1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መደረግ ያለበት

ዓርብ፣ የካቲት 13 2007

ተሐዋሲው አለ ተብሎ ሲጠረጠር በቅድሚያ በፍጥነት ሐኪም ማናገር ይገባል።

https://p.dw.com/p/1EejT
Ebola Screening JFK Flughafen USA
ምስል picture alliance/Landov

በጀርመን ሀገር የሚገኘው ሮበርት ኮህ የተሰኘው ተቋም ኢቦላን ለመመርመር የሚከተሉትን መመሪያዎች አዘጋጅቷል።

ኅመምተኛው ትኩሳት ካለበት (የሰውነት የሙቀት መጠኑ ከ38.5°Cካለፈ) አለያም የሙቀት መጠኑ ከፍ ካለ (የሰውነት የሙቀት መጠኑ ከ37.5°Cካለፈ) ተቅማጥ፣ ማቅለሽለሽ እና ትውከት ካሳየ፦

ያኔ ከሚከተሉት አንደኛው ድምዳሜ ላይ ሊደረስ ይገባል፤

ኅመምተኛው

  • በኢቦላ ከተጠቃ ሰው ጋር፣ ኢቦላ ሊኖርበት ይችላል ተብሎ ከተጠረጠረ ሰው ወይንም የበሽታው ቀዳሚ ምልክቶች ከመታየታቸው በፊት ባሉት 21 ቀናት ውስጥ በኢቦላ የተነሳ ሞቷል ተብሎ ከተጠረጠረ ሰው ጋር ንክኪ ፈጥሯል።

ወይንም

  • ኅመምተኛው በኢቦላ ከተጠቃ ግለሰብ አለያም የበሽታው ቀዳሚ ምልክቶች ከመታየታቸው በፊት ባሉት 21 ቀናት ውስጥ ተሐዋሲው ካለባቸው ሰዎች ደም እና የሰውነት ፈሳሾች ጋር ቀጥተኝ ግንኙነት ሊኖር ይችላል ተብሎ በሚገመትባቸው የቤተ-ሙከራዎች፣ ሐኪም ቤቶች ወይንም መሰል ቦታዎች ውስጥ ይሰራ ነበር።

አለያም

  • የበሽታው ቀዳሚ ምልክቶች ከመታየታቸው በፊት ባሉት 21 ቀናት ውስጥ ኢቦላ በወረርሽኝ መልክ ወደ ተዛመተባቸው ሃገራት (ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ጊኒ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ) ተጉዟል ወይንም የአንዱ ሀገር ነዋሪ ነበር። እናም በቆይታው ፍራፍሬ የሚመገቡ የሌሊት ወፎችን ወይንም የዝንጀሮን አለያም የሌላ አይነት የዱር አውሬን ሥጋ ተመግቧል አለያም ከእንስሳቱ ጋር ንክኪ ፈጥሯል።

እነዚህ ድምዳሜዎች ላይ ከተደረሰ ያኔ ግለሰቡ በፍጥነት ሐኪም ሊያናግር ይገባል፤ በአካባቢው የሚገኝ የጤና ተቋም ጽ/ቤትም ማወቅ ይኖርበታል። ተሐዋሲው ወረርሽኝ በሆነባቸው ሃገራት ውስጥ ስለኢቦላ መረጃ የሚሰጥ የ24 ሰዓት የስልክ አገልግሎት ተመቻችቷል። የደወለው ሰው የኢቦላ በሽታ ምልክት ያለበት ከሆነ የጤና ባለሙያዎቹ ምርመራው እና ሕክምናው እንዴት እና የት እንደሚደረግ ይወስናሉ። ለጤና ባለሙያዎች እና ሐኪሞች ሀቀኛ እና የተብራሩ መልሶችን መስጠት እጅግ ወሳኝ ነው። በጊዜ ምርመራ ተደርጎ በሽታው ከታወቀ ኅመምተኛው በሕይወት የመትረፍ ዕድሉ የተሻለ ይሆናል።

ኢቦላን በተመለከተ የስልክ አገልግሎት
ኢቦላን በተመለከተ የስልክ አገልግሎትምስል DW/A. Kriesch

በዚህ ደረጃ ታዲያ የኢቦላ ተሐዋሲ የተገኘበት ግለሰብ በተቻለ መጠን ከሌሎች ሰዎች ጋር መጨባበጥ፣ መሳሳም እና ወሲብ መፈፀም የመሳሰሉትን ማናቸውንም አይነት የሰውነት ንክኪዎችን ማድረግ አይኖርበትም።

ከሰዎች ላይ የሚወሰዱ የደም፣ የምራቅ እና የሽንት ናሙናዎች የኢቦላ ተሐዋሲ እንዳለባቸው ማረጋገጫ ለማግኘት ደረጃቸውን ወደ ጠበቁ፣ ደኅንነታቸው እጅግ በከፍተኛ ደረጃ ወደተጠበቀ ቤተሙከራዎች በጥንቃቄ መላክ ይኖርባቸዋል።