1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደተኞች በሊቢያ የሚገጥማቸው ፈተና

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 22 2007

በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በየጊዜው ከሊቢያ ተነስተው በሜዲቴራንያን ባህር በኩል ወደ ኢጣልያዋ ደሴት ላምፔዱዛ ያቀናሉ ።ስደተኞቹን ጭነው ከሚጓዙት ጀልባዎች አብዛኛዎቹ ለባህር ጉዞ የማይመጥኑ ደካማ ጀልባዎች ናቸው ማለት ይቻላል ። ሊቢያ የባህር ድንበር ላይ ግን ይህን የሚቆጣጠርም ሆነ የሚከለክል አንድም አካል የለም ።

https://p.dw.com/p/1FITz
Libyen Rettung von Flüchtlingen durch Küstenwache EINSCHRÄNKUNG
ምስል Küstenwache Libyen

የዶቼቬሌዎቹ ማርሊን ዱማስና ሃይከ ፊሸር እንደዘገቡት ወደ አውሮፓ ለመሄድ የሚፈልጉ ስደተኞች መነሻሪያ ከሆነችው ከሊቢያ የባህር ዳርቻ በየቀኑ ማለት ይቻላል በለንቋሳ ጀልባዎች በርካታ ስደተኞች አደገኛውን የሜዲቴራንያን ባህር ጉዞ ይጀምራሉ ። የተሻለ ህይወት ፍለጋ በጀልባ ወደ አውሮፓ ከሚሰደዱት ከእነዚህ ሰዎች አብዛኛዎቹ በጉዞ ላይ የውሐ ሲሳይ ሆነው ይቀራሉ ። በርካቶች መንገድ ላይ እንደሚሰጥሙ በተደጋጋሚ የሚነገር ቢሆንም የስደተኞቹ መነሻ ከሆነችው ከሊቢያ በኩል እንደሚጠበቀው ለአስቸኳይ እርዳታ የሚደርስ የለም ። ዋና ከተማይቱ ትሪፖሊ የሚገኙ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ያልተለመደ ዝምታን መርጠዋል ። ሁኔታውን ለሚታዘብ ሥራ ያቆሙ ነው የሚመስለው ። ሹቢ ቢሸር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሃላፊዎች አንዱ ናቸው ።ስራቸውን በአግባቡ እንዳያካሂዱ ችግር መኖሩን ይናገራሉ ። ከችግሩ አንዱ የመርከቦች መለዋወጫ እጥረት ነው ። በዚህ የተነሳም አንዳንዴ የግል ንብረታቸውን ለመጠቀም መገደዳቸውን ያስረዳሉ ።
« የራሴ ጀልባ አለኝ ። አንዳንዴ ርሱን እንጠቀማለን ። ሥራውን የምናካሂደው በግል ንብረታችን ነው ። »
ካለፈው ጥር አንስቶ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂ የድንበር ቁጥጥር ሥራ አቁሟል ። ድንበር ተቆጣጣሪዎች የሚንቀሳቀሱት ስደተኞችን የጫነ ጀልባ ወደ ኢጣላያዋ ደሴት ላምፔዱዛ በማቅናት ላይ መሆኑን የሚጠቁም መረጃ ካገኙ ብቻ ነው ። የሊቢያ የባህር ጠረፍ ርዝመት 1800 ኪሎሜትር እንደመሆኑ ከሊቢያ ወደ ኢጣላያዋ ደሴት ላምፔዱዛ የሚሄዱ ስደተኞችን ያሳፈሩ ጀልባዎችን ለይቶ ማግኘቱ አስቸጋሪ ነው ። የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እንደሚለው ሊቢያ ውስጥ ወደ አውሮፓ ለመሄድ የሚጠባበቁ 1 ሚሊዮን ሰዎች አሉ ። በሃገሪቱ ያለ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሚገኝ ማንኛውም ስደተኛ መጨረሻው የስደተኞች ማጎሪያ ነው የሚሆነው ። ከቀድሞ የሊቢያ መሪ ሞአመር ጋዳፊ ሞትና ከመንግሥታቸው ውድቀት በኋላ አብዛኛው የሊቢያ ክፍል በተለያዩ ሚሊሽያዎች ቁጥጥር ስር ነው ።ይህም ህገ ወጥ የሰዎች አሸጋጋሪዎች ከመላ ሃገሪቱ ስደተኞችን እየሰበሰቡ በጀልባዎች አጭቀው ወደ አውሮፓ እንዲልኩ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል ። ስደተኞቹን ይዘው የሚሄዱ ጀልባዎች ችግር ሲገጥማቸው የሚያሰሙት ጥሪ የሚደርሰው የባህር ጠባቂ በአካባቢው ከተገኘ ሊታደጋቸው ይችላል ። የሊቢያ የባህር ጥበቃ ሃላፊ ሞሀመድ ባይቲ እንደሚሉት ከሚታደጓቸው ስደተኞች አብዛኛዎቹ ግን ሊቢያ መመለስ አይፈልጉም ።
«አፍሪቃውያኑ ወደ ሊቢያ መመለስ አይፈልጉም አንዳንድ ትላልቅ መርከቦች ላይ ስናሳፍራቸው ያለቅሳሉ ። መርከቡንም ለማበላሸት ይሞክራሉ ።የለም ወደ ሊቢያ አንመለስም ይሉናል ።»
ከትሪፖሊ በስተምዕራብ 50 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ዛውያ በተባለው ስፍራ በሚገኝ የስደተኞች ማጎሪያ ውስጥ ከሚገኙት አንዱ ሴኔጋላዊው ላሚን ኬቤ ነው ። ኬቤ ከአንድ ዓመት በፊት ነው ሊቢያ የመጣው ።
«የተሻለ ህይወት ተስፋ አድርጌ ነው ወደ ሊቢያ የመጣሁት ። መሥራት እፈልጋለሁ ። የወደፊቱን ህይወቴን ማስተካከል እሻለሁ ።ይህ በሊቢያ የሚሳካልኝ ከሆነ እዚሁ እቀራለሁ ። ካልሆነ ግን ወደ ሌላ ሃገር ለመሄድ እሞክራለሁ ።»
የሊቢያ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሊቢያ ውስጥ 8ሺህ የሴኔጋል ስደተኞች እንዳሉ ተናግረዋል።በማጎሪያ ስፍራ ህይወት አስቸጋሪ ቢሆንም ኬቤና ሌሎች 420 መሰሎቹ አሁንም ሊቢያ ሲመጡ ከያዙት ተስፋ ጋር ናቸው ።እዚያ መስራትም ሆነ ከሃገር መውጣት አይችሉም ። ሌላው ሴኔጋላዊ ቡባከር ጋሪ እንደሚናገረው ሊቢያ ውስጥ የተያዙበት መንገድ አሳዛኝ ነው ።
«በክፍላችን ውስጥ ይቆልፉብናል ።እንደ ውሻ ነው የሚይዙን»
የዛዊያውን ካምፕ የሚጠብቁት መቶ አለቃ ካሌድ አቱሚ ስደተኞች አንዳንዴ ከሚሰጣቸው ዳቦ በስተቀር ምግብ እንደማያገኙ ነው የሚናገሩት።

Symbolbild Flüchtlingsboot vor Lampedusa
ምስል picture alliance/JOKER
Libyen Küstenwache - Soubhi Bish
ምስል DW/M. Dumas

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ