1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«እንደ ታንጎ ዳንስ»-የደቡብ ሱዳን ድርድር

ዓርብ፣ የካቲት 20 2007

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች ድርድር በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት አማካኝነት አዲስ አበባ ላይ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ድርድሩን በጥሞና የሚከታተሉ የፖለቲካ ተንታኞች ድርድሩ ፋይዳ ቢስ ነው ሲሉ ይተቻሉ።

https://p.dw.com/p/1Eix9
Südsudan Waffenstillstand 01.02.2014 Addis Abeba
ምስል Reuters/T. Negeri

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች የሰላም ድርድር የካቲት 26 ቀን ከመጨረሻው ምዕራፍ ሊደርስ ቀጠሮ ተይዞለታል። የቀረው ጊዜ አንድ ሳምንት ብቻ ነው። በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ሪየክ ማቻር መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት በምሥራቅአፍሪቃየልማትበይነ-መንግስታት/ኢጋድ/ አዳራዳሪነት ከዚህ ሳምንት ሰኞ አንስቶ አዲስ አበባ ውስጥ የሰላም ንግግር እየተካሄደ ነው ። ከመጀመሩ አስቀድሞ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የስልጣን ዘመናቸውን በሁለት አመት ሲያራዝሙ ጥላ ያጠላበት ድርድር በቀሩት ጊዜያት ፍሬ የሚያፈራ አይመስልም። «ሁለቱ ወገኖች የሚፈለገውን ያህል ለመስማማት ቁርጠኝነት እያሳዩ አይደለም።» የሚሉት በዓለም አቀፍ የጸጥታ ጥናት ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን አየለ ድርድሩን ከታንጎ ዳንስ ጋር ያመሳስሉታል።

«የተኩስ አቁም ስምምነቱን እናከብራለን በወሬ ደረጃ ከማለት በስተቀር በተግባር አልታየም። መንግስትም በስልጣን ላይ ያለውን ቆይታ ማራዘሙ አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ ነው የተገኘው።ከድርድር ውጪም ሆነ ድርድር ላይ ሆነው የሚሰጧቸው መግለጫዎች እና በተግባር የሚያደርጓቸው ነገሮች የድርድሩን መንፈስ እያስተጓጎለውና በፊት ተስማምተው የነበረውን ወደ ኋላ የሚያስኬድ ሁኔታ ነው እየተፈጠረ ነው የታየው። ስለዚህ እንደ ታንጎ ዳንስ አንድ ወደ ፊት ሁለት ወደ ኋላ ይሄዳሉ።» ዶ/ር ሰለሞን የድርድር ሂደቱ ፋይዳ የለውም ብሎ መናገር እንደሚቻልም አስረድተዋል።

Kindersoldat im Süd-Sudan
ምስል Reuters/Migiro

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች ልዩነታቸውን መፍታት ከተሳናቸው በምሥራቅአፍሪቃየልማትበይነ-መንግስታት፤ዩናይትድ ስቴትስ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የታሰበው ማዕቀብ ገቢራዊነት አይቀሬ ይመስላል።ሶስቱም ወገኖች እስካሁን ማዕቀብን ለማስፈራሪያነት ሲጠቀሙበት ቢቆዩም ተግባራዊ ማድረጉ ግን እንዲህ ቀላል አይመስልም። ዩናይትድ ስቴስት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች ላይ የጦር መሳሪያ እንዳይገዙ እንዲሁም በውጪ የሚገኝ ሃብታቸውን ከማንቀሳቀስ የሚያግድ የማዕቀብ ምክረ ሃሳብ ማቅረቧ ተሰምቷል። እንደ ዶ/ር ሰለሞን አየለ ከሆነ ሁለቱም የሚሆን አይመስልም። የቀጠናው ሃገራትም ይሁኑ ዩናይትድ ስቴትስ የጦር መሳሪያ ግዢ ማዕቀብ በደቡብ ሱዳን ላይ የመጣል ፍላጎቱም ይሁን ተነሳሽነቱ የለም የሚሉት ዶ/ር ሰለሞን «በደቡብ ሱዳን እና በሱዳን ማዕከል ያለው የሃይል መጠን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።» የሚል ስጋት መኖሩን አስረድተዋል። የተቀናቃኝ ሃይሎቹ አመራሮች ሃብት እና ንብረትን ማገድም ቢሆን እምብዛም አያዋጣም። «እነዚህ ሰዎች ብዙ ሃብት እና ንብረት ያላቸው በአካባቢውሃገራት ውስጥ ነው። በተለይ በኬንያ እና በኡጋንዳ። አውሮጳ ወይም አሜሪካ ያን ያህል ሃብት አላቸው ተብሎ የሚባል አይደለም ።» ሲሉ ዶ/ር ሰለሞን አየለ ተናግረዋል።

Kindersoldaten in Südsudan
ምስል AFP/Getty Images/Ch. Lomodong

በምክረ-ሃሳቡ ላይ የሚቀረው ብቸኛ አማራጭ የተቀናቃኝ ሃይሎች ባለስልጣናት ላይ የጉዞ ማዕቀብ መጣል ብቻ ይሆናል። ይህም ቢሆን ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለበረከተባት ደቡብ ሱዳን እና ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ 1.9 ሚሊዮን ዜጎች የሚያመጣው መፍትሄ ለጊዜው አይታወቅም። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ባወጣው ዘገባ 7 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያን የረሃብ እና በሽታ ስጋት እንደተጋረጠባቸው ይፋ አድርጓል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ጸሃፊ የሆኑት ሃርቬ ላድሶስ በአዲሲቱ ሀገር ለተፈጠረው ቀውስ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸውን ሪየክ ማቻርን ተጠያቂ አድርገዋል። ሃርቬ ላድሶስ በሳምንቱ መጀመሪያ አሁን በደቡብ ሱዳን የተፈጠረው ዜጎቻቸውን ችላ ብለው በስልጣን ግብግብ በተጠመዱት የአገሪቱ ባለስልጣናት መፈጠሩን ለጸጥታው ምክር ቤት አስረድተዋል።

ካሁን ቀደም ለሰባት ጊዜ ተኩስ ለማቆም ተስማምተው ቃላቸውን ያጠፉት የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ሪየክ ማቻር ሃይሎች የአዲስ አበባ ድርድር ወደ መጨረሻው ተቃርቧል። ዶ/ር ሰለሞን አየለ ድርድሩ ፍሬ ማፍራት ካልቻለ የደቡብ ሱዳን መፃኢ እጣ ፈንታ ፈታኝ መሆኑን ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ