1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤች አይቪ ኤድስን ለመዋጋት የተደረጉ ጥረቶች

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 15 2006

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012ዓ,ም በ50 ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸዉ ሃገራት የተካሄደ ምርምር 12 በመቶ የሚሆኑት በወሲብ ንግድ የተሠማሩ ሰዎች በHIV ቫይረስ መያዛቸዉን ያመለክታል። በዚህ ተግባር ከተሠማሩት 50 በመቶዉ የሚሆኑት በቫይረሱ የተያዙባቸዉ አካባቢዎች ደግሞ ከሰሃራ በስተደቡብ የገኙት ሃገራት ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/1CgnI
AIDS HIV Aids-Schleife
ምስል picture-alliance/dpa

20ኛዉን ዓለም ዓቀፍ የኤድስ ጉባኤ ከቀድሞዎቹ ለየት ያደረገዉ በHIV ኤድስ ሕይወታቸዉ የሚቀጠፍ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ ምርምር ያካሂዱ ከነበሩ ጥቂት የማይባሉ የዘርፉ ምሁራን ባልጠበቁትና ባልጠረጠሩት ሁኔታ ዘገባዎች እንደሚሉት በግድየለሾች በተተኮሰ ሚሳኤል ወደጉባኤዉ የሚወስዳቸዉ አዉሮፕላን ተመትቶ ካሰቡበት ሳይደርሱ ከመንገድ መቅረታቸዉ ነዉ። ጉባኤዉ እሁድ ዕለት ሲከፈት ለአንድ ደቂቃ እነዚህ ምሁራን በተሰበረ ልብ አስቧል። በቪዲዮ የጉባኤዉን መክፈቻ የተሳተፉት የተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ጊ ሙን በሕይወት ኖረዉ በዚህ ጉባኤ ለመሳተፍ የበቁ የዘርፉን ተመራማሪዎች በድንገት ያለፉት የሥራ ባልደረቦቻቸዉን ተግባር ገፍተዉበት ለዉጤት እንዲበቁ ምኞትና አደራቸዉን አስተላልፈዋል።

20th International AIDS Conference
ምስል aids2014

በሜልበርኑ ጉባኤ በተለይ ግኝቶችን ለመገምገም የተሰባሰበዉ ንዑስ ጉባኤ ላይ የካሊፎሪኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ስቴቨን ዲክስ የተናገሩት ለበሽታዉ ይገኛል የሚባለዉ አብነት ገና እንደሰማይ እንደራቀ መሆኑን ነዉ ያመለከተዉ። ዲክስ በHIV ቫይረስ የተያዘን ሰዉ የሚያድን መድሃኒት ለማግኘት የሚመራመሩ ምሁራንን ያሰባሰበዉ ንዑሥ ጉባኤ ምክትል ሊቀመንበር ሲሆኑ ቁርጥ ባለቃ ለዚህ መድሃኒት ለማግኘት« ገና ብዙ,,,, ብዙ ዓመታት» ሊወስድ እንደሚችል እቅጩን ተናግረዋል። እሳቸዉን እንዲህ ያሰኘና መሰል የሙያ ባልደረቦቻቸዉንም ጥረታቸዉ ገና ፍሬ እንዳላስገኘ ያመላከታቸዉ ነገር የተከሰተዉ እዚያዉ ሚሲሲፒ ዉስጥ ስትወለድ ቫይረሱ በደሟ እንዳለ የተወለደች ሕጻንን ፈጽሞ ለማዳን ያደረጉት ሁሉ ከሁለት ዓመታት በኋላ አልቦ ዉጤት መቅረቱ ነዉ። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ሕፃኗ የተቀላቀሉትን የሰዉነት የበሽታ መቋቋም አቅምን መገንባትና ማጠናከር የሚያስችሉ መድሃኒቶች መዉሰድ አቁማ ነበር። ቀደም ሲል ከተወለደችበት ጊዜ አንስቶ የተደረገላት የህክምና እርዳታም ዉጤት ያስገኛል የሚል እምነት ነበር በተመራማሪዎቹ ዘንድ። በየስድስት ሳምንቱም ክትትል ሲደረግላት ቆይቷል። የአዉስትራሊያዉ ጉባኤ ከመካሄዱት ጥቂት ቀናት በፊት ግን የተደረገላት ምርመራ በሽታ ከመቋቋም አቅም ጋ የተገናኘዉ በሰዉነቷ የሚገኘዉ የ CD4 መጠን እጅግ አንሶ ተገኘ። በዚህም ቫይረሱ በደማቸዉ እያለ የተወለዱ ልጆችን በቶሎ የማዳኑ ተስፋ ተነነ። ልጅቷም ወዲያዉ በተመራማሪዎቹ እንዲቋረጥ የተደረገዉ የተቀላቀለ መድሃኒት በምህጻሩ ART እንዲሰጣት ተደርጓል። እናም ይህ ተመራማሪዎቹ በቅርቡ ዉጤት እናይበታለን ያሉትን እንዳይጨብጡት በማድረጉ ነዉ ስቴቨን ዲክስ መፍትሄ ለማግኘት ገና ብዙ ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል ያመለከቱት። በዚህ ጉባኤ ላይ ትናንት ከተነሱት ነጥቦች አንዱ ደግሞ የወሲብ ንግድን የሚያግድ ሕግ ቢደነገግ በHIV ቫይረስ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር በከፍተኛ መጠን መቀነስ ይቻል ነበር የሚለዉ ነዉ። ከሁለት ዓመታት በፊት የተካሄደ አንድ የጥናት ዉጤት እንደሚለዉ ከሰሃራ በስተደቡብ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት በወሲብ ንግድ የተሠማሩ ወገኖች HIV ቫይረስ በደማቸዉ ዉስጥ ይገኛል። ከኤድስ ጋ በተገናኘ ለሚከተለዉ ሞትም 92 በመቶዉ በዚህ ተግባር የተሰማሩ እንደሆኑ ያመለክታል። በኢትዮጵያ የክሊንተን ተቋም ተጠሪ ዶክተር ይገረሙ አበበ HIV በኢትዮጵያ የከተማ በሽታ ነዉ ለማለት እንደሚያስደፍር በመጠቆም ለቫይረሱ በይበልጥ ከተጋለጡት ዉስጥ ዝሙት አዳሪዎችም ዋነኞቹ መሆናቸዉን ነዉ የሚያረጋግጡት።

HIV- und Aids-Behandlung in Malawi
ምስል picture-alliance/dpa

ዶክተር ይገረሙ በኢትዮጵያ ባጠቃላይ ሲታይ ቫይረሱ የሚያደርሰዉን ጉዳት ለመቀነስ የሚደረገዉ ጥረት ጥሩ ነዉ ቢሉም ቀደም ሲል እንደገለፁት ጋምቤላ ዉስጥና አዲስ አበባን ጨምሮ በትላልቅ ከተሞች፤ እንዲሁም በኅብረተሰብ ክፍል ረገድ በዝሙት አዳሪዎች፣ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎችና ከቦታ ቦታ ተዘዋዉረዉ የሚሠሩ ወገኖች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

Kinder im Aids Hospiz in Addis Abeba
ምስል AP Photo

የUNAIDS ዋና ዳይሬክተር ሚሸል ሲዲቤ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ላለፉት 25 ዓመታት ከተከናወነዉ ይልቅ ባለፉት ሶስት ዓመታት ዉስጥ የተሠራዉ ሥራ ትልቅ ለዉጥ እንዳመጣ ነዉ የተገናገሩት። ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃም የHIV ቫይረስ ስርጭት የመቀነሱ ጉዳይ ቢነገርም ሜልበርን አዉስትራሊያ በመካሄድ ላይ በሚገኘዉ ጉባኤ ይፋ የተደረገዉ በመላዉ ዓለም 35 ሚሊዮን ሕዝብ ከቫይረሱጋ ይኖራል፤ ሆኖም ግን 19 በመቶዎቹ ቫይረሱ በደማቸዉ እንደሚገኝ አያዉቁም። አሁን ስጋት የሆነዉ እንደተመራማሪዎቹ በጉርምስና የእድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች ለቫይረሱ የመጋለጣቸዉ ነገር ነዉ። በተለይ ቫይረሱ በደማቸዉ እንዳለ የተወለዱ ሕፃናት አድገዉ ለዚህ እድሜ ሲበቁ ሊከተል የሚችለዉን ከወዲሁ መገመት እንደሚገባ ነዉ በጉባኤዉ ላይ የተገለጸዉ። ከሳይንስ፣ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲዳረሱ ከሚጥሩ፤ እንዲሁም ከባለስልጣናት እና ከንግድ ዘርፉ የተዉጣጡ 12 ሺህ የሚሆኑ ተወካዮች በዚህ ጉባኤ ተሳታፊ ናቸዉ። እሁድ የተከፈተዉ 20ኛዉ ዓለም ዓቀፍ የኤድስ ጉባኤ የፊታችን ዓርብ ይጠናቀቃል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ