1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደተኞችና የ«ፕሮ አዙል» ጥሪ

ረቡዕ፣ መስከረም 21 2007

ወደ ጀርመን እና አውሮጳ ለሚመጡ ስደተኞች መብት የሚሟገተው «ፕሮ አዙል» የተባለው መንግስታዊ ያልሆነው የጀርመናውያን ድርጅት በሜዲትሬንያን ባህር በኩል አድርገው ወደ ኢጣሊያ ለመግባት ሲሞክሩ ባህር ውስጥ ሰምጠው የሚሞቱትን ስደተኞች አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ አወጣ።

https://p.dw.com/p/1DNtX
ምስል Axel Schmidt/dapd

በ10ሺ የሚቆጠሩ ስደተኞች በንዑሷ የኢጣሊያ ደሴት ላምፔዱዛ በኩል አድርገው ወደ አውሮጳ ገብተዋል፤ በመግባትም ላይ ይገኛሉ። ይሁንና፣ የባህሩን ጉዞ የሚጀምሩት ስደተኞች ሁሉ አውሮጳ በህይወት ይደርሳሉ ማለት አይደለም። እንደሚታወሰው፣ ከአንድ ዓመት በፊት ፤ መስከረም 23 በላምፔዱዛ አቅራቢያ አንድ የስደተኞች ጀልባ ሰምጦ 366 አፍሪቃውያን፣ በብዛትም ኤርትራውያን ህይወታቸውን አጥተዋል። ይኸው አሳዛኝ ሁኔታ ያኔ በአውሮጳውያን መንግሥታት ላይ ከያቅጣጫው ብርቱ ወቀሳ ነበር ያፈራረቀው። በተለይ ስደተኞቹ የመጀመሪያ መዳረሻ ያደረጉዋት ኢጣልያ፣ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በባህር ኃይሏ ባቋቋመችው « ማሬ ኖስትሩም» ወይም ሲተረጎም ባህራችን በተባለው ግብረ ኃይል አማካኝነት የመስመጥ አደጋ ያሰጋቸውን ስደተኞች የማዳን ስራ እያከናወነች ነው። እንደዚያም ሆኖ ግን ስደተኞች አሁንም በባህር እየሞቱ ነው።

በአውሮጳ ምክር ቤት በስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች ጉዳይ ክፍል ውስጥ «ፕሮ አዙል»ን የሚወክሉት ፤ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ካርል ኮፕ፤ አሳዛኙን የስደተኞች ዕጣ በተመለከተ ለአውሮጳ ኅብረት ብዙ ጥያቄ ማንሳታቸውን ገልጸዋል። ዋና የሚሉትን ሲያብራሩ፣« በዚህ ዓመት ብቻ ከ 3,000 በላይ ስደተኞች በማዕከላይ የሜዲትራንያን ባህር ውስጥ ህይወታቸውን አጥተዋል። በአውሮጳ የስደተኞች ፖሊሲ ታሪክ ውስጥ ይህን ያህል ብዙ ሰው ሲሞት የመጀመሪያ ጊዜ ነው። እነዚህ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡት ከአደጋ ነፃ የሆነ መንገድ ስላላጋጠማቸው ነው። እና እኛ አሁን የምንፈልገው አውሮጳ ስደተኞችን፣ በተለይም ሶርያውያን ስደተኞችን በትጋት እንድትቀበል ነው። 2ኛ ደግሞ አውሮጳ ለአደጋ ጊዜ የሚሆን የባህር ላይ አደጋ ተከላካይ አገልግሎት እንድትዘረጋ እና ይህን ሰው በብዝት የሚሞትበትን ድርጊት እንዲቀንስ ፣ ወይም እንዲያበቃ ነው የምንጠይቀው።

Pro Asyl feiert 25 Jahre Karl Kopp
በአውሮጳ ምክር ቤት በስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች ጉዳይ ክፍል ውስጥ «ፕሮ አዙል»ን የሚወክሉት ካርል ኮፕምስል Pro Asyl

ካርል ኮፕ እንዳስታወቁት፣ ህይወታቸው ካጡት መካከል የሶርያ፤ የኤርትራ እና የሶማሊያ ዜጎች ይገኙበታል ። የህብረቱ ድንበር ጠባቂ ጓድ፣ በምሕፃሩ «ፍሮንቴክስ» «ፍሮንቴክስ ፕላስ » በሚል መጠሪያ ስም «ማሬ ኖስትሩም»ን ስደተኞችን ለማዳን በጀመረው ተግባሩ ላይ ተጨማሪ አገዝ እንዲያደርግ ማቀዱን የአውሮጳ ህብረት ከጥቂት ጊዜ በፊት ማስታወቁ ባይዘነጋም፣ የ«ፕሮ አዙል» ቃል አቀባይ ካርል ኮፕ ይህን የህብረቱ ዕቅድ በቂ አለመሆኑን ነው ያመለከቱት።« አውሮጳ ውስጥ ስማቸውን ባሳመሩ ቁጥር አብዛኛውን ጊዜ በተግባር የሚያከናውኑት ንዑስ ሆኖ ነው የምናገኘው። ፍሮንቴክስ በመጀመሪያ ነገር የባህር ላይ አደጋ ተከላካይ አገልግሎት ሰጪ አይደለም። የ«ፍሮንቴክስ» ሀላፊነት ድንበር መጠበቅ እና መከላከል ነው። ፍሮንቴክስ ራሱ ይህን አገልግሎት መስጠት እንደማችል እና ይህ ተልዕኮው እንዳልሆነ ነው የሚናገረው። ስለዚህ ያን ያህል ውጤት እንደማያስገኝ እየታወቀ ለአንድ ተቋም የማይችለውን ሀላፊነት መስጠቱ ትርጉም አልባ ነው፣ ስደተኞቹን ለማዳኑ ተግባር ጥቂት መርከቦች እና ትንሽ ገንዘብ ብቻ እስከቀረበ ድረስ ተጨማሪ ሰዎች መሞታቸው አይቀርም። »

Deutschland Flüchtlingspolitik Pro Asyl Tote Hosen
ምስል picture-alliance/dpa

የ« ማሬ ኖስትሩም» የነፍስ አድን ተግባር በጥቅምት ግፋ ቢል በህዳር ወር ይጠናቀቃል ተብሎ ነው የሚጠበቀው። ስለዚህ ስደተኞቾች ባህር ሰምጠው እንዳይሞቱ በጊዜ መፍትሄ ሊገኝለት ይገባል የሚሉት በአውሮጳ ምክር ቤት የስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች ጉዳይ ክፍል ውስጥ «ፕሮ አዙል» ድርጅትን የሚወክሉት ፤ ካርል ኮፕ እንደ መፍትሄ የሚያዩት ፤ ሁለት ነገሮች ጠቅሰዋል። « የባህር ላይ አደጋ ተከላካይ አገልግሎትን ስራ እኛው ራሳችን እስከ ሊቢያ የባህር ክልል ድረስ በመዝለቅ ባለው ማዘጋጀት ይኖርብናል። ይህንን እኛ አውሮጳውያን በጋራ ማድረግ ይኖርብናል። ለዚህም አንድ የትብብር ስልት ያስፈልገናል። ከ100 000 በላይ የጀልባ ስደተኞች እስካሁን ኢጣሊያ ገብተዋል፤ ኢጣሊያ ስለገቡ ብቻ ኢጣሊያ ስደተኞችን የመቀበሉን እና ከለላ የመስጠቱን ኃላፊነት መውሰድ አለባት ማለት አይቻልም። እዚህም ላይ አንድ የጋራ የአውሮፓ ፖለሲ ያስፈልገናል። »

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ