1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በናይጀሪያ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ቡሃሪ አሸነፉ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 22 2007

በናይጀሪያ ባለፈው የሳምንት መጨረሻ በተካሄደው ፕሬዚደንታዊ እና ምክር ቤታዊ ምርጫ የተቃዋሚዉ ወገን መሪ ጄኔራል ሙሃማዱ ቡሃሪ ማሸነፋቸዉ ተገለጸ። ስልጣን ላይ የነበሩት ፕሬዝደንት ጉድላክ ጆነተን ተቀናቃኛቸዉን በስልክ እንኳን ደስ ያልዎት ማለታቸዉ ተዘግቧል። ።

https://p.dw.com/p/1F0DJ
Mohammadu Buhari
ምስል Ekpei/AFP/Getty Images

ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ በዕጩነት ከቀረቡት 14 ተወዳዳሪዎች መካከል ጠንካራው ፉክክር የተካሄደው በፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታን እና በተቃውሞው ቡድን መሪ መሀማዱ ቡሀሪ መካከል ነው። እስካሁን በተቆጠረው የመራጮች ድምፅ በኋላ የተቃዋሚው ቡድን መሪ ሙሀማዱ ቡሀሪ በጠባብ የድምፅ ብልጫ በመምራት ላይ ይገኛሉ።

የሀገሪቱ ምርጫ ቦርድ እንዳስታወቀው፣ ከ36 የናይጀሪያ ፌዴራዊ ክፍላተ ሀገር መካከል እስካሁን በወቅቱ በ33 ቱ የመራጮች ድምፅ የተቆጠረ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት፣ ሙሥሊሙ የተቃዋሚው ቡድን፣ ማለትም፣ ጠቅላላ ህዝብ ኮንግረስ ፓርቲ ዕጩ መሀማዱ ቡሀሪ ተፎካካሪያቸውን የህዝብ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ፣ ፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታንን በጉልህ የድምፅ ብልጫ በመምራት ላይ ይገኛሉ። ጆናታን ግን ብዙ ደጋፊዎቻቸው በሚገኙበት ደቡብ ምሥራቃዊ ናይጀሪያ ሰፊ ድምፅ በማግኘታቸው ከቡሀሪ ጋ ያለውን ልዩነት ማጥበብ መቻላቸው ተገልጾዋል። የ72 ዓመቱ የቀድሞ ወታደራዊ መንግሥት መሪ ቡሀሪ በወቅቱ ጆናታንን በ500,000 የመራጮች ድምፅ ብቻ ነው እየመሩ የሚገኙት። ይሁንና፣ ብዙዎቹ የጉድላክ ጆናታን ደጋፊዎች በሚኖሩበት በደቡባዊ ናይጀሪያ የመራጭ ድምፅ ገና ተቆጥሮ እንዳላበቃ ነው የተገለጸው። ቆጠራው ዛሬ አብቅቶ የመጨረሻው ውጤት ይፋ በሚሆንበት ጊዜ በናይጀሪያ የስልጣን ለውጥ እንደሚኖር ብዙዎቹ በሰሜን ናይጀሪያ የሚገኙት የቡሀሪ ደጋፊዎች ተስፋቸውን እየገለጹ ነው።

Nigeria - nominierter Präsidentschaftskandidat Muhammadu Buhari und Goodluck Jonathan
ምስል U. Ekpei/AFP/Getty Images / AP Photo

« ቡሀሪ ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ነው የምንጠብቀው። ምክንያቱም በመላይቱ ሀገር ብዙ ደጋፊዎች አሉዋቸውና። እንደሰማነውም በመምራት ላይ እንገኛለን። »

በአፍሪቃ በህዝብ ብዛት ቀዳሚውን ቦታ በያዘችው ናይጀሪያ አንድ ዕጩ ፕሬዚደንታዊውን ምርጫ ያሸንፍ ዘንድ ከፍፁሙ የድምፅ ብልጫ ሌላ፣ ከ36 ቱ ፌዴራዊ ክፍላተ ሀገር መካከል ቢያንስ በሁለት ሶስተኛው 25% ድምፅ ማግኘት አለበት። ጉድላክ ጆናታንም ሆኑ መሀማዱ ቡሀሪ ለአሸናፊነት የሚያስፈልገውን አብላጫ ድምፅ ካላገኙ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በሚካሄደው ሁለተኛ ዙር አሸናፊው ይለያል።

ቡሀሪ ካሸነፉ ናይጀሪያ እአአ በ1999 ዓም ሥርዓተ ዴሞክራሲን ከተከለች ወዲህ የተቃውሞ ፓርቲ ድል ያገኘበት የመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል ማለት ነው። ቡሀሪ እአአ በ1984 ዓም በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ስልጣን በያዙበት አንድ ዓመት ሀገሪቱን ጥብቅ ቁጥጥር ይታይበት በነበረ አገዛዝ መምራታቸው ቢታወስም፣ ብዙ ናይጀሪያውያን ቡሀሪን በሙስና አንፃር የቆሙ አድርገው ነው የሚመለከቱዋቸው።

የምርጫውን ሂደት የተከታተሉት የፖለቲካ ተንታኞች እንዳስረዱት፣ ፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታን ፅንፈኛውን ቦኮ ሀራም በሀገሪቱ ያስፋፋውን የሽብር ጥቃት ያላበቁበት እና መሀማዱ ቡሀሪም ሙስናን ለማጥፋት የገቡት ቃል በመራጩ ህዝብ ውሳኔ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አሳርፈዋል።

ጆናታን በዋነኛ የነዳጅ ዘይት አምራች በሆነው የናይጀርያ ክፍለ ሀገር «ሪቨርስ» ከ95% የሚበልጥ የመራጭ ድምፅ ማግኘታቸው ትናንት ከተሰማ በኋላ ፣ የውጤቱን አስተማማኝነት የተጠራጠሩት የቡሀሪ ደጋፊዎች አደባባይ በመውጣት ተቃውሞ ከማሰማታቸው ጎን፣ ምርጫው እንዲደገም ሳይቀር ጠይቀው ነበር። ጥያቄአቸው ግን በምርጫ ቦርዱ ውድቅ አድርጎታል። ምርጫውን በታዛቢነት የተከታተሉት የአውሮጳ ህብረት ቡድን መሪ ሀና ሮበርትስ የምርጫው ሂደት ተጓታች እና ሥርዓት የጎደለው ከመሆኑ በስተቀር የማጭበርበር ተግባር እንዳልታየበት ነው ያስረዱት።

Nigeria Wahlbeobachter
ምስል DW/U. Musa

« የድምፅ አሰጣጡ ሂደት ባጠቃላይ ሥርዓት የጎደለው እና የተጓተተ ነበር። እርግጥ፣ የምርጫ ደንቦቹ ላይ በቂ ክትትል ባይደረግም፣ የአውሮጳ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ሆን ተብሎ የተካሄደ የማጭበርበር ድርጊት አልተመለከተም። »

የጉድላክ ጆናታን ፓርቲ ተወካይ የመራጮች ድምፅ ቆጠራው ሂደት ለቡሀሪ የወገነ ነው በሚል ተቃውሞ ካሰሙ በኋላ ቆጠራው በዛሬው ዕለት ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ እንደነበር ተሰምቶዋል።

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ