1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ቀለም ቀቢ ነኝ» ሰዓሊዉ

ሐሙስ፣ መጋቢት 3 2007

ከ 20 ዓመት በፊት በሥነ-ጥበቡ መድረክ ማበብ የጀመረዉ የዝያን ግዜዉ እንቡጥ ሰዓሊ እንግዳጌጥ ለገሰ በአሁኑ ወቅት አሉ ከሚባሉት ታዋቂ ኢትዮጵያዉያን ሰዓሊዎች ይመደባል ይላል፤ መቀመጫዉን በርሊን ላይ ያደረገዉ ሰዓሊዎችንና ስራቸዉን የሚያስተዋዉቀዉ የመገናኛ መረብ።

https://p.dw.com/p/1EpF2
Deutschland Äthiopien Atelierbesuch bei Engdaget Legesse EINSCHRÄNKUNG
ምስል Engdaget Legesse

«የስዕል ትምህርት የስውን -የእንስሳን፤ የሀገርን፤ የደመናን፤ በጠቅላላው የሥነ-ፍጥረትን መልክና ባሕሪ አጥኝ ሁኖ የራሱን ስሜት በግሉ እየፈጠረ በቀለምና በልዩ ልዩ መሳሪያዎች ከጠፍጣፋ ነገር ላይ ስርቶ ማውጣትን፤ በሐውልት ትምህርት ደግሞ አንደ ስዕሉ የተዘረዘረውን ሓሳብ ከጠፍጣፋ ነገር ላይ በመስራት ፈንታ ጠንካራ ከሆነ አካል ላይ በድንጋይ፤ በአንጨት፤ በዝሆን ጥርስ ወይም በነሐስ ቀርጾ ማውጣት ነው።» ሲሉ በአዲስ አበባ ሥነ- ጥበብ ት/በት የመጀመሪያው ርዕስ መምህር የነበሩት አለ ፈለገ ስላም ስለ ስዕል ሥነ-ጥበብ መናገራቸዉን ዘገባዎች ይጠቁማሉ።

Deutschland Äthiopien Atelierbesuch bei Engdaget Legesse EINSCHRÄNKUNG
ምስል Engdaget Legesse


ከ 20 ዓመት በፊት በሥነ-ጥበቡ መድረክ ማበብ የጀመረዉ የዝያን ግዜዉ እንቡጥ ሰዓሊ እንግዳጌጥ ለገሰ በአሁኑ ወቅት አሉ ከሚባሉት ታዋቂ ኢትዮጵያዉያን ሰዓሊዎች ይመደባል ይላል፤ መቀመጫዉን በርሊን ላይ ያደረገዉ ሰዓሊዎችንና ስራቸዉን የሚያስተዋዉቀዉ የመገናኛ መረብ። ከጎርጎረሳዉያኑ 2003 ዓ,ም ጀምሮ ኑሮዉን ጀርመን መዲና በርሊን ላይ ያደረገዉ የ44 ዓመቱ ጎልማሳ ሰዓሊ እንግዳጌጥ ለገሰ፤ እዚህ ጀርመን በርሊን ላይ ለየት ባለ የቀም ቅቡና ሥዕሎቹ ይታወቃል።


በርሊን መዲና ከመኖርያ ቤቱ ዉጭ በሚገኘዉ የራሱ አነስተኛ ስቱድዮ ዉስጥ ቀለም ያጠቀሰዉን የመሳያ ብሩሹን ቀለም እየነከረ ከሸራ እያገናኘ ዕምቅ እዉቀቱን በቀለም የሚያንፀባርቀዉ የሶስት ልጆች አባት ሰዓሊ እንግዳ ጌጥ፤ የስዕል ስቱድዮዉን ጠባብና ብዙም የፃዳች ባትሆንም እወዳታለሁ ሲል በተለይ እሱን ሊጎበኙ ለሚመጡት የመገኛኛ ብዙኃንና አፍቃሪዎች ያስረዳል።

Deutschland Äthiopien Atelierbesuch bei Engdaget Legesse EINSCHRÄNKUNG
ምስል Engdaget Legesse

በርካታ የጀርመን መገናኛዎች እንዲሁም የስዕል አፍቃሪዎች ስለ ስዕሉ አፍሪቃን፤ ሀገሩን ኢትዮጵያን፤ እያዛመዱ ይጠይቁታል። በሚኖርበት በጀርመንዋ መዲና በበርሊን ብቻ፤ ወደ 20 ሽህ የሚሆኑ፤ በከፍተኛ ትምህርት የተደገፉ ሰዓልያን እንደሚገኙ ብሎም እንደ ሰዓሊ በአዉሮጳ ዉስጥ ኑሮን አሸንፎ መኖር ቀላል እንዳልሆን ይገልፃል፤ ጀርመናዉያን ለሥነ-ጥበብ ያላቸዉ አክብሮት እጅግ ከፍተኛ መሆኑንም ሳይናገር አያልፍም።


አፍሪቃዊ ሥነ-ጥበባዉ ቁሶችን መሰብሰብ በሚወዱት አባትዋ በኩል ሰዓሊ እንግዳጌጥን በልጅነት እድሜዋ የተዋወቀችዉ ጀርመናዊትዋ፤ ሳቢነ ዛሃዉ፤ ከብዙ ዓመታት በኋላ ዳግም በርሊን ላይ ካገኘችዉ በኋላ ስራዎቹን በማስተዋወቅ ድረ- ገፅ በማዘጋጀት ሥራ እገዛ እንዳደረገች ትገልፃለች። የሰዓሊ እንግዳጌጥ ገሰን የሥነ-ጥበባዊ ሥራዎቹም በፊት ከምታዉቀዉ ስራዎቹ ለየት ብለዉ ነዉ ያገኘቻቸዉ፤

Deutschland Äthiopien Atelierbesuch bei Engdaget Legesse EINSCHRÄNKUNG
ምስል Engdaget Legesse


«ከብዙ ዓመታት በኋላ ዳግም ሳገኘዉ ሥራዎቹ ከእንጨት ጋራ ሆኖ ነዉ ያገኘኋቸዉ። በየዓመት ሁለት ዓመቱ የስራዉ አቅጣጫ ሲቀያየርም አይቻለሁ። እኔ እንደሚገባኝ የሥነ-ጥበብ ሥራን ሲጀምር አንድ ርዕስ ላይ ያተኩራል፤ በራሱ አባባል ያንፀባርቀዋል። ሌላ ርዕስን በመቀጠል ይይዛል። ትክክል እየሰራ ነዉ ብዬ አምናለሁ። እያንዳንዱ የሥነ-ጥበብ ሰዉ ስራዎቹ አኗኗሩን ይመስላሉ። እንደኔ እምነት እንግዳጌጥ ለብዙ ዓመታት ጀርመን ዉስጥ በመኖሩ ለስዕል፤ ለሥነ-ጥበብ ያለዉ አመለካከት በሆነ መንገድ ተቀይሮአል። ኢትዮጵያ ዉስጥ ሳለ የሚስላቸዉ ሥዕሎች አሁን ካሉት ጋር አይመሳሰሉም፤ ምናልባትም እዝያ ሳለ፤ ቶሎ ለገበያ የሚዉሉ አይነት አሳሳል ስልት የነበረዉ ይመስለኛል። እንግዳጌጥ በአሁኑ ወቅት ልዩ የአሳል ስልት የተካነ ብቸኛ እና የራሱን መንገድ ይዞ እየሰራ ነዉ።»


በጀርመን የሌስትሮን ታታሪ ሰራተኝነትና ምንነቱን በማሳወቃቸዉ የሚታወቁት፤ የቀድሞዉ ሊስትሮ አሁን ጀርመን መዲና በርሊን ላይ የሚገኘዉ የሊስትሮ ፕሮጀክት መስራችና ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ሻንቆ እንደሚሉት ታዋቂዉ ሰዓሊ እንግዳጌጥ በሊስትሮ ጋለሪ ዓዉደ ርዕይ አዘጋጅቶ ብዙዎችን አስደምሞአል።

Deutschland Äthiopien Atelierbesuch bei Engdaget Legesse EINSCHRÄNKUNG
ምስል Engdaget Legesse


በበርሊን እና በሃንቡርግ የስዕል ሥራዎችዋን በማቅረብ የምትታወቀዉ ሌላዋ ኢትዮጵያዊት የሥነ-ጥበብ ሰዉ የእናትፋንታ አባተ ሰዓሊ እንግዳጌጥ ለገሰን የምታዉቀዉ በአዲስ አበባ በሚገኘዉ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ሳሉ ነዉ። እንግዳጌጥ በኢትዮጵያ ተማሪ ሳለ ጀምሮ በልዩ አይነት ቀለም ቅቡ እጅግ የተዋጣለትና የታወቀ እንደነበር ገልፃለች። ጀርመን ከመጣ በኋላ ደግሞ የአሳሳሉ ሁኔታ ተቀይሮ ሌላ መልክን ይዞአል፤ የራሱን መንገድ እየያዘ ነዉ እጅግ ጥሩ ደረጃ ላይ ነዉ ስትል ገልፃለች።

Deutschland Äthiopien Atelierbesuch bei Engdaget Legesse EINSCHRÄNKUNG
ምስል Engdaget Legesse


ስሜቱን በቃላት ሰንቆ የመግለፅ ተሰጥዖ እንደሌለዉ የሚገልፀዉ ሰዓሊ እንግዳ ጌጥ ለገሰ፤ ስዕሎቹ የተለዩ ምልክቶች ብሎም ምስጥሮች ያዘሉ መሆናቸዉን በተለይ በዘርፉ ያሉ ባለሞያዎች ይመሰክሩለታል። ሰዓሊ እንግዳጌጥ ለገሰ በጀርመን መኖር ከጀመረ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመላለስ በተለይ አዲስ አበባ ዉስጥ፤ የስዕል ትርዒትን ማሳየቱን ገልፆልናል። በቅርቡም ስዕሎቹን ሳይሆን መሳያ መቀብያ ቡሩሹን በኪሱ ይዞ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኝ ተናግሮአል። ሰዓሊ እንግዳጌጥን ለገሰን እደግ ተመንደግ እያልኩ ቃለ ምልልስ የሰጡንን እንግዶቼን አመሰግናለሁ። ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫዉን ማዕቀፍ በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ