎት የነበራቸው ናቸው ግን ያም ሆኖ በሥልጣን ለመቆየት የሚያሰላስሉ ፖለቲከኛ እንደነበሩም አይዘነጋም ።ይሁንና በአፍሪቃና በእስያ ቅኝ ግዛት ለማስፋፋት ይደረግ በነበረው ጥረት ግን በጣም ጥንቁቅ ነበሩ ። ከሌሎቹ የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት ጋር በዚህ ረገድ ተቀናቃኝነት እንዳይፈጠር እንዲኖር አይሹም ነበር ። በተቻለ መጠን ሚዛናዊ የሆነ የመንግሥታት ትብብር እንዲኖር ነበር የሚጥሩት ።»
በሥልጣን ዘመናቸው በጀርመን የሶሻሊስት ስርዓት እንዳይስፋፋ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኃይል እንዲቀንስ አድርገዋል ። ሶሺያሊዝምን ለመዋጋትም አንዱ መንገድ ያደረጉት ሰራተኛውን መደብ ማስደሰት ነበር። ይህንንም በተግባር ተርጉመዋል ። ማህበራዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማትን ለምሳሌ የጤናና የአደጋና የጡረታ ዋስትናን በጀርመን አገር ለመጀመሪያ ጊዜ አስተዋውቀዋል ።
ቢስማርክ ከበርሊን በስተምዕራብ በምትገኘው በያኔዋ የፕረሽያ ግዛት በአሁንዋ የጀርመን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር በዛክሰን አንሃልታዋ ከተማ ሽንሃውዘን Schönhausen ከተማ ከባለፀጋ ቤተሰብ የዛሬ 200 ዓመት ነው የተወለዱት ። የተማሩ ከተሜና የንግግር ስጦታም ያለቸው ሰው ነበሩ ። እንግሊዘኛ ፈረንሳይኛ ኢጣልያንና የፖላንድ የሩስያ ቋንቋን አቀላጥፈው ይናገሩ የነበሩት ቢስማርክ የህግና የግብርና ምሁርም ነበሩ ። በ83 ዓመታቸው የዛሬ 117 ዓመት ነው ያረፉት ።

Porträt - Professor Arnd Bauerkämper
አርንድ ባወርኬምፐርምስል privat
Bildergalerie Bismarck Denkmäler
ምስል imago
Deutschland Prof. Christoph Nonn
ክሪስቶፍ ኖንምስል Heidi Sack
Im Krieg der Propaganda Otto von Bismarck
ምስል picture-alliance/Bibliographisches Institut & F.A

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ