1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤቦላ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ በላይቤርያ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 17 2006

በምዕራብ አፍሪቃ ኤቦላ ተኀዋሲ አብዝቶ ጉዳት እያደረሰ ካለባቸው ሀገራት ውስጥ ላይቤርያ ናት። ከ15 የላይቤርያ ግዛቶች መካከል በስምንቱ የአስቸኳዩ ጊዜ ታውጆዋል። ስለበሽታው በቂ መረጃ የሌለው እና በሰበቡም ስጋት ያደረበባቸው የሀገሪቱ ነዋሪዎቹ በመንግሥታቸው ላይ እምነት አጥተዋል።

https://p.dw.com/p/1CzSX
Liberia Protest gegen Quarantäne
ምስል Getty Images

በላይቤርያ የግባርንጋ ራድዮ ጋዜጠኛ ጄፈርሰን ማሳ ከስቱድዮው «ኤቦላ እዚህ ተከስቶዋል፣ ኤቦላ ይገድላል፣ ለመሆኑ ኤቦላ ምንድን ነው?» የሚለውን ዘፈን ከፍ አድርጎ ያጫውታል። በአሁኑ ጊዜ ኤቦላን በተመለከተ ዝግጅት ያለው የራድዮው ጣቢያ በዚህ ዘፈን አማካኝነት ስለ ገዳዩ የኤቦላ በሽታ እና ራስን ስለመከላከሉ ሁኔታ መረጃ የመስጠት ዓላማ እንዳለው ከመዲናይቱ ሞንሮቪያ አራት ሰዓት ርቃ የምትገኘው ንዑሷ የግባርንጋ ከተማ ጋዜጠኛ ማሳ አስረድቶዋል።

« በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ እና ምን መደረግግ እንዳለበት የሚያስረዱ ቀላልመልዕክቶችን ነው የምናስተላልፈው። ለምሳሌ፣ የኤቦላ በሽታ ምልክት ከታየበት ሰው ጋ ቀጥተኛ ግንኙነት ከማድረግ ተቆጠቡ፣ ለብዙ ጊዜ የሚቆይ ትኩሳት ከተሰማችሁ ወይም የማስታወክ ስሜት ከተሰማችሁ ወዲያው ለጤና ባለሙያዎች አሳውቁ፣ የሚሉ መልዕክቶችን ያካባቢው ሕዝብ በሚገባው ቋንቋ እያዘጋጀን በማስተላለፍ ላይ እንገኛለን። »

Jefferson Massa, Journalist von Radio Gbarnga/ Liberia
ምስል DW/S. Duckstein

ጄፈርሰን ማሳ እና አቻዎቹ በራድዮ ዝግጅታቸው ውስጥ የተካተቱ አጫጭር ዘፈኖችንና የራድዮ ድራማዎችን ለአድማጮች ያደርሳሉ። በነዚሁ ዝግጅቶቻቸው በላይቤርያ ኤቦላን እና ስርጭቱን በተመለከተ ያለውን ወቅታዊ መረጃ በየቀኑ ወደ 800,000 ለሚጠጋው አድማጫቸው ያቀርባሉ። ጋዜጠኞቹ መረጃውን የሚያገኙት በቀጥታ ከጤና ጥበቃ ሚንስቴር ነው። በበሽታው የሞቱትን ወይም የተያዙትን ሰዎች ቁጥር እና በበሽታው አንፃር እየተወሰደ ስላለው ውሳኔ ያካባቢውን ፀረ ኤቦላ ዘመቻ ከሚመራው የጤና ጥበቃ መስሪያ ቤት ቡድን መዘርዝር ያገኛሉ። ጋዜጠኛው ጄፈርሰን ማሳ እንዳስረዳው፣ ራድዮ ሕዝብን ስለበሽታው ግንዛቤ በማስጨበጡ ረገድ ዓቢይ ድርሻ እያበረከተ ነው። ላይቤሪያውያኑ ጋዜጠኞች ሕዝቡን ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተጀመረው ማኅበራዊ ዘመቻ አካል መሆናቸውን ይናገራሉ። የራድዮ ጣቢያቸው ኤቦላን መከላከል ስለሚቻልበት ርምጃ ብቻ ሳይሆን በተኀዋሲው ተይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎችንም ከጤና መኮንኖች ቡድናት ጋር ማገናኘት መቻሉንም ማሳ አስታውቋል።

ከሲየራ ልዮን እና ከጊኒ ቀጥላ በተላላፊው ኤቦላ በጣም የተጎዳችው ሀገር ናት። የጀርመናውያኑ የዓለም የምግብ ድርጅት የላይቤርያ ቅርንጫፍ ኃላፊ ወይዘሮ አስያ ሀናኖ እንደሚሉት፣ የሀገሪቱ ሕዝብም ስለበሽታው በቂ መረጃ የለውም፣ ይህም ስጋት ፈጥሮበታል።

«የኤቦላ በሽታ በሕዝቡ ዘንድ ጭንቀትን እና ፍርሀትን አስከትሎዋል። ወጣቶች በጣም ሰግተዋል። በመንግሥታቸውም ሆነ በምዕራባውያን ርዳታ ሰጪዎች ላይ እምነት የላቸውም፣ ማንንም አያምኑም። በሽታው እንዳይዛቸው ተጨንቀዋል። ሌላ ሰው ለመንካት አይደፍሩም። ፍርሀት ነው የፈጠረው። »

የበሽታው ስርጭት በተለይ እርሱ በሚኖርበት አካባቢ አስደንጋጭ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው ጋዜጠኛው ማሳ የገለጸው።

« በዚህ በማዕከላይ ላይቤርያ በምትገኘው የግባርንጋ ከተማ ብቻ እስካሁን በኤቦላ 30 ሰው ሲሞት ፣ ከ100 በላይ በተኀዋሲው መያዙም ተረጋግጦዋል። ከሁሉም የሚያሳስበው ግን በዚሁ አካባቢ የሚገኙት ሀኪም ቤቶች በጠቅላላ መዘጋታቸው ነው። »

የሀኪም ቤቶቹ ሰራተኞች ርዳታ ፈልጎ ለሄደው የኤቦላ ምልክት ለታየበት በሽተኛ የሚሰጡት መድሀኒትም ሆነ በሽተኛውን ያክሙ በነበረበት ጊዜ ራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችላቸው ትክክለኛው ልብስ እንዳልነበራቸው አስታውቀዋል። የኤቦላ ተኀዋሲ በግባርንጋ ከተማ ከገባ እና አምስት ነርሶች ከሞቱ በኋላ ነው ሁለቱ ሀኪም ቤቶች የተዘጉት።

በሞንሮቪያም ቢሆን የህክምናው አገልግሎት ከበሽታው አሳሳቢነት ጋር በፍፁም የሚመጣጠን አለመሆኑ ነው የተሰማው። ነርሶች ስራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ራሳቸውን መከላከል ስላልቻሉ የስራ ማቆም አድማ ላይ ናቸው። በዚህም የተነሳ በኤቦላ የተያዙት ወይም ተይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩት በሽተኞች ብቻ ሳይሆኑ፣ በሌላ ህመም ሀኪም ቤት የሚገኙት ጭምር የሚያስፈልጋቸውን ህክምና እና መድሀኒት እያገኙ አይደለም ያሉት። የኤቦላ ተኀዋሲ በብዛት የተኢ,በት አንዱ የከተማይቱ ሰፈር በጠቅላላ ተከልሏል። የሰፈሩ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው መውጣትም ሆነ፣ ሌሎች ወደሰፈሩ መግባት አይፈቀድላቸውም። ያይን እማኞች እንደገለጹት፣ የሞንሮቪያ ፖሊስ ባለፈው ረቡዕ የኤቦላን ቫይረስ ስርጭት ለመቆጣጠር ሲባል የተከለለውን ሰፈር ለቀው ለመውጣት የሞከሩ የከተማይቱ ነዋሪዎች ሰፈሩን ለቀው እንዳይወጡ ለማከላከል በሚያስለቅስ ጋዝ እስከመጠቀም ርቆ ነበር ተጠቅሞዋል።

Zubah Yenego Aktivist aus Monrovia
ምስል DW/J. Kanubah

ይህን ዓይነት ዓቢይ ጥፋት እያደረሰ የሚገኘው ተላላፊ በሽታ ሕዝብ ማኀበራዊ ኑሮ እና ስነ ልቦናዊ ይዞታ ላይ አሉታዊ መዘዝ ማስከተሉንም የማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ሰራተኛ ላይቤሪያዊው ዙባህ የኔጎ አመልክተዋል።

«አፍሪቃውያን የምንኖረው ባጠቃላይ ለማኅበራዊ እና ባህላዊ ልማዶች ትልቅ ትርጓሜ በሚሰጥ አህጉር ውስጥ ነው። ለምሳሌ፣ ላይቤርያ ውስጥ ኤቦላ በወጣቱ ዘንድ ትልቅ ስጋት ፈጥሮዋል። ባሁኑ ሰዓት ሰው ሲገናኝ እንደድሮው መጨባበጥም ሆነ መሳሳም ትቶዋል፣ ባጠቃላይ አንዱ ሌላውን ሰው የቅርብ ቢሆንም ለመንካት አይፈልግም፣ ሁሉም በሩቁ ሆኖዋል። በኤቦላ የተነሳ ይህ የተለመደ ሆኖዋል። »

የ14 ዓመቱ ላይቤሪያዊ ተማሪ ኤድዊን ስኖርተን እንደሚለው፣ ተማሪዎችም ትምህርት ቤታቸው በመዘጋቱ ስራ ፈተው ቤት ውስጥ መዋሉን አልወደዱትም ።

« ትምህርት ቤቴ፣ በተለይም ፣ ጓደኞቼ ናፍቀውኛል። እና ወላጆቼ ስራ ስለሚሄዱ ብቻዬን እቤት መቀመጡ ሰልችቶኛል። »

የኤቦላ ተኀዋሲ ስርጭት ኅብረተሰቡ ኑሮውን እና ስራውን እንደተለመደ እንዳያከናውን እያሰናከለው መሆኑን ሌላው የተከለለው ሰፈር ነዋሪ ቪክቶር ሼአ ገልጾዋል።

« የኤቦላ ቫይረስ ኅብረተሰባችንን ወደኋላ መልሶታል። በተለይ፣ ለኛ ለወጣቶች ትልቅ ምት ነው የሆነብን። በሀገራችን ሰላም በወረደባቸው ባለፉት ስምንት ዓመታት ራሳችንን ለማሻሻል ብዙ ሞክረናል። ይሁንና፣ አሁን የኤቦላ መከሰት ልክ የጦርነት ያክል ወደነበርንበት መልሶናል። »

የኤቦላ ስርጭት በላይቤሪያ ማኅበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ይዞታ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በሀገሪቱ ኤኮኖሚም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተገልጾዋል።

ጁልየስ ካኑባህ/አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ