1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢው የደቡብ ሱዳን የጦር መሣሪያ ግዥ

ዓርብ፣ ነሐሴ 16 2006

ወደ ደቡብ ሱዳን በብዛት የሚገባው የጦር መሳሪያ ጦርነቱ እንዳይቆም እያደረገ ነው ሲሉ የጦር መሣሪያዎች ዝውውር ተቆጣጣሪዎች ያሳስባሉ ።አንዳንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ደግሞ በደቡብ ሱዳን ላይ የጦር መሣሪያ ሽያጭ ማዕቀብ እንዲጣል እየጠየቁ ነው ።

https://p.dw.com/p/1CyMF
Südsudan Rebellen 10.02.2014
ምስል Reuters

ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት እስካሁን በደቡብ ሱዳን ላይ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማዕቀብ አልጣለም ።ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘው የዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም በምህጻሩ ISS ሃላፊ ያኪ ሲልየ ሽያጩ አለመታገዱ የደቡብ ሱዳንን መንግስት ጠቅሟል ይላሉ ። የርስ በርስ ውጊያ የሚካሄድባት ደቡብ ሱዳን ብዙ ገንዘብ የፈሰሰባቸው የጦር መሣሪያዎች የሚጎርፉባት ሃገር መሆኗ እያሳሰበ ነው ።ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች እንደሚሉት አሁን የሚያሳስበው ወደ ሃገሪቱ የሚገባው የጦር መሳሪያ ብዛት ብቻ ሳይሆን ዓይነቱም ጭምር ነው ። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ፀረ ታንኮችን ጨምሮ አሁን ወደ ደቡብ ሱዳን የሚገቡት የጦር መሣሪያዎች ብዙ ገንዘብ የወጣባቸውና እጅግ የተራቀቁም ናቸው ። የጦር መሣሪያዎች ጉዳይ አዋቂዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚሉት 38 ሚሊዮን ዶላር የወጣባቸው ፀረ ታንክ ሚሳይሎች ፣ የቦምብ ማስወንጨፊያዎችና ጠመንጃዎች ባለፈው ሰኔ ሱዳን ገብተዋል ። ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘው የዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ሃላፊ ያኪ ሲልየ የጦር መሳሪያ ሽያጭ እገዳ በሌለበት በአሁኑ ሁኔታ የደቡብ ሱዳን መንግሥት መጠቀሙን ያስረዳሉ ።

Symbolbild - Soldaten Südsudan
ምስል Getty Images

«አሁን ያለው ሁኔታ በርግጠኝነት የጁባን መንግስት የሚጠቅም ነው ። ምክንያቱም እነርሱ የእርዳታ ገንዘብ ያገኛሉ ። የጦር መሳሪያ መግዛት ይችላሉ ።ዩጋንዳም አጋራቸው ናት ። የጦር መሳሪያ መግዛታቸውና ራሳቸውን ማስታጠቃቸው በሂደት በአማፅያን እንቅስቃሴ ላይ ጫናውን ያጠናክራል ።የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማዕቀብ ቢጣል አማፅያኑን ሊጠቅም እንደሚችል መንግሥትን ደግሞ እንደሚጎዳ መገመት ይቻላል ።»

ባለፈው ሰኔ ወደ ደቡብ ሱዳን የገባው የጦር መሣሪያ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ከቻይና የተገዛ መሆኑ ተዘግቧል ። መሳሪያው ወደ ጁባ ያቀናውም የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን IGAD አባል በሆነችው በኬንያ በኩል ነው ። የሌላዋ የኢጋድ አባል የዩጋንዳ ጦር ደግሞ ደቡብ ሱዳን ዘምቶ ከአማፅያኑ ጋር እየተዋጋ ነው ። በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማውረድ መንግስትንና አማፅያንን የሚሸመግለውየኢጋድ አባል አገራት በደቡቡ ሱዳን ያላቸው ያላቸው ሚና በሰላሙ ሂደት ላይ የበኩሉን ተፅእኖ ማሳደሩ እንዳልቀረ ጃኪ ሲልየ ተናግረዋል ።

Südsudan Bentiu Rebell Massaker Leiche GEPIXELT
ምስል Reuters

«አማፅያኑ ኢጋድ በደቡብ ሱዳን የሰላም ሂደት ገለልተኛ አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ ። ምክንያቱም እንደተባለው ኬንያና ኡጋንዳ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ወገን የቆሙ ይመስላል ። ስለዚህ ይህ አንድ ችግር ነው ። ሆኖም ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በአጠቃላይ የደቡብ ሱዳንን የአስተዳደር ችግር መፍቻው ህጋዊ መንገድ ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት እንጂ የጦር ኃይል አይደለም የሚል ስሜት ነው ያለው ። ርግጥ ነው ተቃዋሚው ሪክ ማቻርና ሌሎች ይህን ሞክረው ምንም እንቅስቃሴ የለም ነው የሚሉት ።»

የደቡብ ሱዳኑ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ወደ ሃገሪቱ የሚገባው የጦር መሳሪያ ከዚያ በፊት ከነበረው እጅግ የላቀ ሆኖ ነው የተገኘው ።አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩመንራይትስ ዋች የደቡብ ሱዳኑን ጦርነት ያባብሳል የሚሉት የጦር መሳሪያ ሽያጭ እንዲከለከል ጥሪያቸውን እያቀረቡ ነው ።የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ግን በደቡብ ሱዳን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማዕቀብ ሊጣል ይችላል ሲል ከማስጠንቀቀቅ ውጭ እስካሁን ማዕቀብ አልጣለም ። ጃኪ ሲልየ ምክንያቱ ለጁባ መንግሥት ያለው ዓለም ዓቀፍ ድጋፍ ነው ያላሉ ።

«የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አቋም ራሱንና ግዛቱን በጦር መሣሪያ ከሚያጠቁ አማጽያን የመከላከል መብት ያለው በምርጫ ስልጣን የያዘ ህጋዊ መንግሥት አለ የሚል ነው ። በአዲስ አበባ እየተቋረጠም እእንደገና እየቀጠለ የሚካሄደው የሰላም ሂደት አለ ። ስለዚህ ከአካባቢያዊና ዓለም ዓቀፋዊ እይታ አንፃር ለጁባ መንግሥት ድጋፍ አለ ።»

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ