1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃውያት የግብርና ምርምርና የልማት ሳይንቲስቶች

ረቡዕ፣ የካቲት 18 2007

ከ2 ዓመት ገደማ በፊት የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት ያከበረው የቀድሞው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ፤ ያሁኑ የአፍሪቃ ሕብረት ፣ በቀጣይ 50 ዓመታት ፣ ማለትም እ ጎ አ እስከ 2063 ፣ ክፍለ ዓለሙ አንድነቱን አጠናክሮ ፣ በኤኮኖሚ ዳብሮ ፤

https://p.dw.com/p/1EhjQ
ምስል Fotolia/VRD

ሰላምንም አሥፍኖ እንዲገኝ ነው አጥብቆ የሚሻውም ሆነ በተቻለ አቅሙ ለማከናወን የሚጥረው። እስከዚያ ፣ አምሮ ሠምሮ ለማየት የሚሻው የሴቶችን በሁሉ የልማት ዘርፎች የአመራር ችሎታ ቀስመውና አዳብረው እንዲገኙ ማብቃት ይሆናል። ለዚህም ሳይሆን አልቀረም የአፍሪቃ ሕብረት 2015 ጎርጎሪየሳዊውን ዓመት « የሴቶች የአመራር ብቃትና የልማት ተሳትፎ» የሚተኮርበት ዘመን እንዲሆን የወሰነው።

ይህ ፤ ዓላማም ሆነ ራእይ እውን ሆኖ እንዲገኝ ከሚጥሩት ተቋማት መካከል አንዱ ዋና ጽ/ቤቱ በናይሮቢ ኬንያ የሚገኘው ፣ እ ጎ አ በ 2008 ለመጀመሪያ ጊዜ ለ 5 ዓመታት ፣ በፕሮጀክት መልክ የተቋቋመውና በ 2012 እንደገና በ 5 ዓመት የተራዘመው ፣ የአፍሪቃ ሴቶች በግብርና ምርምርና ልማት African Women in Agricultural Research and Development በእንግሊዝኛው ምህጻር AWARD በመባል የታወቀው ነው። ይህን ተቋም ፣ ቱጃሮቹ ፤ አሜሪካውያን ቢልና ሜሊንዳ ጌትስ በሰፊው የሚደግፉት ሲሆን፣ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት፤ እንዲሁም በአፍሪቃ የአረንጓዴ አብዮት ተጓዳኝ የተሰኘው ድርጅትም ያግዙታል ። ተጨማሪውን የከፍተኛ የትምህርት ዕድል የሚያገኙት ሰዎች፤ በዩናይትድ ስቴትስ በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት፣ ለምሳሌ ያህል፤ በኬንያና ፤ በኢትዮጵያ፤ በ በስዊድን ፤ በብራዚል በፊሊፒንስ ፈረንሳይና በመሳሰሉ አገሮችም መከታተል ይችላሉ። የተቋሙ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፤ ዶ/ር ዋንጂሩ ካማዎ -ሩተንበርግ

19.02.2015 DW Global 3000 Kenia Fluss

«አፍሪቃ ውስጥ በግብርና ምርምርና በአጠቃላይ በከፈተኛ የትምህርት ተቋማት የሴቶች ተሳትፎ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ AWARD ግንባር ቀደም ትግል በማካሄድ፤ በተለይ በግብርናና ልማት ምርምር፣ ውሳኔ ሰጭነት ፣ በሙያው ብቃት ያላቸው ሴቶች ቁጥር በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም በመላ እንዲጨምር ተግባሩን ያከናውናል፤ በአፍሪቃ አቀፉ ማሕበረሰብ ውስጥ አፍሪቃውያት ተመራማሪ ሴቶች፤ ለምግብ ዋስትና አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉም ተስፋ አለን » ነው ያሉት።

AWARD ባካሄደው ጥናት መሠረት፤ በአፍሪቃ ምግብም ሆነ እህል አምራቾች ሰብሳቢዎችና ለገበያ አቅራቢዎች ሴቶች ሆነው ሳለ፤ በግብርናና ልማት ምርምር ረገድ ከ 4 ወንድ አንዲት ሴት ብትገኝ ነው በዚሁ የምርምር ዘርፍም ሆነ ተቋም፤ በከፍተኛ የአመራር ደረጃ ላይ የሚገኙት ሴቶች ቁጥር እጅግ ዝቅ ያለ ነው፤ ከ 7 አንድ ! ታዲያ ግብርና ለብልጽግና ዋናው አንቀሳቃሽ ሞተር እንዲሆን ከተፈለገ፤ በምግብ ዋስትናና በግብርና ልማት ረገድ ወጣት አፍሪቃውያት መሪዎችን መኮትኮት የግድ ይላል። ዶ/ር ዋንጂሩ ካማዎ ሩተንበርግ እንደሚሉት፤ በሥነ ቴክኒኩ ብቃት ያላቸው በራሳቸው የሚተማመኑና ተሰሚነት ያላቸው ሴቶች ቁጥር መበራከት ይኖርበታል። ስለሆነም ዘንድሮ ፤ በዚሁ 2015 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት AWARD ከ 11 የአፍሪቃ ሃገራት፤ ማመልከቻ ካስገቡ 1,109 የግብርና ምሁራን ሴቶች መካከል በችሎታቸው ለተመረጡ 70 አፍሪቃውያት የግብርና ሳይንቲስቶች ተጨማሪ የትምህርት ዕድል ሰጥቷል። ከሰባው ዐራ ቱ ፣ ከኢትዮጵያ ሲሆኑ ፤ ከኬንያ 9 ከጋና 4 ከማላዊ 7 ከናይጀሪያ ደግሞ ቁጥራቸው ከፍ ያለ ፣ ማለት ፣ 20 ናቸው ፣ የዚሁ ዕድል ተጠቃሚዎች የሚሆኑት። በተጠቀሰው ተቋም አማካይነት ቀደም ሲል ተጨማሪ የ 2 ዓመት የትምህርት ዕድል በማግኘት በዕለታዊ ተግባራቸው ስላለው ጠቀሚነት ከገለጡት መካከል፣ ኢትዮጵያዊቷ የዲላ ዩንቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር ፣ ዶ/ር ሔዋን ደምሴ ይገኙበታል።

«የኔ ምርምር ይበልጥ የሚያተኩረው አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች፣ የእህልን ዘር ጥራት በማሻሻል ረገድ ነው። ምርጥ ዘር ማስገኘት፤ አርሶ አደሮቹ ጥራት ያለው የእህል ምርት እንዲያገኙና ምርታማነቱም እንዲጨምር ማብቃት ነው። ኢትዮጵያ ፣ ከእንግዲህ በ 10 ዓመት ውስጥ የተሻለ የምግብ ዋስትና ይኖራታል፣ የገጠሩም ሕዝብ ኑሮ በተለይም የሴቶች ኑሮ ተሻሽሎ ይገኛል የሚል እምነት አለኝ።»

ዶ/ር ሔዋን ደምሴ፤ ከ AWARD ተጨማሪ ትምህርት በኋላ ለሙያቸው የቱን ያህል እንደበጃቸው እንዲህ ነበረ ያስረዱት።

«ከ AWARD የአቅጣጫ መምሪያና ክትትል ማድረጊያ ዐውደ ጥናት በፊት በራሴ ተነሳሽነት እርምጃዎች ለመውሰድ ፣ በተለይ ደግሞ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም አልሻም ነበር። ይሁንና ከዐውደ ጥናቱ በኋላ ማድረግ የምችላቸው ብዙ ነገሮች መኖራቸውን ተገነዘብሁ። በሀገሬ ካሉ ባልደረቦቼ በላቀ ሁኔታ ሰፋ ያለ ጠቀሜታም ነው ያገኘሁበት። አሁን ተነሳሽነት በማሳየትና የአመራር ኀላፊነትን ለመሸከም ያገኘሁትን ትምህርት ለሃገሬ መልሼ መስጠት ይኖርብኛል። በዚህ ረገድ ፣ አሁን በዩንቨርስቴዬ የጥራት ዋስትና ጉዳይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ነኝ ይህ ደግሞ ይበልጥ በሥራ እንድታይ ያደርጋልና ከ AWARD የቀሰምኩትን የአመራሩን ጥበብ መልሼ መስጠት ይኖርብኛል።»

Anbau von grünen Bohnen in Kenia
ምስል T. Karumba/AFP/Getty Images

ሌላይቱ ኬንያዊቷ የ AWARD ተጠቃሚና በናይሮቢ ዩንቨርስቲ መምህር ዶ/ር ጄይን አምቡኮ በበኩላቸው እንዲህ ይላሉ።

«የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ሳይንቲስት ነኝ። በዚህ ረገድ ላቅ ያለ ትኩረት ያደረግኩት ከአዝመራ አሰባሰብ ጋር በተያያዘ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ላይ ነው። እናም አዝመራ ሲሰበሰብ የሚባክን ምርትን ማዳንም ሆነ መቀነስ በሚቻልበት ላይ ክትትል አደርጋለሁ። የምርት ብክነትን መግታት ላይ ያተኮርኩበት ምክንያት ከሚመረተው መካከል 50 ከመቶ ገደማ የሚሆነው ጥቅም ሳይሰጥ ባክኖ የሚቀር መሆኑን የጥናት ሰነዶች የሚያሳዩ በመሆናቸው ነው።ስለዚህ የኔ ምርምር ፤ ይህን 50 ከመቶ የጓሮ አትክልትና ፍርፍሬ ምርት እንዴት ከብክነት እናድናለን ነው! ድካሙና ትርፉ በሚሰላበት ጊዜ አብዛኛው ባክኖ የሚቀረው አነስተኛ የመሬት ይዞታ ባላቸው አርሶ አደሮች የሚፈጠር አይደለም። እነርሱ የሚተርፋቸው የምርት ብክነቱ ፤ ኪሣራው ነው።»

በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም በተለይም ከሰሐራ ምድረበዳ በስተደቡብ በሚገኙት አገሮች ከግብርና ጋር በተያያዘ ፤ በጓሮ አትክልትና ፍርፍሬ ልማት ፤ እንዲሁም በአዝርእት ከዘር እስከ አዝመራ መሰብሰብና ማከማቸት እንዲሁም ለቤተሰብ ምግብ ተብቃቅቶ ረሃብ እንዳያጋጥም ዋንኛውን ኃላፊነት የሚሸከሙ ሴቶች መሆናቸው የታወቀ ነው። በባህል ትልቅ ኀላፊነት የሚሸከሙ ሴቶች ፤ በትምህርት ሲታገዝ ፣ ለሕብረተሰቡ የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው የሚሆነው። እዚህም ላይ አፍሪቃውያት የግብርና ሳይንቲስቶች ፤ በዚህም ረገድ የአመራር ኀላፊነት እንዲሸከሙ ከሚጥሩት አንዷ ኬንያዊቷ የግብርና ሳይንስ ተማራማሪዋ ሜሪ ኦዩንጋ ናቸው። ሜሪ ኦዩንጋ ፣ ከ 6 ዓመት ገደማ በፊት የምግብ ዋስትናንና ጤንነትን ያቀናጀ የምርምር ውጤት ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ቀይ ሥር ወይም ብርቱካንማ ቀለም ያለው ስኳር ድንች ለምግብነት ብቻ ሳይሆን የተሟላ ቪታሚን A ስላለው በዚህ ረገድ የሚያጋጥም ጉድለትን በማስወገድ ሰፊ ጠቀሜታ ሊሰጥ እንደሚችል፤ በተለይም ከሰሐራ ምድረበዳ በስተደቡብ ከ 40 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዕድሜአቸው ከ 5 ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት የሚበጅ መሆኑን የግብርና ሳይንቲስቷ በማረጋገጥ ማለፊያ ስም ማትረፋቸው አይዘነጋም። ቀይ ሥር መሰሉ ፤ ብርቱካንማ ቀለም ያለው ስኳር ድንች ፤ በሰፊው ቪታሚን A ብቻ ሳይሆን፤ ቪታሚን B5 , B6 Thiamin,Niacin እና የመሳሰሉትን ጠቀሚ ንጥሮች ያካተተ ነው።

Master zum Themenheader Kann Afrika den Hunger stillen? SÄTTIGUNG NEU
ምስል AFP/Getty Images

ስኳር ድንችም ሆነ መደበኛው ድንች በኃይል ሰጪ ምግብነቱ የታወቀ ሲሆን ፣ እንደ ሙዝና በቆሎ እርሱም ምንጩ ማዕከላዊና ደቡብ አሜሪካ ነው። ለምግብነት ይውል ዘንድ መልማት ከጀመረ ቢያንስ የ 10ሺ ዓመት ዕድሜ አለው። እ ጎ አ በ 1492 ክርስቶፈር ኮሎምበስ ከካራይብ ደሴቶች ሲ,መለስ ለአውሮፓ ካስተዋወቀ በኋላ፣ በ 16ኛው ክፍለ ዘመን ፖርቱጋላውያንና እስፓኛውያን አገር አሳሾች፤ ስኳር ድንችን በአፍሪቃ ፤ በደቡባዊው እስያ፤ ፊሊፒንስ፣ ሕንድና ኢንዶኔሺያ አስተዋወቁ። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ውስጥ ስኳር ድንጭ በገፍ የምታመርት ሀገር ቻይና ናት ። በያመቱ ፣ 80 ሚሊዮን ቶን ያህል ታመርታለች። አፍሪቃ 14 ሚሊዮን ቶን ያህል ነው የሚያመርተው።

አፍሪቃ ፤ በሳይንሳዊ ምርምር በመታገዝ ፣ የአፈር ልማትን በሚገባ በመንከባከብ፤ አልሚ ፤ ኃይል ሰጪና የተለያዩ በሽታዎችን ተከላካይ አዝርእት፤ አትክልትና ፍራፍሬ በማማረት ፣ ሕዝቡን ከረሃብና በሽታ መታደግ ይቻለው ዘንድ ፣ በብዛት የግብርና ባለሙያዎች ያስፈልጉታል። በተለይ ሴቶች የግብርና ሳይንቲስቶች! ስለሆነም የ AWARD ተጨማሪ ከፍተኛ ትምህርት ሰፊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ነው የሚታመነው።

ተክሌ የኋላ

ኂሩት መለሰ