1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ ጀርመን የሚገኙ ስደተኞች እጣ

ማክሰኞ፣ መስከረም 27 2007

በሺ የሚቆጠሩ ስደተኞች በየሳምንቱ በሊቢያ በኩል አድርገው ወደ አውሮጳ ለመግባት ይሞክራሉ። የአንዳንዶቹ እጣ ፋንታ በሜዲትሪያን ባህር ሰምጦ መሞት ሲሆን በህይወት የተረፉት ደግሞ በስፓኝ፣ በማልታ፣ በግሪክ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ በኢጣሊያ አድርገው ወደሰሜን አውሮጳ ለመግባት ይሞክራሉ።

https://p.dw.com/p/1DRAr
Verhaftung von Flüchtlingen auf dem Rosenheimer Bahnhof
ምስል DW/L. Abebe

ካለፈው ጥር ወር አንስቶ ከ100 000 በላይ ስደተኛ በተቀበለችው ጣሊያን በርካቶች የሥራም ይሁን የኑሮ ተስፋ ስለማይታያቸው ወዲያው ወደ ሌሎች በሰሜን አውሮጳ የሚገኙ ሃገራት መጓዙን መርጠዋል። ስለሆነም የጀርመን ፌደራላዊ ድንበር አስከባሪ ፖሊሶች ቁጥጥራቸውን አጠናክረው በየቀኑ በርካታ ስደተኞችን ደቡብ ጀርመን በምትገኘው ሮዝንሀይም ከተማ በቁጥጥር ሥር ያውላሉ።

ፖሊስ ሮኒ እና ፖሊስ ያኮ፤ ሥራ የሚጀምሩት ከጠዋቱ 11 ሰዓት ነው። ደቡብ ጀርመን፤ ሮዝንሀይም ከተማ በሚገኘው የፌደራል ድንበር አስከባሪ ፖሊስ ጣቢያ ያገለግላሉ። በጀርመን እና ኦስትሪያ ድንበር አቅራቢያ 30ኪ ሜ ስፋት ባለው አካባቢ ፤ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ጀርመን የሚገቡ አደንዛዥ እፆች፣ የጦር መሣሪያዎች እንዲሁም ሰዎችን ይፈልጋሉ።

Flüchtlinge in Rosenheim
ሮዝንሀይም ከተማ የሚገኘው የፌደራል ድንበር አስከባሪ ፖሊስ ጣቢያ በቀንምስል DW/L. Abebe

ውጭው ገና ጨለማ ነው። ወደ ደቡብ ጀርመን ዋና ከተማ ሙኒክ የሚያመራው አዉራ ጎዳና ላይ ግን በርካታ ተሽከርካሪዎች ይጓዛሉ። ብርማ ቀለም ባለው BMW መኪና ውስጥ የተቀመጡት ፖሊሶች አጥፍጠው አንድ ጥግ እንደቆሙ፤ አንድ የኢጣሊያ መለያ የሰሌዳ ቁጥር ያለው አውቶብስ ዐይናቸው ውስጥ ገባ፤ እነሱም ተከታትለው ሹፌሩ እንዲቆም ምልክት ሰጡት።

የደንብ ልብስ ያለበሱት ፖሊሶች መታወቂያቸውን ለአሽከርካሪዉ አሳይተው ወደ አውቶብሱ በመግባት እንቅልፍ የተጫጫናቸውን መንገደኞች መቆጣጠሩን ተያያዙ። አውቶብሱ ውስጥ ጥቂት አፍሪቃውያን ተቀምጠዋል። ከነዚህም ውስጥ ፖሊሶቹ ሁለቱን ይዘው ወረዱ። ናይጄሪያውያን ናቸው። አንደኛው ወደ ጀርመን የመጣሁት «መኪና ገዝቼ ወደ አፍሪቃ ልልክ ነው» አለ። የመጓጓዣ ሰነድ ማለትም (ፓስፖርት)ግን አልያዘም ፣ ከኢጣሊያ ያገኘው የመቆያ ወረቀትም ቢሆን ፖሊሶቹ አጣርተው ሲደርሱበት ጊዜው ያለፈ ነው። ፖሊሶቹ እንደሚሉት፤ « ይህ በጀርመን ሕግ መሠረት ወንጀል ነው።» ሌላኛው፤ ኬኔዲ እባላለሁ ያለው ናይጄሪያዊ ደግሞ ትንሽ ካመነታ በኋላ፤ ወደ ጀርመን የመጣሁበት ምክንያት አለ፤«ህይወቴን ለማሻሻል ወደእዚህ መጥቼ ጥገኝነት ብጠይቅ ያዋኛል ብዬ ነው አሰብኩ። በዚህ አጋጣሚ የጀርመን መንግሥት ያለሁበትን ሁኔታ ከግንዛቤ እንዲያስገባው እጠይቃለሁ። እኔ እዚህ የመጣሁት ዕርዳታ ለማግኘት ነው»

ኬኔዲ ፤ በሊቢያ አድርጎ ወደኢጣሊያ እንደተጓዘ ይናገራል። እሱ እንደሚለው ኢጣሊያ ለ 3 ዓመት ያህል ሲቀመጥ ሥራ ሊያገኝ እና ኑሮውን ሊያሻሽል አልቻለም። የጀርመን ፖሊሶች እሱን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸው ብዙም አልረበሸውም። ሆነም ቀረ ሙኒክ ሄዶ ጥገኝነት ለመጠየቅ በጉዞ ላይ እንደነበር ፤ ዘና ብሎ ያስረዳል።

ሁለቱም ናይጄሪያውያን፤ ሮዝንሀይም ከተማ ወደሚገኘው የፌደራል ድንበር አስከባሪ ፖሊስ ጣቢያ ሲደርሱ፤ የጣት አሻራ እና ሰፊ ቃለ መጠይቅ ይጠብቃቸዋል። ኋላም በአውሮፓ ከዚህ ቀደም አሻራ ሰጥተው መሆኑ ይጣራል። እነዚህን የሥራ ሂደቶች ፖሊሶቹ ከፈፀሙ በኋላ ቀጣዩ ኃላፊነት የስደተኞችን ጉዳይ የሚመለከተው የስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች ምክር ቤት ይሆናል።

Flüchtlinge in Rosenheim
ፖሊስ አሻራ ሲወስድምስል DW/L. Abebe

ነገር ግን ፖሊስ ጣቢያ ሲደረስ ሁሉም መጠበቅ ነበረባቸው። የሮኒ እና የያኮ ባልደረቦች፤ ሰባት የሶርያ ስደተኞን እና እነሱን ይዞ በመጓዝ ላይ የነበረ ደላላን በቁጥጥር ሥር አውለው ክፍሎቹ በሰዎች ተሞልተዋል። ፖሊስ ያኮ «አሁን አሁን የዕለት ከዕለት ውሎዋችን ብዙም አስደሳች አይደለም። ሁሉም ከአቅማችን በላይ ሆኗል። በየቀኑ ከ 20-30 ከዚያም በላይ የሆኑ ያለ ሕጋዊ ሰነድ ወደ ጀርመን የሚገቡ ሰዎች ያጋጥሙናል። ብዙዎቹ በባቡር የተወሰኑት ደግሞ በአውቶብስ ነው የሚመጡት ።

በመስከረም ወር ብቻ የሮዝንሀይም ፖሊሶች 700 የሚጠጉ ስደተኞችን ይዘዋል። አብዛኞቹ ከሶርያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ አፍጋኒስታን እና ናይጄሪያ የመጡ ናቸው። ወደጀርመን የተለያዩ ግዛቶችና ወደሰሜን አዉሮጳ ሃገራት የሚወስዱ እና ደቡብ ጀርመን ሮዝንሀይም ከተማ ላይ የሚገናኙ ሁለት ዋና መንገዶች አሉ። አንዱ በአፍጋኒስታን እና በባልካን ሀገራት አድርጎ ጣሊያን እና ኦስትሪያን አቋርጦ ወደ ጀርመን የሚያስገባ አዉራ ጎዳና፤ ሲሆን ሌላኛው ከአፍሪቃ በሜዲትራኒያን በኩል አድርጎ ወደ ኢጣሊያ እና ኦስትሪያ የሚወስደዉ ነው።

ሞሀመድ ኢድሪስ ከሳምንታት በፊት አንስቶ ከሮዝንሀይም ትንሽ ወጣ ብላ በምትገኘው ከተማ ፍራስዶርፍ ከሌሎች 14 ስደተኞች ጋር ይኖራል። ከሀገሩ ኤርትራ ተነስቶ በሱዳን በኩል አድርጎ ነው ሊቢያ የገባው።« ሊቢያ ዉስጥ ከባድ ነበር። ለአንድ ወር ያክል ታስሬ ነበር። ከዛም ከሊቢያ በባህር አድርገን ወደ ኢጣሊያ መጣን።»

ሮኒ እና ያኮ በሚሰሩበት ፖሊስ ጣቢያ ብቻ ካለፈው ጥር ወር አንስቶ ከ 5,800 በላይ ስደተኞች ተመዝግበዋል። በጎርጎሮሳዊዉ 2013 ዓ ም በጠቅላላ በፖሊስ ጣቢያዉ የተመዘገበው ስደተኛ ቁጥር 4000 ነበር። ይህ የሚያመለክተዉ በፖሊስ የተያዙትን ሲሆን በድብቅ የገቡት ስደተኞች ቁጥር ጥቂት እንደማይሆንም ይገመታል። ፖሊስ ሮኒ እና ያኮን የሚያሳስባቸው ግን በሕገ ወጥ መንገድ የገቡት ስደተኞች ብቻ ሳይሆኑ እነሱን ከሀገር ወደሀገር የሚያሸጋግሩ ደላላዎች ናቸው። በፖሊስ ጣቢያው ውስጥ ከ 60-80 የሚደርሱ በፖሊሶች ቁጥጥር ሥር የዋሉ የደላላ ተሽከርካሪዎች ቆመዋል። አብዛኞቹ ከኢጣሊያ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ የተለያየ የሰሜን አውሮፓ ሃገራት የሰሌዳ መለያ ያላቸው መኪናዎች ናቸው። የፖሊስ ጣቢያው ቃል አቀባይ ራልፍ ሻርፍ ቃላቸውን ከሰጡ ስደተኞች እንደሰሙት ደላሎቹ በሺ የሚቆጠር ገንዘብ ይጠይቃሉ።«ከአፍሪቃ የሜዲትራያንን ባህር ለማሻገር ከ 3,000- 30,000 ዶላር ይጠይቃሉ። ብዙ ሰዎች ለእነዚህ ሕገ ወጥ የሰዉ አሸጋጋሪ ደላላዎች ለመክፈል ሲሉ ያላቸውን ንብረት ያጣሉ። ከኢጣሊያ ወደ ጀርመን ወይም ስካንዴኔቪያን ሃገራት ለመውሰድ ደግሞ ወደ 500 እና700 ዶለር የሚጠይቁ አሉ።»

Flüchtlinge in Rosenheim
በፖሊሶች ቁጥጥር ሥር የዋሉ የደላላ ተሽከርካሪዎችምስል DW/L. Abebe

የ17 ዓመቱ ሶማሊያዊ አሊ አህመድ 3,000 ዶላር ለሕገ ወጥ ደላሎች እንደከፈለ ይናገራል። ሮዝንሀይም ከተማ ከገባ ገና ሶስት ሳምንቱ ነው።«ብዙ ሰዎች አሉ ገንዘብ ተቀብለው ሰዎችን ወደ አውሮፓ ለማሻገር የሚተባበሩ። ይህ ቀላል ነው። ቀላል ያልሆነው ነገር ግን ባህር ላይ መሞት አለ። እኔ ግን ዕደለኛ ስለነበርኩ ይሄው እዚህ አለሁ።

አሊ ጀርመን መቅረት ዓላማው አልነበረም። ወደ ኖርዌይ በጉዞ ላይ ሳለ ነው በጀርመን ፖሊስ የተያዘው። በኋላም ለመጀመሪያ ጊዜ አሻራ በሰጠበት ጀርመን ጥገኝነት ጠይቆ መኖር ጀምሯል።

ቀስ እያለ ለሮዝንሀይም የፌደራል ድንበር አስከባሪ ፖሊሶች እኩለ ቀን ሆነ። የጀርመን-ኦስትሪያን ድንበር ተሻግረው ፖሊሶቹ ፤ ከኦስትሪያ በኦይሮሲቲ 88 ፈጣን ባቡር ውስጥ ተሳፈሩ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የጀርመንን ድንበር ባቡሩ አቋረጠ። እነሱም ሥራቸውን ጀመሩ፤ፖሊሶቹ ገና ከኦስትሪያ ሲሳፈሩ በር ላይ አንድ ወጣት ሱዳኒያዊ ቆሟል። ፖሊሶቹ የደንብ ልብስ ባለመልበሳቸው ከጎኑ የቆሙት መንገደኞች ከጥቂት ደቂቃ በኋላ የጉዞ ሰነድ ወይም መታወቂያ እንዲያሳይ ሲጠይቁት ይበልጥ ግራ ለተጋባው አፍሪቃዊ ፤ የጀርመን ፖሊሶች መሆናቸውን በተደጋጋሚ ግልፅ ካደረጉ በኋላ መሣሪያም ሆነ ሌላ የሚጎዳ ነገር ይዞ እንደሁ ፈተሹት፤ ወጣቱ ግን በኪሱ ይዞት ከነበረ ወረቀት በስተቀር በኪሱ ምንም አላገኙም። ተቀያሪ ልብስ እንኳን አፍሪቃዊው አልያዘም። በኪሱ ስለተገኘው ወረቀት ፖሊስ ሮኒ ያስረዳሉ፤«ይህ የኦስትሪያ ፖሊስ ይዞት እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ዛሬ ምናልባትም የጣሊያንን ድንበር ተሻግሮ ኦስትሪያ እንደገባ ይዘዉት እንደነበር ያመላክታል። »

Karte Rosenheim Bayern Deutschland

ኦስትሪያ ከምትገኘው የኩፍሽታይን ከተማ የጀርመኗ ሮዝንሀይም ከተማ ለመድረስ በፈጣን ባቡር 20 ደቂቃ ይፈጃል። ሁለቱ ፖሊሶች ከዚሁ ባቡሩ ሌላ ተጨማሪ ሱዳናዊ ይዘው ሲወርዱ፤ ከባቡሩ ሙኒክ ከተማ የደረሰ መስሎት የወረደ አንድ ጋምቢያዊ ነኝ ያለ እና ምንም አይነት ማስተጃ ያልያዘ አፍሪቃዊን ጨምሮ፤ ሶስት ስደተኞችን በቁጥጥር ሥር አዋሉ። ፖሊሶቹ ከዚህም በላይ ያለ ሕጋዊ የይለፍ ሰነድ የሚጓዙ ባቡሩ ውስጥ ይኖራሉ በሚል ዕምነት፤ ሙኒክ ለሚገኙት ባልደረቦቻቸው መረጃ አስተላለፉ። ባቡሩ ቀጥሎ የሚቆመው እዛው ነው።ከዚሁ ባቡር ከኢጣሊያ የተሳፈሩ እና ሮዝንሀይም የወረዱ አንዲት ጀርመናዊት፤ ስደተኞቹ ስላሉበት አስከፊ ሁኔታ ጣልቃ ገብተው ይናገሩ ጀመር። «ደቡብ ቲሮል ቦልዛኖ ውስጥ በርካታ ሰዎች ባቡር ጣቢያ ተቀምጠዋል። ባቡሩ በሰው ተሞልቷል። በሙሉ ጥቁሮች ናቸው። እንደሚመስለኝ እየተደበቁ ነው። እንዳው በጣም የሚያሳዝን ነው።»ወ/ሮዋ እንባ ባቀረረ ዐይናቸው ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ስደተኞች አልፈው መንገዳቸውን ቀጠሉ።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ