1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቦኮ ሀራም እና ያካባቢ ሀገራት ስጋት

ረቡዕ፣ ጥር 13 2007

የናይጀሪያው ፅንፈኛ ቡድን ቦኮ ሀራም የሽብር ተግባሩን ከሰሜናዊ ናይጀሪያ አልፎ አሁን ወደ ጎረቤት ሀገራት ማስፋፋት መጀመሩ ባካባቢው ትልቅ ስጋት ፈጠረ። በናይጀሪያ ስለቀጠለው የቡድኑ ጥቃት ትናንት የመከረው የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ቡድኑ ለጠቅላላ ምዕራብ እና ማዕከላይ አፍሪቃ ትልቅ አደጋ መደቀኑን አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/1ENqs
Nigeria Boko Haram Terrorist
ምስል picture alliance/AP Photo

የቡድኑ ጥቃትም በናይጀሪያ ብዙ የሀገሪቱን ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው እንዳፈናቀለ እና ለከፋ ሁኔታ እንዳጋለጠ ካካባቢው የሚወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል። የአሸባሪውን ቡድን እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ተንታኞች እንደጠቆሙት፣ ቦኮ ሀራም በናይጀሪያ እና በጎረቤት ሀገራት ያስፋፋውን ሽብር እና የስደተኞቹን ችግር ለማብቃት አንድ ያካባቢ ሀገራት የጋራ ስልት ያስፈልጋል።


ቦኮ ሀራም በሰሜናዊ ናይጀሪያ ባካሄደው ጥቃቱ በስብዕና ላይ ወንጀል ሳይፈፅም እንዳልቀረ ነው የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ያስታወቀው። የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የቦኮ ሀራምን ሽብር በተመለከተ ይህን ዓይነት ጠንካራ መግለጫ ሲሰጥ የትናንቱ የመጀመሪያ ጊዜ ነው። የቦኮ ሀራምን ጥቃት ለመከላከል ሳይዘገዩ ትብብር መጀመር እንደሚኖርባቸው የተገነዘቡት እና ትናንት በኒዠር አስተናጋጅነት በመዲናይቱ ኒያሜ የተሰበሰቡት የምዕራብ አፍሪቃ መንግስታት የኤኮኖሚ ማህበረሰብ ፣ የኤኮዋስ አባል የሆኑት የቤኒን፣ ካሜሩን፣ ኢኳቶርያል ጊኒ እና የቻድ የውጭ እና የመከላከያ ሚንስትሮች አንድ የጋራ ስልት ማውጣት ስለሚችሉበት ጉዳይ መክረዋል። ይህንን ለማሳካትም ባስቸካይ አንድ ልዩ ኃይል ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን የኒዠር ውጭ ጉዳይ ሚንስትር መሀመድ ባዙም አስታውቀዋል።
« አንድ ብሔራት አቀፍ የጦር ኃይል ለማቋቋም ሁላችንም በተጨባጭ መንቀሳቀስ ይኖርብናል። ይኸው ጦር ከመጀመሪያው አንስቶ በጥንካሬ መንቀሳቀስ እንዲችል በቂ ወታደሮች እና መሳሪያ ሊኖሩት ይገባል። »
እንደሚታወሰው፣ እነዚሁ መንግሥታት ባለፉት የመፀው ወራት 3,000 ወታደሮች የሚጠቃለሉበት ጦር ለማቋቋም ቢስማሙም፣ እስካሁን በዚሁ ረገድ የተፈፀመ ነገር የለም። ቦኮ ሀራም ጥቃቱን ወደ ጎረቤት ካሜሩን አስፋፍቶ ወደ 80 የሚጠጉ ሰዎችን ካገተ በኋላ ካሜሩንን ለመርዳት ቻድ ሰሞኑን 400 ወታደሮች ከማሰማራቷ በስተቀር ሌላ ርምጃ አልተወሰደም።
በትናንቱ የኒያሜ ስብሰባ የአውሮጳ ህብረት እና የጀርመን ተወካዮችም የተገኙ ሲሆን፣ አፍሪቃውያኑ መንግሥታት በቦኮ ሀራም አንፃር ሊያቋቁሙት ላሰቡት እና በአፍሪቃ ህብረት እዝ ስር ሊውል የሚችል ልዩ ጦር የአውሮጳ ህብረት ሊተባበራቸው እንደሚችል በወቅቱ የኤኮዋስ ሊቀመንበርነት የያዘችው የጋና ፕሬዚደንት ጆን ድራማኒ ማሀማ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
« ከዓለም አቀፍ አጋሮቻችን የትጥቅ እና ስንቅ፣ እንዲሁም፣ የፊናንስ ድጋፍ ያስፈልገናል ብየ አስባለሁ። አውሮጳ ውያን ወታደሮች በሰሜናዊ ናይጀሪያ መሰማራት አይኖርባቸውም፣ ያካባቢ ሀገራት ፀረ ቦኮ ሀራምን ትግል ማካሄድ የሚችሉ በቂ ወታደሮች ማሰማራት ይችላሉ። »
እስካሁን የቦኮ ሀራም ጥቃት የ13,000 ሰው ሕይወት ሲቀጥፍ፣ በይፋ ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጋ ሰውም ከቤት ንብረቱ መፈናቀሉን መንግሥት አስታውቋል። የርዳታ ድርጅቶች እንደሚገምቱት ግን፣ የስደተኛው እና ተፈናቃዩ ቁጥር 1.5 ሚልዮን ይደርሳል። ተፈናቃዮቹን የማስተናገዱ ሁኔታ ከናይጀሪያ መንግሥት አቅም በላይ በመሆኑ ትልቅ ችግር ላይ እንደሚገኙም ነው የርዳታ ድርጅቶቹ የሚናገሩት። በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉት ለጊዜው በተዘጋጁ እና እጅግ በተጨናነቁ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ እስካሁን ከመንግሥት አስፈላጊውን በቂ ርዳታ እንዳላገኙ ተናግረዋል። ከተፈናቃዮቹ መካከል ብዙዎቹ ሴቶች እና ሕፃናት ይገኙባቸዋል። ቦኮ ሀራም በሰሜናዊ ናይጀሪያ ከተቆጣጠራቸው መንደሮች የሸሹ በመቶ የሚቆጠሩ ስደተኞች የአራት ሳምንት ሕፃን የያዙ ቤተሰብ ሳይቀሩ ካለፉት አምስት ወራት ወዲህ በመዲናይቱ አቡጃ በሚገኙ በፈራረሱ ሕንፃዎች ውስጥ ይገኛሉ። ብዙዎች የሚተኙበት ፍራሽ እንኳን እንደሌላቸው እና ባጠቃላይ በአዳጋች ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም አንዱ ተፈናቃይ ዛዲያ ዛይዱ ለዶይቸ ቬለ ገልጾዋል።
« ስራ የለንም፣ ምንም የለንም። ምን እንደምል አላውቅም። በጣም የሚያሳዝን ነው፣ መንግሥት ወደየመኖሪያ ቤታችን እንደንመለስ ማድረግ አለበት፣ አለበለዚያ ደግሞ እዚህ ባለንበት በሆነ መንገድ ሊረዳን ይገባል። »
በሌላ የአቡጃ ሰፈር የሚገኙ ሌሎች ተፈናቃዮችም እስካሁን ከመንግሥት ተገቢው ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው በተደጋጋሚ በቅሬታ ገልጸዋል፣ ይሁንና፣ የናይጀሪያ ብሔራዊው የአደጋ ጊዜ መከላከያ መስሪያ ቤት ስደተኞቹ የሰነዘሩትን ወቀሳ ሀሰት ሲል አስተባብለዋል።

Nigeria Borno Boko Haram Flüchtlinge 14.01.2015
ምስል picture-alliance/AA/Mohammed Abba
Kamerunische Soldaten an der Grenze zu Nigeria Archiv 12.11.2014
ምስል AFP/Getty Images/R. Kaze

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ