1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አነጋጋሪው የዪኒቨርስቲ ተማሪዎች የፖሊሲ ስልጠና

ረቡዕ፣ ነሐሴ 21 2006

ተማሪዎችና የፖለቲካ ተቋዋሚ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ፖሊሲ ላይ ያተኮረው ለከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት ተማሪዎች የሚሰጠውሥልጠና ከጥሪው አንስቶ በግዳጅ የሚካሄድ መሆኑን ነው የሚናገሩት የኢትዮጵያ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የሁለት ሳምንታት የፖሊሲ ስልጠና ላይ መሆናቸውን መንግስት አስታውቋል ።

https://p.dw.com/p/1D2lF
Hauptcampus der Universität Addis Abeba AAU
ምስል DW

ነሐሴ 20 የተጀመረው ይኽው ስልጠና ተማሪዎች በግዳጅ የሚሳተፉበት መሆኑን አንዳንድ ተማሪዎችና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይናገራሉ ።መንግሥት ግን ይህን ያስተባብላል ።

ተማሪዎችና የፖለቲካ ተቋዋሚ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ፖሊሲ ላይ ያተኮረው ለከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት ተማሪዎች የሚሰጠውሥልጠና ከጥሪው አንስቶ በግዳጅ የሚካሄድ መሆኑን ነው የሚናገሩት ። በተለይ በስልጠናው የማይሳተፉ ተማሪዎች በመጪው አመት የትምህርት እድል እንደማያገኙ ይገልፃሉ ።ከዚህ በተጨማሪ የትምህርት ነጻነትና ፖለቲካዊ ሰበካ በመርህ ደረጃ አብረው የማይሄዱ ሆኖ እያለ ተማሪዎችም ይህን አስመልክቶ ቅሬታቸውን እንዳያሰሙ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ነው የሚገልፁት ። በትምህርት ላይ ሳሉ የኢህአዴግ አባል የሆኑ ተማሪዎች በኩል መመዝገባቸውንና የስልጠና ቅጽ መሙላታቸውን በስልጠናው የሚሳተፉ ተማሪዎች ይናገራሉ።ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የስልጠናውን አጀንዳዎች ያብራራል።

ካሁን ቀደም ምላሽ ያላገኘው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጥያቄ በቅድሚያ ምላሽ ሊሰጥበት ይገባል የሚል ተቃውሞ መነሳቱን ይኽው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ተናግሯል። ተማሪው ስልጠና የሚሰጥባቸው አካባቢዎች በፌዴራል ፖሊስ መከበባቸውንና ተማሪዎች ከቅጥር ግቢው መውጣት መከልከላቸውንም ገልጿል። ተማሪው እንዳለው በስልጠናው የሚሳተፉ ተማሪዎች የተሰጣቸውን የስልጠና ሰነድ በማቃጠል ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

Demonstration der Semayawi-Partei in Addis Ababa Äthiopien 22.09.2013
ምስል DW

ካልተመዘገቡና ካልተሳተፉ በመጪው አመት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የጀመሩትን ትምህርት ለመቀጠል እንደማይችሉም ጨምረው ተናግረዋል።

ተቃዋሚው የፖለቲካ ፓርቲ ሰማያዊ ፓርቲ ባለፈው ሳምንት ይህን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በስልጠና አመካኝቶ የራሱን አስተሳሰብና ርዕዮተ ዓለም በተማሪዎች ላይ እየጫነ መሆኑን አስታውቋል።የፓርቲው ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ ስለሺ ፈይሳ ስልጠናውን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት የትምህርት ተቋማት ከፖለቲካ ጫና ነፃ መሆን እንዳለባቸው ይናገራሉ።እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ አገሪቱ ካለችበት አስቸጋሪ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አኳያ ይህን አይነት ስልጠና ትልቅ ወጪ የሚጠይቅ ስለሆነ ከየትኛው በጀት ተወስዶ እየተካሄደ መሆኑ ግልጽ ስላልሆነ ሃብት ማባከን ነው ።

መንግስት በበኩል ሥልጠናው በግዳጅ የሚስጥ እንዳልሆነና የትምህርት ነጻነትን እንደማይጋፋ ነው ያስታወቀው ። በአምቦ፤ ወለጋ፤መዳወላቡና ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች ተቃውሞዎች አሉ ቢባልም አቶ ሬድዋን ሁሴን ግን የፖሊሲ ስልጠናው ያለምንም እንከን እየተካሄደ መሆኑን ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ባሉ ከ30 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ከስምንት መቶ ሺ በላይ ተማሪዎች በስልጠናው እንደሚሳተፉ ተገልጿል ።

መርጋ ዮናስ

ነጋሽ መሐመድ