1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እቁብ የሚጥሉ ወጣቶች

ዓርብ፣ ጥቅምት 7 2007

የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዶቻችን ፤ታክሲ ላይ የሚያገለግሉ ወጣቶች ናቸው። ከደሞዛቸው እየቆጠቡ እና እቁብ እየጣሉ ፤ ህይወታቸውን እንዴት በመቀየር ላይ እንደሚገኙ ያጫውቱናል።

https://p.dw.com/p/1DW5k
Taschenrechner Währung Euro
ምስል Fotolia/alexandro900

በሳምንት አንድ ጊዜ የሚሰበሰብ እቁብ ነው። እጣ የወጣለት እቁብተኛ ደግሞ እስከ 100 000 ብር የማግኘት እድል አለው። የእቁቡ ሰብሳቢ ዮናስ ጌታቸው ከአምስት ዓመት በፊት ስለተጀመረው እቁብና አሰራሩ አጫውቶናል። ብሩክ ጌታቸው ደግሞ እንኳን ደስ ያለህ ከተባሉት እቁብተኞች አንዱ ነው። መጀመሪያ የደረሰው የ 25 000 ብር እቁም ነበር። ብሩክ አሁንም እቁብ ከመጣል አልተቆጠበም። ይበልጥ የተሻለ ነገር እንዳስብ ገፋፍቶኛል ይላል። ብሩክ ባገኘው እቁብ ታክሲ ገዝቶ በአሁኑ ሰዓት ራሱ ያሽከረክራል። የራሱን ታክሲ መንዳቱም ለተለሻለ ገቢ መንገድ ፈጥሮለታል። ሰብሳቢው ዮናስ እንደ ብሩክ ያሉ በርካታ እቁብ የደረሳቸውን ወጣቶች አስተናግዷል። ዮናስ እንደሚለው አብዛኞቹ እቁብተኞች ብሩን ወደ ንብረትነት ነው የሚቀይሩት።

ሌላው እቁብተኛ ያሬድ መንግሥቱ ይባላል። ያሬድ እቁብ ገና አልወጣለትም። የ 24 ዓመቱ ወጣት የሚተዳደረው አዲስ አበባ ውስጥ በታክሲ ረዳትነት ነው። ይህንን ስራ ሲሰራ አራት ዓመት ሆነው። በአሁኑ ሰዓት ራሱን ለማሳደግ እቁብን እንደ ትልቅ እድል ያያል።

ዮናስ ስለ እቁቡ አሰራር በገለፀልን ወቅት እቁቡ የተለያየ መደብ እንዳለውና ፣ እቁብተኛው እቅሙ የሚፈቅደውን ያህል እቁብ መጣል እንደሚችል እንዲሁም የሚያገኘው ገንዘብ ከጣለው እቁብ ጋር ተመጣጣኝ እንደሚሆን ገልፆልናል።

100 ሺ ብርም ባይሆን ብሩክ 25 ሺ ብር ሲደርሰው እቁቡን ለማግኘት ማቅረብ ስለነበረበት ዋስትና ያስታውሳል። በወቅቱ ፈተናውን እንዴት እንተጠጣው ገልፆልናል።

መንጃ ፍቃድ ለማውጣት የእቁብ እጣ እስኪወጣለት በመጠባበቅ ላይ ያለው ያሬድ ደግሞ ለጊዜው ስለሚያቀርበው ዋስትና ብዙም አያሳስበውም። ለሱ ከባዱ እቁብ ሳይጥል ገንዘቡን በግሉ ላጠራቅም ቢል ነበር፤

ከደሞዛቸው እየቆጠቡ በገቡት እቁብ ህይወታተውን ለማሻሻል ቆርጠው የተነሱ ወጣቶች ናቸው የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዶች ። ሙሉውን ዝግጅት በድምፅ ያገኙታል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ