1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አማርኛ ቋንቋን ከባዕድ ቋንቋ የመቀላቀል አባዜ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 3 2006

ተማርን የሚሉ ሰዎች አማርኛን ቋንቋ ዉስጥ አንዳንድ የእንግሊዘኛ ቋንቋን እየሰነቀሩ ቋንቋዉ እንዲመነምን እየዳረጉ ናቸዉ ይላሉ ምሁራን። በሌላ በኩል ሃሳብን ለመግለፅ አማርኛ ቋንቋ አስቸጋሪ ነዉ የሚሉም አልጠፉም!የባዕድ ቃላትን የመዋስ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፤ እንግሊዘኛ ቃላትን ጣል እያደረጉ የመናገር አባዜ የተለመደ ይመስላል

https://p.dw.com/p/1CZSe
Traditioneller Tanz in Addis Abeba Äthiopien
ምስል DW/A. Tadesse-Hahn

አሁን አሁን በተለይ በከተሜዉ አካባቢ የሚገኙ በርካታ ወላጆችም ልጆቻቸዉ ከአማርኛ ይልቅ በእንግሊዘኛ ትምህርት የሚሰጥበት ት/ ቤት ልጆቻቸዉን አስገብተዉ ልጆቻቸዉ እንግሊዘኛ ጣል እያደረጉ ሲነጋገሩ ሲሰምዋቸዉ እጅግ የሚኮሩ ጥቂቶች እንዳሆኑ ይሰማል። እዉነት የባዕድ ቋንቋን ጣል እያደረጉ ማዉራት ዘመናዊነት ነዉን ወይስ ዘመናዊ ትምህርትን እንደቀመሱ ማመላከቻ ? ከባዕድ ቋንቋ የምናመጣዉን ቃል ከትዉልድ ቋንቋችን ስንቀላቅል እዉነት ትርጉሙ ከባህላችን አንጻር ተቀባይነት እንዳለዉስ እንመረምራለን? በዕለቱ ዝግጅታችን ምሁራንን አነጋግረን ጥንቅር ይዘናል።
ዓለም በቴክኖሎጂ በተራቀቀበት በአሁኑ ዘመን ምንም እንኳ የቋንቋ መወራረስ እጅግ ቢኖርም በሃገራችን እየታየ ያለውን ግን ቋንቋ እንደሌለው በሰው ሀገር ቋንቋ የመናገር ልምድ በፍጥነት በመዛመት ላይ ይመስላል፡፡ ይህ አኩሪ ማንነታችንን መርሳት በመሆኑ ይህን ችግር ለመቅረፍ የበኩላችንን አስተዋጾ ማድረግ ይኖርብናል ያሉን፤ በሥነ-ግጥምና አጫጭር ልብ ወለዶችን በመፃፍ የሚታወቁት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የቋንቋ እና ሥነ-ጽሁፍ መምህር ዶር በድሉ ዋቅጅራ፤ አሳሳቢ ጉዳይ ነዉ ሲሉ ገልፀዋል።
ዘመናዊ ቴክኖሎጂና እድገትን ተከትለዉ የመጡ የባዕድ ቃላትን የመዉሰድ የመዋስ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፤ እንግሊዘኛ ቃላትን ጣል እያደረጉ የመናገር አባዜ የተለመደ ይመስላል ያሉን በአዲስ አበባ የፎክሎር ትምህርት ክፍል የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ፤ አቶ ገዛኸኝ ፀጋዉ፤ በበኩላቸዉ እንደስልጣኔ ምልክት እየታየ መትዋል፤ ለእንግሊዘኛ ቋንቋ የተለየ ግምት እየተሰጠ ነዉ ሲሉ ገልፀዋል።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሞያ አቶ ታደለ ጀማል፤ የአፍ መፍቻ ቋንቋን የመቀላቀል ልምዱ ሊወገድ የሚገባ ነዉ። እንዲያም ሆኖ ግን አስፈላጊ ቦታዎች ላይ መጠቀሙም የግድ ነዉ ሲሉ ይገልፃሉ።
ሀገርን ለማስጎብኘት፤ እና ሀገር ጎብኝዎችን ወደ ሀገር ለመሳብ፤ ለመግባብያ በርግጥ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን ማወቁ የማይታበል ጉዳይ በመሆኑ አስጎብኝ ድርጅቶች በዚህ ረገድ ሥልጠናን ይወስዳሉ፤ ያሉን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሞያዉ አቶ ታደለ፤ አስጎብኝ ባለሞያዎቹ በየቋንቋዉ ስልጠና ይሰጣቸዋል ሲሉ ገልፀዋል።
በአዲስ አበባ ከተሞች ላይ የሚታዩት አንዳንድ ማስታወቅያዎች የማኅበረሰቡን ባህል ማዕከል ያላደረጉ እና ተቆጣጣሪ ያልጎበኛቸዉ ናቸዉ ያሉን የቋንቋ እና ሥነ-ጽሁፍ መምህሩ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ፤ በሀገሪቱ የሚገኙ አብዛኞቹ የብዙሃን መገናኛዎችም ቢሆኑ፤ ቋንቋን በመቀላቀሉ ጉዳይ ድጋፍ እየሰጡ ይመስላል።
በአሁኑ ወቅት ባህልን የመጠበቅ መርህ ስለማይታይ በተለይ በተለይ የብዙሃን መገናኛዎች ለኅዝብ ጆሮና እይታ የሚያደርስዋቸዉ ዝግጅቶች ሊጠንባቸዉ ይገባል ሲሉ፤ ዶክተር በድሉ በማከል ገልፀዋል።
ይህን ችግር ለመቅረፍ፤ የሀገርን ባህል እና ሥነ-ምግባርን ለመጠበቅ የኅብረተሰቡ መንፈሳዊ ጤንነት እንዳይታወክ ምን መደረግ ይኖርበታል ማንንስ ማሳሰብያ መስጠት ይቻላል? ለሚለዉ የተደነገገ ፖሊሲ መኖር ይኖርበታል። አይመቼ ቃላትን የመጠቀሙን ነገር ለመቆጣጠር የባህል ሚኒስቴር ተጠያቂ ይመስለኛል ሲሉ ነግረዉናል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሞያዉ አቶ ታደለ ጀማል ሥራ ቤታቸዉ ይህን አይነቱን ችግር ለመቅረፍ የቋንቋ ፖሊሲ በመቀረፅ ላይ፤ ነዉ ። ወጥ የሆነ አሰራር እየተመቻቸ መሆኑን ነግረዉናል።
እንድያም ሆኖ ይላሉ፤ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሞያዉ አቶ ታደለ ጀማል ኅብረተሰቡ ቋንቋዉን ባህሉንን እና ማኅበረሰባዊ ሥነ-ምግባሩን ህግና ደንብን ጠብቆ ብቻ ሳይሆን መጠበቅ ያለበት በተለይ የብዙሃን መገናኛዎች እና ባለሞያዎች ነዋሪዉ ግንዛቤ እንዲያገኝ ማስተማር ይኖርባቸዋል።
ከዓለም ሀገራት ህዝቦች ጋር ለመቀራረብ፤ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ማህበራዊና ባህላዊ እድገት ለማምጣትም ዓለም አቀፍ ቋንቋን ማወቁ እጅግ አስፈላጊነቱ ባይካድም፤ ከትውልድ ሲወራረስ የኖረን የአፍ መፍቻ ቋንቋን መጠቀም እና ማዳበር ሊታሰብበት ይገባል በማለት፤ ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማኅደሩን በመጫን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

Kinder in Äthiopien
ምስል UNO
Hauptcampus der Universität Addis Abeba AAU
ምስል DW


አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ