1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኤቦላ ያልተደፈረችዉ ኮትዴቩዋር

ሐሙስ፣ ግንቦት 13 2007

ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2013ዓ,ም ታህሳስ ወር አንስቶ በምዕራብ አፍሪቃ ሶስት ሃገራት በኤቦላ ወረርሽኝ ከ11ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። አስቀድሞ የተጠናከረ ዉጤታማ ድጋፍ ቢደረግ ኖሮ የበርካቶችን ሕይወት ማዳን በተቻለ ነበር።

https://p.dw.com/p/1FTrQ
Aufklärungskampagne Ebola in Abidjan Elfenbeinküste 25.09.2014
ምስል Reuters/Luc Gnago

[No title]

የዓለም የጤና ድርጅት ወረርሽኙን በመዋጋትና በመከላከል ሂደት ከባድ ግድፈቶች መፈጸማቸዉን አምኗል። በዚህ ሁሉ የወረርሽኝ ቀዉስ መካከል የጊኒና የላይቤሪያ ቀጥተኛ ጎረቤት ኮትዲቩዋር ከኤቦላ ነፃ እንደሆነች ቆይታለች። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ሀገሪቱስ ምን ብታደርግ ነዉ ከዚህ ሕይወት ከሚያሳጣ አጣዳፊ ትኩሳት የተረፈችዉ? የኤቦላ ወረርሽኝ ስጋትስ በሕዝቡ የአኗኗር ስልት ላይ ምን ለዉጥ አስከተለ? የዶይቼ ቬለዋ ክላዉዲያ ሃይሰንበርግ የላከችዉ ዘገባ ይህን ይተነትናል።

«በሽታዉ ገዳይ ነዉ ብለዉናል። ለዚህ ነዉ ሁሉም ሰዉ መቀራረብ የተወዉ። ከጎረቤታችን ጋ ቢሆንም ማለት ነዉ። በተሐዋሲዉ ማን እንደተለከፈ ማወቅ አይቻልም፤ በሽታዉም ከየት ሊጋባበት እንደሚችል የሚያዉቅ የለም። ለዚህ ነዉ እንደድሮዉ ሰላምታ መለዋወጥ የተዉነዉ። የእጅ ሰላምታ የለም መተያየት ብቻ ነዉ። ጓደኛሽ በበሽታዉ ይያዝ አይያዝ አታዉቂም፤ ምናልባት ሊያጋባብሽ ይችላል። ይህ እኔን ያስፈራኛል። በየቦታዉ ሞትነዉ፤ እናም እያንዳንዳችን እሞታለን ብለን እንሰጋለን። ለዚህም ነዉ ጥንቃቄ የምናደርገዉ።»

Elfenbeinküste Leben in Zeiten von Ebola Schutzmaßnahmen
ምስል DW/C. Heissenberg

ማዳሜ ክራ ስለኤቦላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዜና ከሰሙበት ቀን አንስቶ የማይቀር አስፈላጊ ነገር ከሆነ ብቻ ነዉ ከቤት የሚወጡት። የዋና ከተማ አቢጃን ኗሪ ናቸዉ። ከምግብ ጠረጴዛቸዉ አጠገብ አንድ ፕላስክ የእጅ ማስታጠቢያ ዉኃ እንደሞላ፤ ከጎኑ ሳሙናና እላዩ በተፃፈዉ የህክምና መረጃ መሠረት 99 በመቶ በዐይን የማይታዩ ረቂቅ ተሐዋሲያንን የሚያጠፋ ፈሳሽ ተቀምጠዋል። ቢጫማዉ ፈሳሽ ንጥረነገር በመላዉ ሀገሪቱ በሚገኙ የእጅ መታጠቢያ ስፍራዎች፤ በየባንኮቹ መግቢያ፤ በየመሥሪያ ቤቱና የገበያ አዳራሾች መግቢያ፤ እንዳንዴም በየምግብ ቤቱ ጠረጴዛ ላይ በቲማቲም ድልህና ሰናፍጭ መካከልም ይገኛል። ምንም እንኳ ትህትና የጎደለዉ ቢሆንም ማዳሜ ክራ አምስት ልጆቻቸዉ ለሰላምታ ለሰዎች እንጃቸዉን እንዳይሰነዝሩ አስጠንቅቀዋል። ልደት ተጋብዘዉ ወደጓደኞቻቸዉ ቤት ሲሄዱም ቢቻል ምንም እንዳይበሉም መክረዋል። የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ጎረቤታቸዉ ዴዚሬ ኒያምባም ይስማማሉ።

«የመጀመሪያዉ መመሪያ፤ አንድ ሰዉ በተደጋጋሚ እጁን በደንብ መታጠብ ነዉ እና ከቤት ዉጪ የሚሄድ ከሆነም ረቂቅ ተሐዋሲያንን የሚገድለዉን ንጥረነገር መያዝ እና መጠቀም ነዉ። ከዚህ ሌላ የራሱን ምግብና መጠጥ እንዲመገብ፤ ከዚህ በፊት እንደለመድነዉም የራሱንም መመገቢያና መጠጪያዎችም ከሌሎች ጋ እንዳይጋራ የሚለዉን ሁሉ ያካትታል።»

ኤቦላ ኮትዴቩዋር ዉስጥ የሕዝቡን የአኗኗር ይዞታ ለዉጦታል። የተመ የሕፃናት መርጃ ድርጅት UNICEF የዉኃና የንፅሕና አጠባበቅ ዘርፍ ተጠሪ ዳንኤል ሽፓልትሆፍ ግን ለዉጡ ለበጎ ነዉ ይላሉ።

Elfenbeinküste Warnung vor Ebola in Abidjan Krankenhaus
ምስል Reuters

«እርግጥ ነዉ ኤቦላ ጥሩ ጎን አለዉ ብዬ ለመናገር አልደፍርም። ሆኖም ግን ባለፉት ዓመታት የሕብረተሰቡ እጅን በአግባቡ የመታጠብ ጥንቃቄ እንዲጎለብት ማድርጉ እዚህ UNICEF የምንገኘዉን አስደስቶናል። ምክንያቱም ያነዉ በከፍተኛ ደረጃ የሰዎችን ሕይወት ማትረፍ ያስቻለዉ።»

ከ16 ወራት በፊት በጎረቤት ጊኒና ላይቤሪያ ኃይለኛ ትኩሳት በሚያስከትለዉ በኤቦላ ተሐዋሲ ሰዎች የመሞታቸዉ ዜና እንደተሰማ ነበር የኮትዴቩዋር መንግሥት አፋጣኝ ርምጃ የወሰደዉ። ከጤና ዘርፍና ከአካባቢዉ ፖለቲከኞች የተዉጣጡ ልዑካን ወደገጠር የሀገሪቱ ክፍሎች በመሠማራት ስለበሽታዉ ሕዝባቸዉን አስተማሩ፤ አነቁ። ካለፈዉ ነሐሴ ወር አንስቶም በኤቦላ ከተጎዱት ሃገራት አዉሮፕላን በምድራቸዉ እንዳያርፍ አደረጉ፤ ድንበራቸዉንም ዘጉ።

አሁንም በመገናኛ ብዙሃን አስፈላጊ መረጃዎችና ስለበሽታዉ ጥርጣሬ ሲኖር በነፃ የጥሪ የሚቀበሉ ስልክ ቁጥሮች፤ በሽታዉን ለመከላከል ሊወሰዱ የሚገባቸዉ ርምጃዎች በየጊዜዉ ይሰራጫሉ። በአደን የተገኙ የሥጋ ምርቶችም ገበያ ላይ እንዳይዉሉ ታግዷል። በየገበያዉና ምግብ ቤቱ ድንገተኛ ፍተሻዎች በተደጋጋሚ ይካሄዳሉ። አንዳንዶች ስጋን መመገብ ማቆማቸዉን ይናገራሉ፤ አገር አስጎብኚዉ ሞቲ ቱሬ አንዱ ነዉ፤

Ebola Warnung Symbolbild
ምስል Reuters

«የፖሊሶችን ፍተሻ ተመልክቼያለሁ። ማቀዝቀዣ ዉስጥ እንዲሁም ድስቶች ሳይቀሩ ነዉ የአደን ሥጋ ገብቶ እንደሁ ሲፈትሹ የተመለከትኩት። ከዚህ በፊት እንደነበረዉ ኮትዴቩዋር ዉስጥ የዱር እንስሳትን ሥጋ የመመገቡ ልማድ አሁን መቅረቱን ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ። ሰዎች አሁን ዓሣ ወይም የበሬ ሥጋን ብቻ ነዉ መብላት የሚመርጡት፤ ምክንያቱም ፍራቻዉ አለ። መሞትን ይፈራሉ።»

ከወራት በፊት ታዋቂዉ የሀገሪቱ የድረገጽ ጸሐፊ ኢስራኤል ዮሮባ ኤቦላን የሚያወግዝ ዘፈን በኢንተርኔት አሰራጨ። ቪዲዮዉ አንድ ወጣት በአቢጃን ጎዳናዎች ላይ ሲሮጥ ያሳያል። በሽታዉ ከያዛችሁ ከባድ ትኩሳት እና መድማትን ያስከትላ እያለም ያዜማል። ተሐዋሲዉ አደገኛ ነዉ፤ ስለዚህ ለራስህ ጥንቃቄ አድርግ ከሌሎችም ጋ ተነጋገርበት። ምክንያቱም ሊገድልህ ይችላል በማለትም ያስጠነቅቃል።

ክላዉዲያ ሃይሰንበርግ / ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ