1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ናይጀሪያዉያን ተማሪዎች ከታገቱ መቶ ቀን

ረቡዕ፣ ሐምሌ 16 2006

ናይጀሪያ ዉስጥ የሚንቀሳቀሰዉ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን ቦኮሃራም በሰሜን ምሥራቅ የሃገሪቱ ክፍል ከሚገኘዉ ቦርኖ ግዛት ከ200 የሚበልጡ ታዳጊ ሴት ተማሪዎችን አግቶ ከወሰደ 100 ቀን ሞላዉ። ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2009ዓ,ም ጀምሮ ከ10,000 ሕዝብ በላይ ከፈጀዉ ከዚህ ቡድን እስካሁን ልጆቹን ማስለቀቅ ባለመቻሉ የናይጀሪያ የጦር ኃይል ይተቻል።

https://p.dw.com/p/1ChLS
Schulklasse in den Gwoza-Bergen
ምስል privat

ቡድኑ በጥቅሉ 276 ልጃገረዶችን ያገተ ሲሆን ዓለም ዓቀፍ ዉግዘት ከየአቅጣጫዉ ቢወርድበትም ጠፍተዉ መምጣታቸዉ ከሚነገርላቸዉ በቀር የተቀሩትን አሁንም በቁጥጥሩ ሥር እንደያዘ ነዉ። የሀገሪቱ ፕሬዝደንትም ቸል ብለዋል በሚል ይወቀሳሉ።

ባለፈዉ ሚያዝያ ወር በ6 ለሰባት አጥቢያ ቦርኖ ግዛት ቺቦክ ቀበሌ ወደሚገኘዉ የመንግስት የሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ደጃፍ ላይ ተሽከርካሪዎች ተደረደሩ። የእስላማዊ ታጣቂዉ ቦኮ ሃራም አባላትም ወደየክፍሎቹ ተቻኩለዉ በመግባት እድሜያቸዉ ከ12 እስከ 18ዓመት የሚሆን ወደ300 የሚሆኑትን ታዳጊ ሴቶች ተሽከርካሪዉ ላይ ጭነዉ ከአካባቢዉ ተሰወሩ። የቦርኖ ሀገረ ገዢ ዘግየት አሉና በታጣቂዎቹ እጅ የሚገኙት 129 እንደሆኑ፤ 52ቱ ማምለጥ እንደቻሉ ተናገሩ። ወላጆቻቸዉ መንግስት ከዛሬ ነገ ልጆቻችንን አስጥሎ ያመጣልናል በሚል ተስፋ ቢጠባበቁም ይህ ነዉ የሚባል የተጨበጠ ነገር አላገኙም። በዉድቅት ከተኙበት ታፍሰዉ የተወሰዱት ልጆችም ላለፉት አንድ መቶ ቀናት በቦኮሃራም የሽብር ቀንበር ሥር እንደወደቁ ነዉ። በእነዚህ ቀናትም ልጆቻቸዉ ከታገቱባቸዉ ወላጆች 11ዱ ህይወታቸዉ አልፏል። አሁን በህይወት ካሉት ወናጆች አንዷም ከእንግዲህ ለነፍሳቸዉ እንደማይሳሱ ነዉ የሚናገሩት።

Nigeria Protest Boko Haram Entführung
ምስል picture-alliance/AP Photo

«እገታዉ ከተፈጸመበት ጊዜ አንስቶ እየተሰቃየሁ ነዉ። እንደዉም እንደእኔ ምንም ነገር ይምጣ፤ በመሣሪያ የሚያስፈራራኝ ሰዉ ቢመጣ እንኳ ምን አይገደኝም። ብሞትም እንኳን ግድ የለኝም።»

ገና በግንቦት ወር ነበር የመንግስት የሀገሪቱ የጦር መኮንን ጀነራል አሌክስ ባዴህ ለጋዜጠኞች ጦሩ ተማሪዎቹ የት እንደሚገኙ እንደሚያዉቅ የገለፁት። ዝርዝሩን ግን መናገር እንደማይችሉም ጭምር። ቀደሚ ሲል የናይጀሪያ የስለላ ኃይሎች ቦኮሃራም ልጃገረዶቹን በቀጥታ ወደካሜሮን አሻግሯል የሚል ግምት ነበራቸዉ። በመቀጠል ልጆቹ በሰሜን ምሥራቅ ናይጀሪያ ሳምቢሳ ደን ዉስጥ ሸሽጓቸዋል የሚል መረጃ ወጣ። ያም ሆኖ ይሄም መረጃ ቢሆን እስከዛሬ የተጨበጠ ነገር የለም። የመብት ተሟጋች የሆኑት ጂቦ ኢብራሂም በሁኔታዉ ከሚያዝኑት አንዱ ናቸዉ፤

Brasilien Fußball WM 2014 Fotos von AFP-Fotograf Jewel Samad Nigeria Fan
ምስል Jewel Samad/AFP/Getty Images

«መንግስት ልጃገረዶቹ በመሃሉ ነፍሳቸዉ እንዳይጠፋ እነሱን ለማስለቀቅ ሲባል ምንም ዓይነት ወታደራዊ ጥቃት ለመሰንዘር አልፈልግም ብሏል። እናም ወታደራዊ ኃይል አማራጭ ካልሆነ ችግሩን ለመፍታት ዉይይት ከቡድኑ ጋ መካሄድ ይኖርበታል። ወይስ መንግስት ልጆቹ በዚህ ሁኔታ በቡድኑ ቁጥጥር ሥር እንዲኖሩ ይችላሉ ብሎ ያምናል

«ልጆቻችንን መልሱ» የተሰኘዉ ዓለም ዓቀፍ ዘመቻ የተጀመረዉ የቺቦክ ቀበሌ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆኑት ልጃገረዶች በታጣቂዎቹ እጅ በወደቁ በጥቂት ቀናት ዉስጥ ነዉ። በማኅበራዊ መገናኛ በስፋት የተዳረሰዉ ይህ መልዕክት የአሜሪካን ፕሬዝደንት ባለቤት ቀዳማይት እመቤት ሚሼል ኦባማን ጨምሮ ብዙዎችን አሳትፏል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ቀይ የለበሱ ወላጆች ቺቦክ አደባባይ ላይ ወጥተዉ መንግስትም ሆነ ሌሎች ሃገራት ልጆቻቸዉን በማዳኑ እንዲረዱ ጠይቀዋል። የቦኮሃራም መሪ መሆኑ የተገለጸዉ አቡባከር ሼኹ ደግሞ በቪዲዮ መልዕክት ልጆቹ የሃይማኖት ትምህርት እየተማሩ እንደሆነና ለባርነትም ሊሸጧቸዉ እንደሆነ መግለፃቸዉም ከሀገር ዉስጥ ብቻ ሳይሆን ከዉጭም ትኩረት ሳበ። የተመድ ጠለፋዉ አወገዘ፤ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይና ዩናይትድ ስቴትስም አስፈላጊዉን መሳሪያ በመያዝ በፍለጋዉ ለመተባበሩ ተነሱ። ቻይናና እስራኤልም በየግላቸዉ ለትብብሩ እጃቸዉን ዘረጉ። በዚህ ጊዜ ሁሉ ግን የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ጉድላክ ጆነተን የተናገሩት ነገር አልነበረም። እንደዉም ወደቺቦክ ለማድረግ ያሰቡትን የጉብኝት ጉዞ መሰረዛቸዉ በወቅቱ ትችት አስከትሎባቸዋል። ፓሪስ ላይ የተሰባሰቡት ናይጀሪያና ጎረቤት ቤኒን፣ ቻድ፣ ካሜሮንና ኒዠር ቦኮሃራምን በጋራ ለመዋጋት ቢዝቱም እስካሁን ግን ይህ ነዉ የሚባል ዉጤት አይታየም። የልብ ልብ ያገኘ የሚመስለዉ ታጣቂ ቡድንም ጨምሮ ሌሎችን አግቶ መዉሰዱ ተሰማ። ጥቃቱንም አጠናክሮ በመቀጠሉም መንደር ማቃጠል ህይወት ማጥፋቱን ገፋበት። ቦርኖ በተባለችዉ ግዛት ብቻም ባለፉት ሶስት ዓመታት የምዕራባዉያን የትምህርት ማዕከል በሚል የሚነቅፋቸዉን 176 መምህራንን ሲገድል 900 ትምህርት ቤቶችን አዉድሟል። ፕሬዝደንት ጉድላክ ጆነተንም ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሸሹት እንዳልነበረ ልጆቻቸዉ የታገቱባቸዉን ቤተዘመዶች ለማግኘት መድፈራቸዉ ተሰምቷል። ልጆቹ ዛሬም የት እና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የሚያዉቀዉ ቦኮ ሃራም ብቻ ነዉ። የአሜሪካ ሰዉ አልባ የስለላ አዉሮፕላኖች መሰማራታቸዉ ቢነገርም ያዩትና የደረሱበት አልተሰማም ወይም ለህዝብ ይፋ አልሆነም።

Goodluck Jonathan spricht mit entkommenen Geiseln
ምስል Wole Emmanuel/AFP/Getty Images

ሽቴፈኒ ዱክሽታይን

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ