1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኬንያ ፀረ ካንሰር ዛፍን የማዳን ጥረት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 22 2007

ለመድሃኒትነት የሚዉሉ በርካታ የእፅዋት ዓይነቶች መኖራቸዉ ይታወቃል። ከተክሎች የተቀመሙ መድሃኒቶችን መጠቀምም የተለመደ ነዉ። ለመድሃኒት የሚሆኑትን ተክሎች መንከባከቡ ግን ይጎድላል።

https://p.dw.com/p/1F00o
Fotoreportage Aberdare Kenia 2014
ምስል DW/H. Fischer

የዓለም የካንሰር ምርምር ተቋም ባወጣዉ መረጃ መሠረት በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012 ዓ,ም በወንድ ዘር ማመንጫ ላይ በሚከሰተዉ ካንሰር የተጠቁት ቁጥር ከ1,1 ሚሊዮን ይበልጣል። የበሽታዉ ሰለባዎች አብዛኞቹ በበለፀገዉ ምዕራቡ ዓለም ቢገኙም፤ መጠኑ ይነስ እንጂ አፍሪቃና እስያ የሚኖሩትም ለዚህ የተጋለጡ መሆናቸዉን ጥናቱ ያመለክታል።

ዶሮቲ ናያሚ እና ሜሪ ናያምቡራ የተባሉት ሁለቱ ኬንያዉያት ከሌሎች የተለየ የሚባል ኑሮ የሚገፉ አልነበሩም። አንደኛዋ የከተማ ሌላኛዋ የገጠር ኗሪዎች ናቸዉ። አንደኛዋ ወጣትና ለወደፊት በምርምሯ አንዳች ዉጤት ለማስመዝገብ የምትጥር ተማሪ ስትሆን አንደኛዋ ግን በሙያቸዉ የበኩላቸዉን አበርክተዉ አሁን ጡረታ ላይ ይገኛሉ። የሚገርመዉ አንዳቸዉ ከሌላኛቸዉ ጋ አይተዋወቁም። ሆኖም ግን የሚያስተሳስራቸዉና አንድ የሚያደርጋቸዉ ፖርኖስ አፍሪካና የተሰኘዉንና ፀረ ካንሰር መሆኑ የሚነገርለትን ዛፍ ከመጥፋት ለማዳን ያላቸዉ ቁርጠኝነት ነዉ።

የ23ዓመቷ ዶሮቲ ናያሚ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ የባዮ ኬሚስትሪ ተመራማሪ ናት። ለሁለተኛ ዲግሪዋ ዛፍ በዚህ የዉጭኛዉ አካል ማለትም ቅርፊት ወይም ልጥ ላይ ጥናትና ምርምሯን ታካሂዳለች። የዚህ ዛፍ ቅርፊት ለተለያዩ በሽታዎች በመድሃኒትነት ያገለግላል በተለይም የወንድ ዘር ማመንጫ ላይ ለሚከሰተዉ ካንሰር።

Fotoreportage Aberdare Kenia 2014
ምስል DW/H. Fischer

«ለካንሰር ህክምና የሚያገለግሉ የእጽዋት ዘሮች ላይ ጥናት ማድረግ ነዉ የእኔ ከፍተኛ ፍላጎት። እህቴን በጡት ካንሰር ምክንያት አጥቻለሁ። ከዚያ በኋላ ደግሞ እናቴ በማህፀን ካንሰር ምክያት ሞተች። ለዚህ ነዉ ካንሰር ላይ ምርምር የማድረግ ፍላጎት ያደረብኝ።»

ትላለች አሳዛኝ ታሪኳ ለምርምር እንዳነሳሳት የምትገልፀዉ ዶሮቲ። ወጣቷ ተመራማሪ የዛፉ ቅርፊት ለመድሃኒትነት እንዴት ጥቅም ላይ ሊዉል እንደሚችል ትመራመራለች። በወፍ ዘራሽ መንገድ በተፈጥሮ በበቀለዉ እና ለዚሁ ምርምር ተብሎ በሰዎች ተተክሎ ክብካቤ በሚደረግለት የዚህ ዛፍ ተክል መካከል ያለዉን አንድነትና ልዩነትም ታጠናለች። በዓለማችን ከሚገኙት እድሜያቸዉ ከስልሳ በላይ ከሞላ ወንዶች ከግማሽ የሚበልጡት የዘር ፍሬ ማመንጫ የአካላቸዉ ክፍል ችግር እንደሚገጥመዉ ጥናቶች ያመለክታሉ። እንደየዓለም የካንሰር ምርምር ተቋም መረጃ ከሆነም በመላዉ ዓለም ከተመዘገበዉ የዚህ ካንሰር ተጠቂዎች ቁጥር 68 በመቶዉ የሚሆኑት የበለፀጉ ሃገራት ኗሪዎች ናቸዉ። ዶሮቲን ምርምር የምታደርግበት ዛፍ መድሃኒትነቱ ባያነጋግርም፤ እንዴት ጥቅም ላይ የቢዉል እንደሚበጅ የምትመራመረዉ ወጣት ምሁር የጥናት ዉጤትም ለብዙዎቹ ጠቃሚነቱ አያነጋግርም። ሆኖም አሁን የዚህ ዛፍ ህልዉና ችግር የገጠመዉ ይመስላል። ዛፉ ከባህር ጠለል 1500 ሜትር በላይ በሆነ አካባቢ ብቻ ነዉ የሚበቅለዉ። ይህ ዛፍ በሚበቅልበት ስፍራ የሚኖሩ ወገኖች ይህን ዛፍ እየቆረጡ ለማገዶና ለቤት መሥሪያነት ይጠቀሙበታል። ከስሩ እየመነገሉ በመነቃቀልም የበቀለበትን መሬት ለእርሻ ተግባር ያዉላሉ። ከኬንያ የቆዳ ስፋት አንድ ሶስተኛዉ በደን የተሸፈነ እንደነበር ነዉ መረጃዎች የሚያመለክቱት። አሁን ግን ይህ ተመናመኖ ሰባት በመቶ የሚሆነዉ የደን ልባስ ብቻ ቀርቷል። ይህም ዛፎቹ በስሮቻቸዉ ይይዙት የነበረዉን ለም አፈር በንፋስና በዉኃ እንዲጠረግ እያጋለጠዉ ነዉ።

Fotoreportage Aberdare Kenia 2014
ምስል DW/H. Fischer

ወደኬንያ ተጉዛ ይህን ያስተዋለችዉ የዶቼ ቬለዋ ሂልከ ፊሸር ከናይሮቢ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አበርዳር ተራራ ወደሚገኝበት አካባቢ ተጉዛ ያገኘቻቸዉ ሜሪ ናያምቡራ ይህን ችግር በደንብ ተረድተዋል። ጡረታ ከመዉጣታቸዉ በፊት በዚህች አነስተኛ የገጠር መንደር በመምህርነት ያገለገሉት ሜሪ በልጅችነታቸዉ የሚያዉቁትን የአካባቢዉን ገፅታን ዛሬም አልዘነጉትም። ያኔ ደኑ ለመንደራቸዉ እጅግ ቅርብ ነበር። አሁን ግን ይህ ለካንሰር ጭምር መድሃኒት መሆኑ የሚነገርለትን ዛፍ ወደሚገኝበት የደን ስፍራ ለመድረስ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን መጓዝ ይጠበቅባቸዋል። ፖርኑስ አፍሪካና የተሰኘዉን ይህን ዛፍ ፍለጋም አብረዉ ወደደኑ ተጓዙ።

«የዛሬ ሃያ ዓመት ደኑ እጅግ ጥቅጥቅ ያለ ነበር። በዚያን ጊዜ ዝናብ በትክክለኛዉ የጊዜ ልዩነት ዝናብ ቶሎ ቶሎ ይመጣ ነበር። አሁን አሁን ግን የዝናብ እጥረት አለ፤ ያም በከፊል የደኑ መመንጠር ያስከተለዉ መዘዝ ነዉ። ይህም ለማኅበረሰባችን ትልቅ ችግር አስከትሏል። የምንተክለዉ አይበቅልም።»

ሜሪ ይህን የካንሰር መድሃኒት መሆኑ የሚነገርለትን ዛፍም ሆነ ሌሎቹን ከጥፋት ለማዳን የበኩላቸዉን እየሠሩ ነዉ። በጫካዉ ዉስጥ በሚዘዋወሩነት ጊዜ የዛፍ ችግኞችን እየሰበሰቡ በመዉሰድ በግላቸዉ ባዘጋጁት የአትክልት ስፍራ ላይ በመትከል ይንከባከባሉ። ይህ የሜሪ ናያምቡራ የአትክልት ስፍራ አስር ዓመት አስቆጥሯል። ተንከባክበዉ ያሳደጓቸዉን ዛፎች እየሸጡም ኑሯቸዉን ይደጉማሉ። እሳቸዉ እንደሚሉትም ለልጆቻቸዉ ትምህርት የሚሆን ገንዘብም ያጠራቅማሉ። የእሳቸዉን ተግባር እያስተዋሉ በትምህርት ተኮትኩተዉ የሚያድጉት ልጆቻቸዉም አንድ ቀን የተፈጥሮ አካባቢን የሚንከባከቡና ይህ ሊጠፋ የተቃረበ የመድሃኒት ዛፍ ዘርን ጨምሮ ሌሎች የእፅዋት ብዝሃ ህይወት ስብጥር ነፍስ አድኖች ይሆናሉ ብለዉ ተስፋ ያደርጋሉ።

Fotoreportage Aberdare Kenia 2014
ምስል DW/H. Fischer

«ግሪን ቤልት ሙቭመንት» የተሰኘዉ የኬንያ የአካባቢ ተፈጥሮ ተንከባካቢ ቡድን እንደሜሪ ያሉ ሰዎች በየግል የአካባቢ ተፈጥሮን ለመንከባከብ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ይደግፋል። ለጋ ተክሎችን በዋናነት ከእነዚህ ሰዎች የሚገዛዉም ቡድኑ ነዉ። የወደመዉን የደን ሃብት ለመመለስ አልሞ የሚንቀሳቀሰዉ ይህ ቡድን በገጠር ከሚኖሩና በየበኩላቸዉ ለአካባቢ ተፈጥሮ ልምላሜ ከሚሠሩት ጋም በትብብር መሥራት ይሻል። «ግሪን ቤልት ሙቭመንት» ለመድሃኒት የሚሆኑ እንደፑርኖስ አፍሪካና ያሉትን አገር በቀል ዛፎች ላለፉት 40 ዓመታት ጠቀሜታቸዉን እየገለፀ ጥበቃ እንዲደረግላቸዉ ሲያሳስብ ቆይቷል። ቻርለስ ሙዋንጊ የግሪን ቤልት ሙቭመንት ከፍተኛ የፕሮግራም መሪ እንዲህ ላሉ ሀገር በቀል ዛፎች ልዩ ትኩረት የሰጡበትን ምክንያት ያስረዳሉ።

«በሌሎች የዛፍ ዘሮች ላይ ጦጣዎችን አታይም። ይልቁንም እነሱ የሚገኙት በሀገር በቀል ዛፎች ላይ ነዉ። እነሱን ነዉ የሚያዉቁት ቤታቸዉ መኖሪያቸዉ ናቸዋ። እነሱን ብቻ ሳይሆን ሌሎች እንስሳትንም የምታገኛቸዉ በሀገር በቀል ዛፎች ላይ ነዉ እነሱን ነዉ የለመዷቸዉ። ለዚህም ነዉ እንደነዚህ ያዙ ዛፎች በይበልጥ ጥቅማቸዉ ታዉቆ እንዲጠበቁና የብዝሃ ህይወት ስብጥሩም እንዲሰፋ የምንሠራዉ።»

ሜሪ ናያምቡራም ሆኑ ሌሎች የዛፍ ችግኝ የሚያለሙ ወገኖች ባደራጁት የአትክልት ስፍራ ይህ ፀረ ካንሰር መሆኑ የተነገረለት የመድሃኒት ዛፍ ለስድስት ወራት ያህል በጥሩ ክብካቤ ካደገ በኋላ የኬንያ የተፈጥሮ አካባቢ ተንከባካቢ ቡድን «ሪን ቤልት ሙቭመንት» ለጋዉን ዛፍ ወደጫካ በመዉሰድ ይተክለዋል። ሃሳቡ መልሶ አካባቢዉን በሀገር በቀል ደን መሸፈን ነዉ። ሜሪም ደኑ ልክ እንደዛሬ ሃያ ዓመቱ ጥቅጥቅ ብሎ የማየት ምኞት አላቸዉ። ከናይሮቢ ብዙም ሳይርቅ በምትገኘዉ ትንሽ ከተማ መጉጋ አቅራቢያ ለምርምር የተተከሉ የፖርኖስ አፍሪካና ዛፍ ተክሎች የሚገኙበት ጣቢያ አለ።

በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ ምርምሯን በዚህ ዛፍ ላይ የምታካሂደዉ ዶሮቲ በጥንቃቄ ተተክሎ ተገቢዉ ክብካቤ ያልተጓደለበነትን ይህን ፖርኖስ አፍሪካና የተሰኘ የዛፍ ተክል የሚገኝበትን ስፍራ በየጊዜዉ ትጎበኛለች። ለቤተ ሙከራ ምርምርና ጥናቷ የሚሆናትን የዛፉን ቅርፊት ናሙናም ትወስዳለች። ምርምሯ የህክምናዉና መድሃኒቱን ዘርፍ ዉጤት ለማፋጠን ብቻ ሳይሆን በሚበቅልበት ቦታ ለሚኖሩ ወገኖችም እጅግ ጠቃሚ መሆኑ ይታመንበታል። እንደወጣቷ ተመራማሪ ሃሳብ ከሆነ ለገበሬዎቹ አዲስ የገቢ ምንጭ የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም።

Fotoreportage Aberdare Kenia 2014
ምስል DW/H. Fischer

«በወፍ ዘራሽ መንገድ የበቀለዉም ሆነ በእንዲህ ያለ መንገድ ተተክሎ የሚያድገዉ የዚህ ዛፍ ላይ የምናገኘዉ የመድሃኒትነት ጠቀሜታ ተመሳሳይ ከሆነ በሚበቅልበት ስፍራ ለሚኖሩ ገበሬዎች ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል። ይህም የመጥፋት አደጋ ያንዣበበትን የዚህ ዛፍ አይነቴ በየአካባቢያቸዉ እያባዙ ይጠብቁታል። ዛፎቹ ይበልጥ ከተባዙም የዛፎቹ ቅርፊት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለዉ ይታወቃልና፤ ገበሬዎቹ ለዉጭ ገበያ እንዲያቀርቡት ቅስቀሳችንን መቀጠል እንችላለን። ምክንያቱም ከእፅዋት ለሚቀመሙ መድሃኒቶች በአዉሮጳ ዝግጁ የሆነ ገበያ መኖሩ ግልፅ ነዉ።»

በጎርጎሪዮሳዊዉ የዘመን ቀመር በ1990ዎቹ ዉስጥ በየዓመቱ ከ3,000 እስከ 5,000 ቶን የሚገመት የፖርኖስ አፍሪካና ዛፍ ቅርፊት ከአፍሪቃ ወደፈረንሳይና ስፔን ይገባ ይላክ ነበር። በዚህ ወቅትም ነዉ እንዲህ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የመድሃኒት እጽዋት ንግድ በዓለም አቀፍ ደረጃ አፍሪቃ ያካሄደችዉ። አብዛኛዉም ከካሜሮን የተገኘ ነበር። ኬንያ እስከዛሬ ፖርኖስ አፍሪካናን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማቅረብ የሰባት ከመቶ ድርሻ ብቻ ነዉ ያላት። የጠፋዉን የደን ሃብት መልሶ መተካትና ዘላቂነት ያለዉ የዛፍ መትከልና ማብቀል ስልት መከተሉ የአካባቢ ተፈጥሮን አበልፅጎ በኬንያ ደጋማ አካባቢ የሚኖሩ ወገኖችን ሊጠቅም እንደሚችል ይታመናል። ከምንም በላይ ደግሞ በመላዉ ዓለም የዘር ፍሬ ማመንጫ አካላቸዉ በካንሰር ለተጠቃ ወንዶችም መፍትሄ ነዉ።

ሂልካ ፊሸር /ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ