1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያና የጀርመን ባለወረቶች

ማክሰኞ፣ ግንቦት 18 2007

የጀርመንና የአፍሪቃ የንግድ መታሰቢያ ዕለት ባለንበት 2015 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት፤ ፤ ሰኔ 2 ቀን 2007 በርሊን ውስጥ በስብሰባ የሚዘከር ሲሆን ፤ የጀርመን የኤኮኖሚ ትብብርና የልማት ተራድዖ ሚንስቴር ፤ እንዲሁም አፍሪቃን በመወከል የታንዛንያ

https://p.dw.com/p/1FWgN
ምስል DW/Ludger Schadomsky

[No title]

ባለሥልጣናት ንግግር ያሰማሉ። በአፍሪቃ ገንዘብን ሥራ ላይ በማዋል የልማትና ንግድ ተባባሪ የሆነው ፤ የአፍሪቃና የጀርመን ማሕበር ፣ በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት እንደሚያደርገው ሁሉ ፤ ኢትዮጵያም ውስጥ ገንዘብ ሥራ ላይ ለማዋል ፍላጎት እንዳለው የታወቀ ነው። DW፤ Afrika-Verein der deutschen Wirtschaft የተሰኘውን ማሕበር ሥራ አስኪያጅ አነጋግሮአል።

የጀርመን ባለወረቶች ገንዘባቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ላይ ለማዋል ላቀረቡት ጥያቄ ያገኙት ምላሽ ምን ይመስላል? ገንዘብ ሥራ ላይ የሚውልበት ሁኔታ የሠመረ እንዲሆን ፣ መሟላት የሚኖርባቸው ቅድመ ግዴታዎች የትኞቹ ናቸው? ለአፍሪቃና ጀርመን የኤኮኖሚ ማሕበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ክሪስቶፍ ካነንጊሰር የ DW ው ሉድገር ሻዶምስኪ ያቀረበላቸው ጥያቄ ነበር።

«የጀርመን ኩባንያዎች ስላገኙት ምላሽ የሚናገሩት የተለያየ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንድ የኢንዱስትሪ ኩባንያዎች ለማቋቋም ፣ ንግድም ለማካሄድ፤ በንጽጽር ማለፊያ ዕድል እንዳጋጠማቸው፣ ድጋፍ እንደሚሰጣቸው የተሰማቸው መሆኑን የሚናገሩ አሉ። ሌሎች ኩብንያዎች በፊናቸው፤ በተተበተበ ቢሮክራሲ ፤ ሕግን ባልተከተለ አሠራርና ፍትሓዊነትን በማያንጸባርቅ የፍርድ ቤት ብይን እንዲሁም በሙስና መቸገራቸውን የገለጹ አሉ። አንድ ዓይነት ምላሽ አይደለም የተገኘው። ያም ሆኖ፤ ኩባንያዎች ሁሉ፤ ኢትዮጵያ በቀጣይ ትልቅ የዕድገት እመርታ ማሳየት ከፈለገች፤ ገንዘብ ሥራ ላይ የሚውልበት የንግዱ መንፈስ መሻሻል ይኖርበታል ብለው ያምናሉ።»

የዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በተደጋጋሚ የተፍታታ ነጻ የገበያ በር እንዲከፈት፣ ማሳሰባቸውን ይናገራሉ። እንደርስዎ ተመክሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ዓመታት፣ በቂ ማሻሻያዎችን አድርጓል ወይ? በተለይ ገንዘብን ሥራ ላይ በማዋል ረገድ፣ --እንበል በባንክ አሠራር፣ ምንዛሪን ወደ ውጭ በማውጣት፤ በ Telecomunication፣ ብድር በማግኘትና በመሳሰለው የተሻሻለ ሁኔታ አለ?

«በዚህ ረገድ በተሃድሶ ለውጥ መርኆዎችን ለማሻሻል፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ከዚህ ቀደም እንደታየው ሁሉ የሚያጓጓ ሁኔታ አይታይም። ተስፋ የምናደርገው በሚመጡት ዓመታት በግልጽ እንደሚሻሻል ነው። ቀደም ሲል እንደገለጽነው ሁሉ ብርቱ የቢሮክራሲ ችግር አለ። ቢሮክራሲው በአገሪቱ በሰፊው ነው ጣልቃ የሚገባው። ክፍያን በሚመለከት የአስተማማኝነት ሳንክ አለ። ይህ ደግሞ ከውጭ ምንዛሪ ገቢ የማግኘት እጥረት ጋር የተያያዘ ነው የሚመስለው። የማሻሻል ምልክቶች የሚታዩ ቢመስሉም፤ ኢትዮጵያ ገና በአመዛኙ መድረስ ከሚገባት ቦታ ላይ አይደለም የምትገኘው። እርግጥ፤ ቀስ በቀስ የሚሻሻሉ ሁኔታዎች ይታያሉ። ገንዘብ ሥራ ላይ ለሚያውሉ ሁኔታዎችን ለማሻሻል ጥረት ይደረጋል። ምርት ወደ ውጭ ከሚያቀርቡ ይልቅ ገንዘብ ሥራ ላይ ይውል ዘንድ ወረታቸውን ሥራ ላይ ለሚያውሉ የተሻለ ሁኔታ አለ።»

deutsches Unternehmen Forschner in Svalyava (Ukraine)
ምስል DW/N. Sokolowska

የዘንድሮው ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የሰብአዊ መብት አያያዝን በተመለከተ ዐቢይ ግምት ሊሰጠው እንደሚገባና ይህም መመሪያ ሆኖ መቅረብ አለበት ሲሉ ማስገንዘብዎ ይታወሳል። ገንዘብን ሥራ ላይ ማዋሉ ከሰብአዊ መብት ጥበቃ ጋር መቆራኘት አለበት ነው የሚሉት? የ DW ጥያቄ ነበር።

«ለጀርመናውያን ኩባንያዎች ባጠቃላይ የምዕራባውያን ኩባንያዎች ገንዘብን ሥራ ላይ ማዋል የሚበጀው፣ ማለፊያ የፖለቲካ መርሕም ሆነ ስም ባላቸው አገሮች ነው። በተለይ የሰው ልጅ መብት ነጋ ጠባ እንደሚረገጥባቸው በየዕለቱ በማይሰማባቸው አገሮች!ስለሆነም፤ በአንድ ሀገር ዓለም አቀፍ ባለወረቶችን የሚያማልልበት፤ የሰብአዊ መብት የሚከርበትና ደረጃው የሚጠበቅበት ሁኔታ ግንኙነት አላቸው።»

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ምርጫ ተካሂዷል፤ በመጪው መስከረም ወር ማለቂያ ገደማ ፣ ቀጣዩ አስተዳደር ሥራውን ሲጀምር ፤ ለጀርመናውያን ባለወረቶች የሥራ እንቅሥቃሤ፣ አነቃቂ ሁኔታ ይፈጥራል ብለው ያስባሉ?

ወደዚሁ አቅጣቻ እንደሚያመራ ተስፋ እናደርጋለን ለዚህም፣ በሌሎች አገሮች ያጋጠሙ ሁኔታዎች ጠቋሚዎች ናቸው። ከምርጫ በፊት እርግጠኛ ለመሆን ጠብቆ ማየት የሚል ስሜትb ይኖራል። ምርጫ፤ አዲስ የተሃድሶ ለውጥ ለማድረግ መነሣሣትን ሊፈጥር ይችላል፤ የተሃድሶ ለውጥ መነሣሣት ደግሞ ኢትዮጵያም ውስጥ ከምርጫው በኋላ ያጋጥማል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።»

ተክሌ የኋላ/ሉድገር ሻዶምስኪ

ኂሩት መለሰ