1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በግዳጅ ካገር ተባራሪዎች ማቆያ ጣቢያ በጀርመን

ሐሙስ፣ ኅዳር 11 2007

የአውሮጳ ዳኞች እስር ቤት የሚወረወሩ ተገን ጠያቂዎች ቁጥር አነስተኛ እንዲሆን ያደረጉት ጥረት በስተመጨረሻ ውጤት አስመዝግቧል። ሆኖም ለስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች የሚቆረቆረው፥ ኢየሱሳውያን በመባል የሚታወቀው የካቶሊክ ጽ/ቤት ይኽ በቅርቡ መቀየሩ አይቀርም ሲል ስጋቱን ገልጧል። ያን ሊቀይር የሚችል ሕግ በጀርመን ሚንስትሮች እየተመከረበት ነው።

https://p.dw.com/p/1DpPQ
ምስል SJ-Bild / Leopold Stübner

አባ ሉድገር ሒለብራንድ ተገደው ካገር የሚሰናበቱ ተገን ጠያቂዎች ወደሚገኙበት የበርሊኑ ማቆያ ጣቢያ ሰሞኑን እንደተለመደው አቅንተው ነበር። አባ ሉድገር ግራ የተጋባውን ከኤርትራ የመጣ የ21 ዓመት ወጣት ከእንግዲህ ማናገር አይችሉም። ወጣቱ ምንም እንኳ ጀርመን ውስጥ ኗሪ የሆነችው እህቱ ብትቀበለውም በቅርቡ ወደ ጣሊያን እንዲመለስ ተገዷል። በእርግጥ በአውሮጳ ሕግ መሠረት የቤተሰብ ዳግም ቅልቅል ተግባራዊ የሚሆነው ለአባት፣ ለእናት እና ለትንንሽ ልጆች ብቻ ነው። ለስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች የሚቆረቆረው ኢየሱሳውያን በመባል የሚታወቀው የካቶሊክ ጽ/ቤት በርሊን እና ብራንደርቡርግ ከተሞች ውስጥ ለ70 ካገር ተሰናባች ተገን ጠያቂዎች የሕግ አገልግሎት ድጋፍ በማድረግ በእዚህ ዓመት ብቻ 55ቱ ነፃ እንዲወጡ አስችሏል። አብዛኞቹ በግዳጅ ካገር ተሰናባች ተገን ጠያቂዎች ማቆያ ጣቢያዎች ባዶ ዅነዋል። ለስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች የሚቆረቆረው የካቶሊክ ጽ/ቤት ባልደረባ አባ ሉድገር ሒሌብራንድ።

«ተገደው ካገር የሚሰናበቱ ስደተኞች ቁጥር እጅጉን ቀንሷል፤ ለእዚህ ደግሞ ምክንያቱ ቀደም ሲል በሌላ የአውሮጳ ሀገር አሳብረው የጀርመንን ድንበር የረገጡ ተገን ጠያቂዎች ከእዚህ ዓመት አጋማሽ አንስቶ ሊታሰሩ እንደማይችሉ መጠቀሱ ነው። ቀደም ሲል ወደ 80 በመቶ ያኽል ተገን ጠያቂዎች ጀርመን በገቡ የመጀመሪያ ቀን ወደ እስር ቤት ይወረወሩ ስለነበር እስር ቤቶች የተጨናነቁ ነበሩ። ይኼ የሚገርም ነው።»

አባ ሉድገር ሒለብራንድ
አባ ሉድገር ሒለብራንድምስል SJ-Bild / Christian Ender

ጀርመን ውስጥ ተገን ጠያቂዎች ወደ የትም እንዳይንቀሳቀሱ ከሚዘጋባቸው ጣቢያዎች መካከል በርሊን ከተማ ኲዬፐኒክ የሚገኘው የተሰናባቾች ማቆያ የመጨረሻው ነው። ከአውሮጳ ኅብረት እና ከፌፌራል ጀርመን ከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ በርካታ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኙ የነበሩ ስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ ተደርገዋል። ሉክዘምበርግ የሚገኙ የአውሮጳ ዳኞች ተሰናባች ተገን ጠያቂዎች የእስራት ቅጣት ከተበየነባቸው ፍርደኞች ጋር በምንም መልኩ በአንድነት እንዳይታሰሩ ውሳኔ ካስተላለፉ ወራት ተቆጥረዋል። ለስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች የሚቆረቆረው የካቶሊክ ጽ/ቤት እንደሚገምተው ከሆነ ጀርመን ውስጥ በአምስት የተለያዩ አካባቢዎች ከ50 እስከ 60 የሚጠጉ ካገር ተሰናባች ተገን ጠያቂዎች ማቆያ ጣቢያዎች ይገኛሉ።

በርሊን ከተማ በሚገኘው በግዳጅ ካገር ተሰናባች ተገን ጠያቂዎች ማቆያ ግዙፍ ህንፃ ውስጥ 30 እስረኞች ይገኛሉ፥ በ50 ፖሊሶች በዐይነቁራኛ ይጠበቃሉ። ጣቢያው በዓመት 55,000 ዩሮ ያስወጣል። ሆቴል ውስጥ ቢሆኑ ኖሮ ወጪው ከእዚያ ያነሰ ይሆን ነበር ይላሉ አባ ሉድገር ሒለብራንድ። በርካታ ካገር ተሰናባች ተገን ጠያቂዎች በተደጋጋሚ ወደ ጀርመን መምጣታቸው የተለመደ ነው። ለአብነት ያኽል አባ ሉድገር ድጋፍ የሚሰጡት የሠርብ ስደተኛ ባለፈው ሣምንት ለአራተኛ ጊዜ በግዳጅ ከሀገር ተሰናብቷል።

Ein Flüchtling in der Abschiebungshaft
ምስል SJ-Bild / Leopold Stübner

እንደ አባ አባባል ከሆነ ስደተኛው ለአምስተኛ ጊዜ መምጣቱ አይቀርም። ሠርቢያ ደኅንነቷ የተጠበቀ ሀገር ተደርጋ ስለምትታይ ከእዚያ የሚመጣ ተገን ጠያቂ ተቀባይነት የማግኘት እድሉ ዜሮ ነው። እንዲያም ሆኖ ጀርመን ውስጥ ከሠርቢያ የመጡ ስደተኞች በግዳጅ ካገር ተሰናባች ተገን ጠያቂዎች ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ። ስደተኞቹ ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮጳን የረገጡት ቡልጋሪያ በመግባት ነበር። ቡልጋሪያ ውስጥ ደግሞ የስደተኞች አያያዝ እጅግ የከፋ መሆኑን ስደተኞቹ ይገልጣሉ። እናም ብዙዎቹ ከሶርያም የመጡትን ጨምሮ ወደ ቡልጋሪያ ከሚላኩ ወደ ሀገራቸው ቢመለሱ እንደሚመርጡ ነው የሚናገሩት። ካገር ተሰናባች ተገን ጠያቂዎች ማቆያ ጣቢያዎች ዳግም እንዲጨናነቁ ሊያደርግ የሚችል ሕግ ለወራቶች በሚንስትሮች እየተመከረበት ነው። በሚቀጥለው ወር የሚንስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ እንደሚሰጥበት ይጠበቃል። አባ ሉድገር። «እንግዲያው ቡልጋሪያን መርገጥ የማይችሉ ተገን ጠያቂ ሶሪያውያን ተመልሰው እስር ቤት ይወረወራሉ ማለት ነው። ሲበዛ ትርጉም አልባ፥ እጅግ ሲበዛ አስቂኝ ነገር ነው።»

ተገን ጠያቂዎችን እንደሚመለከተው ሕግ ከሆነ አንድ ስደተኛ ተገን ጠያቂ መሆን የሚችለው «ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ካለበት ነው።» በዓለም አቀፍ ደረጃ 51 ሚሊዮን ሰዎች ቀዬያቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ለስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች የሚቆረቆረው የካቶሊክ ጽ/ቤት ኃላፊ ፍሪዶ ፍሉይገር ገልጠዋል። 140,000 ያኽል ስደተኞች በአሁኑ ወቅት ጀርመን ውስጥ ይገኛሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ