1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሻጭ እና ገዢ በቀላሉ በኢንተርኔት ሲገናኙ

ዓርብ፣ ነሐሴ 16 2006

ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ሻጭ እና ገዢ በድረ ገፆች ይገናኙ ጀምረዋል።እንዴት? የተለያዩ ድረ ገፆችን የሰራው ወጣት ያብራራልናል። በኢንተርኔት ግብይት የዛሬው ርዕሳችን ነው ።

https://p.dw.com/p/1Cyvg
Firmenlogo mekina.net
ምስል Araya Lakew

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ ሀገራትም ከጊዜ ወደ ጊዜ የኢትንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። አብዛኞቹ ተጠቃሚዎች እንደ ፌስ ቡክ እና ኢሜል ያሉ የማህበራዊ መገናኛ ገፆችን ሲጎበኙበበለፀጉት ሀገራት የሚኖሩ ደግሞ ከዚህም ሌላ የበገበያያ ድረ ገፆችን በመጎብኘት ይገበያያሉ። የድረ ገፅ ባለሙያ የሆነው አርዓያ ላቀው ይህንን ኢትዮጵያ ውስጥ ከአራት ዓመታት በፊት ሲጀምር ለመኪና ፈላጊዎች እና ሻጮች አንድ ድረ ገፅ በመስራት ነው።

ምንም እንኳን አርዓያ ይህንን ከ4 ዓመት በፊት ሲጀምር፤ የኢንተርኔት ተጠቃሚውም ሆነ የመኪና ፈላጊው ቁጥር ከፍተኛ ባይሆንም፤ ገፁን የሚጎበኙ በርካታ ተጠቃሚዎች ግን ነበሩ ይላል ። ይህ ጥሩ መነሻ እንደሆነው የሚናገረው አርዓያ ዛሬ ሌሎች ሻጭ እና ገዢ የሚገናኙበት ድረገፆችንም ሰርቷል።

አርዓያ እንደገለፀልን ሶስቱን ድረ ገፆች የሚጎበኙ ሻጮችም ሆኑ ገዢዎች ለጊዜው በነፃ ነው የሚገለገሉት።ወደፊት ግን ልክ እንደ መኪና ድረ ገፁ ለሻጮቹ የተወሰነ ክፍያ ይጠይቃል። ተስፋዬ ለማ የመኪና ደላላ ነው። ይህንን ድረ ገፅ ካገኘ ጀምሮ መኪኖችንም ሆነ ቤቶችን በፍጥነት ለማሻሻጥ ድረ ገፁን ይጠቀምበታል።ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ ደላላው ተስፋዬ ከገዢም ሆነ ሻጮች ጋር ሲገናኝ ችግሮች ይገጥሙታል። አንዱ ችግሩ የሰዎች የቀጠሮ አለማክበር ሲሆን ሌላው ትልቁ ችግር ደግሞ ክህደት ነው።

Araya Lakew
አርዓያ ላቀውምስል Araya Lakew

የድረ ገፅ ባለሙያው አርዓያ ብዙም ከዚህ ችግር ጋ አይጋፈጥም። እሱ የድረ ገፅ ስራው ላይ ሲያተኩር አብሮት የሚሰራው ሚኪያስ ገብረ እየሱስ ደግሞ ከንግድ ደንበኞች ጋር በቅርበት ይሰራል።እነ ሚኪያስ ሁለቱን አካላት ስለገበያው ዓላማ ከማስተዋወቅና ማሳመን ስራ ውጪ እግረ መንገዳቸውንም ገፃቸው ላይ ስለሚያወጡት ማስታወቂያ ለማጣራት የሚሞክሩበት መንገድ እንዳለ ሚኪያስ ገልፆልናል።ከዚህ ባለፈ ድረ ገፁ ላይ ስለሚወጡት መኪናዎችም ሆነ ቤቶች ሙያዊ ዕውቀት እንዲኖረን ማወቅ አይጠበቅብንም የሚለው አርዓያ አሁን ባለው ሁኔታ ላይ ተመርኩዞ ወደፊት በተለይ አዲሱ ትውልድ ከቤቱ ሆኖ የሚፈልጋቸውን ነገሮች በኢትንተርኔት እንደሚገበያዩ አርዓያ ባለ ሙሉ ተስፋ ነው።

ከድረ ገፅ ባለሙያ አርዓያ ላቀው ፤ አብሮት ከሚሰራው ሚኪያስ ገብረ እየሱስ እና ይህንን ድረ ገፅ መኪናዎችን ለማሻሻጥ ከሚጠቀመው ደላላ ተስፋዬ ለማ ጋር የነበረንን ቆይታ ከድምፅ ዘገባው ያገኙታል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ