1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዓረብኛ ፊደል የተገኙ የኢትዮጵያ የፅሁፍ ቅርሶች

ሐሙስ፣ መጋቢት 25 2006

የዓረብኛ ሥነ-ፅሁፍ በኢትዮጵያ በተሰኝባቀረብነዉ ዝግጅት ላይ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቋሚ ባልደረባ አቶ አህመድ ዘካርያ በኢትዮጵያ የተገኙት የዓረብኛ ሥነ-ፅሁፎች በዓረብኛ ፊደላት ይቀመጡ እንጂ ቋንቋዉ አገርኛ እንደሆነ በዝርዝር ገልፀዉልናል።

https://p.dw.com/p/1BaB5
Stadtmauer von Harar Stadt im Südosten von Äthiopien
ምስል Azeb Tadesse Hahn

በኢትዮጵያንና በአካባቢዋ የሚገኙ ሃገራትን የእሥልምና ሥነ-ፅሁፍ ይዘትንና ታሪካዊ ፋይዳዉን የሚቃኝ አንድ ዓለም አቀፍ ጥናታዊ ጉባኤ፤ አዲስ አበባ ዉስጥ መካሔዱን ተከትሎ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ በዓረብኛ ፊደላት የተፃፉ የተለያዩ የአገርኛ ቋንቋ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ሥነ-ፅሁፎች አጀም የሚል መጠርያ እንዳላቸዉ እንዲሁም በነዚህ ሥነ-ፅሁፎች ላይ በተለይ በቅርቡ ጥናትና ጥበቃ መጀመሩን ቃለ መጠይቅ ያደረግን ምሁራንን አነጋግረን ባቀረብነዉ የመጀመርያ ክፍል ዝግጅት ማድመጣችን ይታወሳል። በኢትዮጵያ ዉስጥ የተገኙት እና በተለያዩ አገርኛ ቋንቋዎች በዓረብኛ ፊደላት የተፃፉት ሥነ-ፅሁፎች በአብዛኛዉ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸዉ ብቻ እንዳልሆኑ የሚገልጹልን በኣዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ዉስጥ በምርምር ላይ የሚገኙት ዶክተር ከማል አብዱልዋሃብ፤ የዓረብኛ ሥነ-ፅሁፍ በሃገራችን ከሰባተኛዉ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንደገባ ገልፀዉልናል። በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የፊሎሎጊ ፋካሊቲ በኢትዮጵያ የተገኙ ጥንታዊ የዓረብኛ ሥነ- ፅሁፎችን በማሰባሰብ በሃገር አቀፍ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥናት ጥናት መጀመሩን ተነግሮአል።

የሐረር ከተማ የ«ሸሪፍ ሙዚየም» መስራችና ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱላሂ አሊ ሸሪፍ፤ በሐረር ከተማ እና አካባቢዋ የሚገኙ ጥንታዊ የዓረብኛ ስነ-ፅሁፎችን አሰባስበዉ ልዩ ጥበቃ በማድረጋቸዉ ይታወቃሉ። በሸሪፍ ቤተ-መዘክር ዉስጥ በአሁኑ ግዜ ከአንድ ሽ በላይ ጥንታዊ የእስልምና ሥነ ፅሁፎች መኖራቸዉ ተመልክቶአል። እነዚህ ጥንታዊ ፅሁፎች እስከዛሪ ጥበቃ አልተደረገላቸዉም የሚሉት በኣዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ዉስጥ በምርምር ላይ የሚገኙት ዶክተር ከማል አብዱልዋሃብ፤ አብዛኞቹ ጥንታዊ የዓረብኛ ሥነ-ፅሁፎች የተፃፉት በወረቀት ላይ ስለነበረም ቶሎ ለመጥፍት እና ለመበላሸት መዳረጋቸዉ ሌላዉ አንዱ ችግር ነዉ።

Markt Harar Äthiopien
ምስል Dr. Andreas Wetter

ባለፈዉ ሰሞን የፈረንሳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ጥናት ተቋም ከኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ጋር በመሆን በምሥራቅ አፍሪቃ ሙሥሊሞችና በዓረብኛ ሥነ-ፅሁፍ ላይ ጥናት ያደረጉ የተለያዩ ሐገራት ምሁራን ጥናታዊ ፅሁፋቸዉን ያቀረቡበትን ጉባኤ በማስመልከት ለሁለት ተከታታይ ሳምንታት የኢትዮጵያንና በአካባቢዉ የሚገኙ ሐገራትን የእሥልምና ሥነ-ፅሁፍን ይዘትና ታሪካዊ ፋይዳዉን የቃኘንበት ዝግጅታችንን ደመደምን። አድማጮች ስለዝግጅታችን ያላችሁን አስተያየት በተለመዱት አድራሻዎቻችን አድርሱን። ሙሉዉን ጥንቅር የድምጽ መከታተያዉን በመጫን ያድምጡ!

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሰ