1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቱርካውያንና የአውሮፓ ፍርድ ቤት ውሳኔ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 15 2006

የአውሮፓ ህብረት ፍርድ ቤት ባለፈው ሰሞን በጀርመን የቪዛ አሰጣጥ ህግ በተለይም ቱርኮችን በሚመለከተው ደንብ ላይ ያሳለፈው ብይን ቱርካውያንን አስደስቷል ። በአንፃሩ አንዳንድ የጀርመን ፖለቲከኞችን ቅር አሰንኝቷል ።

https://p.dw.com/p/1Cgol
Sprachkurs Migranten Symbolbild
ምስል picture-alliance/dpa

ቱርካዊቷ ወይዘሮ ኔይመ ዶጋን ባለፈው ዓመት የባለቤታቸው መኖሪያ ወደ ሆነው ወደ ጀርመን ለመሄድ ቪዛ ቢጠይቁም አልተፈቀደላቸውም ። በወቅቱ የተሰጣቸው ምክንያት መሰረታዊ የጀርመንኛ ቋንቋ ዕውቀት ከሌላቸው በስተቀር ጀርመን ወዳሉት ባለቤታቸው መሄድ እንደማይችሉ ነበር ። ምንም እንኳን ባለቤታቸው ለbርካታ ዓመታት ጀርመን የኖሩና ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ቢሆንም በጀርመን ህግ ወይዘሮ ኔይመ ዶጋን ጀርመንኛ መናገር እስካልሞከሩ ድረስ ጀርመን ውስጥ ከባለቤታቸው ጋር መኖር አይችሉም ። ጀርመን እጎአ ከ2007 ዓም ጀምሮ ከቱርክና ከሌሎችም የሶሶተኛው ዓለም ሃገራት ለኑሮ ወደ ጀርመን የሚመጡ የትዳር አጋሮች ወደ ጀርመን ከመምጣታቸው በፊት ቢያንስ በጀርመንኛ መግባባት የሚያስችላቸው መሰረታዊ የቋንቋ ችሎታ እንዲኖራቸው ያስገድዳል ። የችሎታቸው ማረጋገጫ የሆነውን የቋንቋ ፈተናንም ባሉበት ሃገር ማለፍ ይጠበቅባቸዋል ። ፈተናውን ካላለፉ ቪዛ ይከለከላሉ ። እንደገና ለሌላ ፈተና መዘጋጀት ይኖርባቸዋል ። ወይዘሮ ኔይመ በቋንቋ ምክንያት ከባለቤታቸው ተለያይተው እንዲኖሩ ያደረጋቸውን ይህን የጀርመን የቪዛ አሰጣጥ ደንብ በመቃወም ጉዳዩን ወደ አውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወስደው ባለፈው ሰሞን ረተዋል ።

Symbolbild Händedruck Handschlag Hand reichen Integration
ምስል imago/imagebroker

ፍርድ ቤቱ ባሳለፈው ብይን ጀርመን ከዛሬ 7 ዓመት ጀምሮ ሥራ ላይ ያዋለችው በትዳር ምክንያት ወደ ጀርመን ለሚመጡ የውጭ ዜጎች ያስቀመጠችው ቋንቋ የመማር ቅድመ ግዴታ በተለይ በቱርካውያን ላይ ሊሰራ እንደማይችል ፈርዷል ። ፍርድ ቤቱ እንዳለው የጀርመን የቪዛ አሰጣጥ መርህ የአውሮፓ ህብረት እጎአ በ1970 ዎቹ ከቱርክ ጋር ከተፈራረመው የአውሮፓ ህብረት የትብብር ስምምነት ጋር የሚጋጭ ነው ። ፍርድ ቤቱ ቋንቋን የመሰሉ ገደቦች የቤተሰብን በአንድ ላይ መሰባሰብ አስቸጋሪ ያደርጋል ። ብይኑ ጀርመን የሚኖሩ የቱርክ ማህበረሰብ አባላትን አስፈንድቋል ። ፍርድ ቤቱ ባሳለፈው ብይን ላይ የጀርመን ፖለቲከኞች የተለያዩ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል ። ብይኑን የደገፉ የተቃወሙም አሉ ።የውጭ ዜጎች ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርበው የሚኖሩበት መንገድ የሚመለከተው የጀርመን የውህደት ጉዳዮች መሥሪያ ቤት ሃላፊ ኤይዳን ኦዞጉዝ ባለትዳሮች በቋንቋ ምክንያት ተለያይተው መኖራቸውን አይደግፉም ።ሆኖም እርሳቸው እንደሚሉት ጀርመን በቋሚነት ለመኖር ያሰበ ሰው ጀርመንኛ ቋንቋ ማወቁ አስፈላጊ ነው ።

« እንደሚመስለኝ ጀርመን ውስጥ ያሉ ወይም ከቱርክ የትዳር አጋሮቻቸውን ማምጣት የሚፈልጉ እስካሁን ቋንቋ የት ማማር እንዳለባቸውም ሲፈልጉ የቆዩ ሰዎች ሁሉ በዚህ ውሳኔ በጣም ይደሰታሉ ብዬ አምናለሁ ። ርግጥ ቋንቋ በጣም አስፈላጊ ነው ።በዚህ ጉዳይ ላይ ያለመግባባት ሊኖር አይገባም ። ሆኖም በዚህ ወጣት ባለትዳሮች አብረው መኖር መቻላቸው መወሰኑ በርግጥ ከባድ ነው ። »

Staatsministerin für Migration und Flüchtlinge Aydan Özoguz
ምስል picture-alliance/dpa

አንዳንድ የጀርመን ባለሥልጣናት በፍርድ ቤቱ ውሳኔ አዝነዋል ። ከነዚህ አንዱ የወግ አጥባቂው የጀርመን ክርስቲያን ዲሞክራት ህብረት ፓርቲ አባል የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ጉንተር ክሪንግስ ናቸው ። በርሳቸው አስተያየት ቋንቋ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀርርቦና ተመሳስሎ ለመኖር አስፈላጊ በመሆኑ ነው የጀርመን መንግሥት ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር ጀርመን በቋሚነት ለመኖር ለሚፈልጉ የውጭ ዜጎች ቢያንስ መሰረታዊ የቋንቋ እውቀት እንዲኖራቸው ያስገደደው ። የጀርመን መንግሥት እንደሚለው የቋንቋ ችሎታን ቪዛ ለመስጠት ግዴታ ያደረገው የውጭ ዜጎች ከጀርመናውያን ጋር ተቀራርበውና ና ተግባብተው እንዲኖሩ ለማገዝ ብቻ ሳይሆን የግዳጅ ጋብቻዎችንም ለመከላከል ጭምር ነው ።ኤይዳን ኦዞጉዝም ጀርመን ውስጥ ቋንቋ የማወቅ አስፈላጊነትን አጉልተው ነው የሚናገሩት ።ይሁንና ከባዱ ነገር ይላሉ ኦዞጉዝ አመልካቾች ፈተናውን ከወደቁ በኋላ ወደ የትዳር አጋራቸው ወደ ሚኖርበት ጀርመን እንዳይገቡ መከልከላቸው ነው ።

« እዚህ የሚመጣ ሁሉ ጀርመኝኛ ማወቅ አለበት ።ይህን ሳያደርግ እዚህ የሚመጣም ሆነ እዚህ የሚኖር ዋጋ የለውም ። ለኛ ጀርመንኛ ማወቅ አስፈላጊም ጥሩም ጉዳይ ነው ። ይሁንና እስካሁን እኛ እንዳደረግነው ፈተና አላለፍክም ተብሎ ባለቤቷ ወዳለበት አትሄጂም ብሎ መገደብ መጥፎ ፍርድ ነው ። ወጣት ባለትዳሮች አብረው መሆን አይችሉም የሚለውን መቃወማችን ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ ። »

Symbolbild Hamburg Islam
ምስል picture-alliance/dpa

ሶሻል ዲሞክራትዋ ኦዙጉዝ እንደሚሉት ምንም እንኳን የጀርመን መንግሥት የውጭ ዜጎች ጀርመንኛ እንዲማሩ የሚፈልግ ቢሆንም ፣ መሠረታዊ የነበረው የቋንቋ ፈተና እንዲቀር መበየኑ በጀርመን የውጭ ዜጎች ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ በመኖር ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አያደርግም ። ኦዙጉዝ ይህን ሲሉ የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የሚመሩት የወግ አጥባቂው የክርስቲያን ዲሞክራት ህብረት ፓርቲ በምህፃሩ CDU አባላት ፍርድ ቤቱ ያሳለፈውን ውሳኔ ተቃውመዋል። እህት ፓርቲው የክርስቲያን ሶሻል ህብረትም እንደ CDUው ምክትል የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪንግስ ሁሉ ብይኑን ተችቷል ። የፓርቲው አባል ሽቴፋን ማየር የውጭ ዜጎች ከህብረተሰቡ ጋር በተሳካ ሁኔታ እንዲቀራረቡ ቢያንስ መሰረታዊ የቋንቋ ችሎታ እጅግ አስፈላጊ ነው ይላሉ ።በጀርመን ምክር ቤት የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበርና ና የCDU አንጋፋ ፖለቲከኛ ቮልፍጋንግ ቦስባህ ባለፈው ሰሞኑ ውሳኔ ማዘናቸውን ገልፀዋል ።ለአንድ ደረ ገፅ በሰጡት አስተያየት ህጉን የሚቃወም ውሳኔ ቢተላለፍም እጎአ ከ2007 አንስቶ ህጉ ተግባራዊ የሆነበትን ምክንያት ግን አይለውጠውም ነው ያሉት ። ወግ አጥባቂዎቹ በውሳኔው ሲያዝኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ ደንቡ ውድቅ በመደረጉ ተደስተዋል ።የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ መሪ ሴም ኦዝዴሚር የቋንቋ እውቀት ለተሳካ መቀራረብ በመሠረቱ አስፈላጊ መሆኑን ያምናሉ። ሆኖም ለዚህ ሲባል ግን ባለትዳሮች መለያየት የለባቸውም ሲሉ ነው የሚከራከሩት ።ስለዚህም

Migranten und Migrantinnen
ምስል picture-alliance/dpa

ይላሉ ከተራ ግንዛቤም ተነስተንም ቢሆን ከልምድም ስናየው ባለትዳሮች ተለያይተው እንዳይኖሩ ወደ ጀርመን የሚመጡት የትዳር አጋሮች እዚሁ ቋንቋ እንዲማሩ ቢደረግ ነው ይሻላል ይላሉ ።የአውሮፓ ሃገራት የትዳር አጋሮች ከሶስተኛው ዓለም ወደ ጀርመን እንዲመጡ ከሚፈቅዱባቸው ተመሳሳይ መስፈርቶች ውስጥ አንዱ በአውሮፓ የሚገኘው የትዳር አጋር የገንዘብ አቅም ነው ።ሆኖም የሃገሪውን ቋንቋ መጠቀምን እንደ ቅድመ ግዴታ የምታስቀምጠው ጀርመን ብቻ አይደለችም ። ሌሎችም የአውሮፓ ህብረት ሃገራት ተመሳሳይ ህግ አላቸው ። ለምሳሌ ብሪታኒያም እንደ ጀርመን በትዳር ምክንያት ወደ ሃገርዋ ለሚሄዱ የውጭ ዜጎች ቋንቋን ማወቅን የሚያስገድድ መስፈርት አላት ። ኔዘርላንድስም እንደዚሁ በተመሳሰኢe ምክንያትወደ ሃገርዋ ለሚመጡ የውጭ ዜጎች የደች ቀንቋ ፈተና ትሰጣለች ። ፈተናው የሚሰጠውም አመልካቾቹ በሚገኙበት ሃገር ኤምባሲ ነው ።በዴንማርክ ደግሞ በትዳር ወደ ሃገሪቱ የሄዱ የውጭ ዜጎች በተመዘገቡ በ6 ወራት ውስጥ የዴንማርክ ቋንቋ የቃል ፈተና ይሰጣቸዋል ። ፈተናውን ያላለፉ ከሶስት ወር በኋላ እንደገና እንዲፈተኑ ይደረጋል ። ታዲያ በድጋሚ ከወደቁ ግን የመኖሪያ ፈቃዳቸውን ይቀማሉ ። ያለፈው ሰሞኑ የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብይን የሚመለከተውው በትዳር ምክንያት ከቱርክ ለሚመጡት እንጂ ሌሎች የቋንቋ ግዴታ መስፈርት የተጣለባቸውን የሌሎችአገራት ዜጎችን አይደለም ። ከሌሎች ሃገራት የሚመጡ በተለይ የቋንቋ ፈተና የመውሰድ ግዴታ የተቀመጠባቸው ሃገራት ዜጎች አሁንም ፈተናውን ካላለፉ ቪዛ እንደማይሰጣቸው የጀርመን መንግሥት አስታውቋል ።

ሂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ