1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«በኢትዮጵያዊነቴ እጅግ እኮራለሁ» አርመኑ

ሐሙስ፣ መጋቢት 10 2007

«በቆዳ ቀለማችን ለየት ብንልም ልባችን ኢትዮጵያዊ ነዉ ፤ ኢትዮጵያን፤ ኢትዮጵያዉያንን በኔና በቤተሰቤ ስም በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ» ትዉልደ አርመኑን ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ ቫሄ ቲልብያን የዛሬ ወር ኢትዮጵያን፤ አፍሪቃን ብሎም አርሜንያን ወክሎ በግዙፉ የአዉሮጳ ሃገራት የሙዚቃ ዉድድር ላይ ሙዚቃ እንዲያቀርብ ተመርጦአል።

https://p.dw.com/p/1Et4e
Armenian-Ethiopian 2015 Eurovision Song Contest Vahe Tilbian
ኢትዮ አርመኑ ሙዚቀኛ ቫሄ ቲልብያንምስል Ruzanna Pilosyan_ Head of Press / Armenia, ESC 2015 Armenian

ከአራት ትዉልድ ጀምሮ ቤተሰቦቹ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚኖሩት ቫሄ ቲልብያን የፊታችን ግንቦት ወር የአዉሮጳ ሃገራት በየዓመቱ ሙዚቃ በሚወዳደሩበት ግዙፍ መድረክ «ይሮ ቪዥን ሶንግ ኮንቴስት» ላይ አርሜንያን ወክሎ ሙዚቃ እንዲያቀርብ ተመርጦ ዝግጅት ላይ ነዉ። በመሰንቆና ክራር የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች በሙዚቃ ቅንብሩ ማካተት የሚወደዉ ጎልማሳዉ ኢትዮ- አርመኑ ሙዚቀኛ አርሜንያን ወክሎ በግዙፉ የሙዚቃ መድረክ ይቅርብ እንጂ ትዉልድ ሃገሩን ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪቃን እንደሚወክል ነዉ የተዘገበዉ።

Logo Armenia “Genealogy” Eurovision 2015 Song
ምስል Ruzanna Pilosyan_ Head of Press / Armenia, ESC 2015 Armenian

ትዉልደ አርመናዊዉ ኢትዮጵያዊ ቫሄ ቲልብያን በቅርቡ ለአርመናዉያን ጆሮ ያደረሰዉ በመሰንቆ የተቀናበረዉ ጥንታዊና ታዋቂ የአርመን የህዝብ ሙዚቃን ለአድማጮች ጆሮ አድርሶአል።

የቫሄ ቲልብያን ወላጆች ጨምሮ ቅድም አያቶቹ ሁሉ የተወለዱት ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉ። እሱም እንደሌላዉ ኢትዮጵያዊ ሀ ሁ ን ቆጥሮ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ትምርቱን የተማረዉ እዝያዉ አዲስ አበባ ዉስጥ ሲሆን፤ በቆዳ ቀለም እንጂ ሃገራዊ ስሜቱና ባህሉ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ከልቡ ይናገራል፤ አርሜንያን ወክሎ በግዙፉ የዉድድር መድረክ ለመቅረብ ለልምምድ ወደ አርሜንያ መዲና የረቫን ያቀናዉም በኢትዮጵያ ፓስፖርት ነዉ። ግንቦት ወር ቬና ኦስትርያ ላይ በሚደረገዉ 60 ኛዉ የአዉሮጳ ሃገራት የሙዚቃ ማለት «ይሮ ቪዥን ሶንግ ኮንቴስት» ዉድድር ላይ የሚቀርበዉም የኢትዮጵያ ፓስፖርቱን ይዞ ነዉ ፤ በዚህም ሙዚቀኛ ቫሄ እጅግ መደሰቱንና ኩራት እንደሚሰማዉ ገልፆአል። ምናዊ ነህ ሲሉት ኢትዮጵያ አርመናዊ ነኝ ነዉ ሲል የሚመልሰዉ።

Armenian-Ethiopian, 2015 Eurovision Song Contest Vahe Tilbian Pass
ምስል Ruzanna Pilosyan_ Head of Press / Armenia, ESC 2015 Armenian

የአርመን ቋንቋን እና አማርኛን ትምህርት ቤት መማሩን እንዲሁም ከቤተሰቦቹ ጋር የሚነጋገርበት ቋንቋም በመሆኑ በጥራት ለማወቅ መቻሉን ገልፆአል።

በጎርጎረሳዉያኑ 1917 ዓ,ም በአንደኛዉ ዓለም ጦርነት ወቅት በአርመናዉያን ላይ የደረሰዉን ጭፍጨፋ በማምለጥ ወደተለያዩ ሃገሮች መሰደዳቸዉ ይታወቃል። ቤተሰቦቹ በኢትዮጵያ ሲኖሩ እሱ አራተኛ ትዉልድ እንደ ሆነ የሚናገረዉ ሙዚቀኛ ቫሄ ቲልብያን እንደሚለዉ ቤተሰቦች ወደ ኢትዮጵያ የገቡት እጅግ ጥንት መሆኑን ተናግሮአል።

በግዙፉ የአዉሮጳ ሃገራት የሙዚቃ ዉድድር አርመሜንያ በተለያዩ የዓለም ሃገራት ተበታትነዉ የሚገኙኑትን አርመናዉያን በፍቅር በሙዚቃ ለማገኛኘት ባቀደዉ መሰረት ከአምስት አህጉራት የተሰባሰቡ አምስት ሙዚቀኞች አንድ ከአርመንያ በአጠቃላይ ስድስት አርመናዉያን ሙዚቀኞች በአዉሮጳዉ የሙዚቃ ዉድድር መድረክ ለመቅረብ ተዘጋጅተዋል። አፍሪቃን ወክሎ የተመረጠዉ ትዉልደ አርመኑ ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ ቫሄ ቲልብያን፤ በርካታ ቋንቋዎችን ቢናገርም የዓለም ህዝቦች ቋንቋ ወደ ሆነዉ ወደ ሙዚቃ እንደሚያዳላ ይናገራል።

በአርመን ቋንቋ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ቅኝትን አካቶ በመሰንቆ የታጨወትኩት ሙዚቃ በአርመንያ እጅግ ተወዶልኛል፤ ስለ ኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያ መሰንቆም ብዙ ማብራርያ ሰጥቻለሁም ሲል ገልፆአል።

Armenian-Ethiopian 2015 Eurovision Song Contest Vahe Tilbian
ሙዚቀኛ ቫሄ ቲልብያን ከዘመን ባንድ ጋር አዲስ አበባምስል Ruzanna Pilosyan_ Head of Press / Armenia, ESC 2015 Armenian

Eurovision Song contest የተሰኘዉ የሙዚቃ ዉድድር አዉሮጻዉያን እርስ በርስ ጦርነትን አቁመዉ ለጋራ መተሳሰር እና መግባባትና በመደጋገፍ የጀመሩት ያጋራ መድረክ ሲሆን ሁለተኛ ዓለም ጦርነት በተጠናቀቀ በአስራ ሁለተኛ ዓመቱ እንደ አዉሮጻዉያን አቆጣጠር 1956 የአዉሮጻ የራድዮ ስርጭት ማህበር ለመጀመርያ ግዜ ያቋቋመዉ የሙዚቃ ዉድድር እንደሆነም ጽሁፎች ይጠቁማሉ። ነገሩ አዉሮጻዉያን ተሰኘ እንጂ የራድዮ ማህበር አባል ሃገራት ሁሉ የሚሳተፉበት ሲሆን የማህበሩ አባላት እስራኤልን የእስያ አገራትን እንዲሁም የሰሜን አፍሪቃ ሃገራትንም ያጠቃልል። እስከ ዛሪ በዚህ ዉድድር ከአፍሪቃ ሞሮኮ እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር 1980 ዓ.ም የተሳተፈች ሲሆን፤ ከአዉሮጻዉ የራድዩ ስርጭት ማህበር በዚህ የሙዚቃ ዉድድር እስከዛሪ ያልተሳተፉ ሃገራት አልጀርያ፤ ቱኒዚያ፤ ሊቢያ፤ ግብጽ ዮርዳኖስና ሊባኖን ይገኙበታል። የአዉሮጻ የራድዩ ስርጭት ማህበር አባላት በአጠቃላይ ሰባ አምስት ሲሆኑ ሃምሳ ስድስቱ አዉሮጻ ዉስጥ የሚገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ሰሜን አፍሪቃና እስያ ዉስጥ የሚገኙ ሃገሮች ናቸዉ። ዘንድሮ ለ 60ኛ ግዜ የሚደረገዉ የአዉሮጻዉ የሙዚቃ ዉድድር አዘጋጅ ኦስትርያ ስትሆን፤ ለዚህ ዝግጅት የተመረጠችዉ ባለፈዉ የአዉሮጻዉያኑ ዓመት የተዘጋጀዉን ዉድድር አሸናፊ በመሆንዋ ነበር።

በዚህ የዉድድር መድረክ አሸናፊዎች ወደ 80 ሽህ ይሮ እንደሚያገኙ ሲገለጽ በሌላ በኩል የተለያዩ የአዉሮጻ አገራት የተለያዩ ስራዎች እና የራድዮ ቃለ መጠይ በማድረግ እንዲሁም ራስን በማስተዋወቅ የሙዚቃ ስራቸዉን በመሸጥ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያገኙበት የዉድድር መድረክ ነዉ።

እጎአ 1965 አ.ም ለመጀመርያ ግዜ በኦስትርያ ሉጋኖ ዉስጥ የተካሄደዉ ይህ የአዉሮጻ የሙዚቃ ዉድድር መድረክ በዓለም ዙርያ ተወዳጅ የሆኑ ሙዚቀኞችን አፍርቶአል። ለምሳሌ በዓለም ታዋቂዋ የፖፕ የሙዚቃ ተጫዋች ሴሊን ዲዮን የአዉሮጻዉ የሙዚቃ የዉድድር መድረክ ለ 33ኛ ግዜ ባቀረበዉ የዉድድር መድረክ ላይ ተሳትፋ ባቀረበችዉ የፈረንሳይኛ ሙዚቃ ነዉ። በዓለም የሙዚቃ መድረክ ኮከብ ለመሆን የበቃችዉ።

Armenian-Ethiopian, 2015 Eurovision Song Contest Genealogy group
ከ 6 አህጉር የተሰባሰቡት አርሜንያን ወክለዉ የሚያዜሙት ሙዚቀኞችምስል Ruzanna Pilosyan_ Head of Press / Armenia, ESC 2015 Armenian

ABBA በመባል የታወቀው የስዊድን የፖፕ ሙዚቃ ባንድ አባላትም፤ እ ጎ አ በ1974 ዓ.ም፤ waterloo የተሰኘዉን ሙዚቃ አቅርበዉ በማሸነፍ ተደናቂነትን አግኝተዋል።

40 ሃገራት ለአሸናፊነት የሚወዳደሩበት ለ 60 ኛ ጊዜ የሚዘጋጀዉ የዘንድሮ የአዉሮጳ ሃገራት የሙዚቃ ዉድድር «ይሮ ቪዥን ሶንግ ኮንቴስት» የዛሬ ወር አዉስትርያ መዲና ቬና ዉስጥ በሚገኘዉ መዘጋጃ ቤት ይካሄዳል፤ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪቃን ወክሎ አርሜንያን አስቀድሞ የሙዚቃ ድግሱን ከሙዚቃ ባልንጀሮቹ ጋር ለማቅረብ የተዘጋጀዉን ትዉልደ አርመን ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ ቫሄ ቲልቢያንን በለስ ይቅናህ በማለት ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ