1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሳኡዲ አረቢያ ያሉ አንዳንድ ኢትዮጵያውን ስሞታ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 9 2007

ሳኡዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ቢኖራቸውም በግልጽ በማያውቁት ምክንያት ታስረናል ይላሉ።ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ተገቢውን ድጋፍ አላገኙም።

https://p.dw.com/p/1E6h3
Karte Saudi Arabia und Al-Ahsa Governorate

ሙባረክ የሱፍ ከሁለት አመታት በላይ ሳኡዲ አረቢያ ኖሯል። ህይወቱን በአሽከርካሪነት የሚገፋው ሙባረክ ዛሬ በሳኡዲ አረቢያ ጅዳ አካባቢ ሽመሽ በተብሎ በሚጠራ እስር ቤት ይገኛል። ሙባረክ ለእስር የተዳረገው በሃሰት ተወንጅሎ እንደሆነ ያምናል።

«መኪና አቁሜ ሱቅ ገብቼ ነበር። የሱቁ ባለቤት መንገድ ዘግቶብኝ ነበር። የሱቁን ባለቤት ና መንገድ ልቀቅልኝ ልል ስወጣ ያዙኝ። ሴቶች አመጡና እነዚህ ካንተ ጋር ናቸው ብለው በወንጀል አስገቡኝ።»

ሙባረክ የታሰረው ብቻውን አይደለም። ደሳለኝ ወርቁ ተገኝ ለሊት በተኛበት ፖሊሶች የመኖሪያ ቤቱን በር ሰብረው ገብተው እንደያዙት ይናገራል። በወቅቱ 'ኢቃማ' ተብሎ የሚጠራውን የመኖሪያ ፈቃድ ጠይቀውት ቢያሳያቸውም ከመታሰር አላመለጠም። ለእስሩ ምክንያት የሆነው ደግሞ 'ከጎረቤት የተከራዩ ሴቶች መኖራቸው' መሆኑን እና ለአንድ ወር መታሰሩን ተናግሯል።ሌላው ኢትዮጵያዊ ሳኒ ከድር መሃመድ በዚሁ እስር ቤት አስራ ሁለት ቀናት ሆኖታል።

«የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ቢታሰሩም ወዲያው ወደ ሃገራቸው ይሸኛሉ። 'ኢቃማ' የሚባለውን ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ መያዝ ወንጀል ሆኖ ተገኝቷል። ለምን እንደሆነ አላወቅንም።» የሚለው ሳኒ ከድር መሃመድ ለእስር የታደረገው ከጸሎት በኋላ ከመስጊድ ሲወጣ ነበር።

ሳኒ ከድር መሃመድ «ከየት መጣችሁ? ለምን ተያዛችሁ? የሚለን ሰው የለም።» ሲል ያሉበትን ሁኔታ ያስረዳል። «ልብስ አይገባልንም። ፍራሽ ላይ የሚነጠፈው አንሶላውን ቀዳደን ነው ሽርጥ አድርገን የምንለብሰው።»

Saudi Arabien Riad Unruhen
ምስል AFP/Getty Images

በተመሳሳይ እስር ቤት የሚገኘው ተስፍሃዬ ተስፋይ ቢያንስ ልብስ እንዲገባላቸው ይማጸናል። ተስፍሃዬ ተስፋዬን ጨምሮ አራቱም ኢትዮጵያውያን በጅዳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤትም ሆነ በሳኡዲ አረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ችግራቸውን በዝምታ እንዳለፈው ያማርራሉ።

በተመሳሳይ መንገድ የታሰሩ የሌላ ሃገር ዜጎች በኤምባሲዎቻቸው ድጋፍ ሲደረግላቸው ተመልክተናል የሚለው ሙባረክ የሱፍ «በሳምንት አንድ ቀን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰዎች ይመጣሉ። ተሳድበው ይሄዳሉ እንጂ እንደ ዜጋ እንኳ የሚቆረቆሩ አይደሉም።» ሲል ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰዎች ተገቢውን ድጋፍ አለማግኘታቸውን ይናገራል።

ደሳለኝ ወርቁ ተገኝ አሁን በታሰሩበት የሽመሽ እስር ቤት ውስጥ በህጋዊ መንገድ የሚኖሩ ሰዎች የሚታሰሩባቸው አራት ክፍሎች መኖራቸውን በእያንዳንዱ ክፍልም እስከ ስልሳ የሚደርሱ እስረኞች እንደሚኖሩ ይገምታል። እንደ ደሳለኝ በዚህ እስር ቤት ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ በህጋዊ መንገድ በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩና የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ታስረው እንደሚገኙ ይገምታል።

ኢትዮጵያውያኑ 'ጅዋዛት' ተብሎ የሚጠራው የሳኡዲ አረቢያ ፍርድ ቤት ለተጠረጠሩበት ወንጀል ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በእስር የሚቆዩ ይሆናል። ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ተመዝግበናል ያሉት አራቱም ኢትዮጵያውያን ግን ይህ ውሳኔ መቼ እንደሚወሰን አያውቁም።

ከአንድ አመት በፊት ሳኡዲ አረቢያ ህገ-ወጥ ያለቻቸውን ከ150,000 በላይ ኢትዮጵያውያን ማባረሯ አይዘነጋም።

በጉዳዩ ላይ በጅዳ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት አስተያየት ብንጠይቅም ጥያቄያችሁን በፋክስ አስገብታችሁ ቀጠሮ ውሰዱ የሚል ምላሽ ሰጥተውናል። በሳኡዲ አረቢያ የሚገኘውን ኤምባሲ እና በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ለማነጋገር ያደረግንውም ጥረት አልተሳካም።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሃመድ